ማይክ ሐመር (አምባሳደር)

ዜና ‹‹የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ አልሸባብን ለመዋጋት ዋጋ ከፍለዋል›› ማይክ ሐመር (አምባሳደር)፣ የአሜሪካ ልዩ…

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: September 15, 2024

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል እንደገና ጦርነት መቀስቀስ የለበትም ብለዋል

የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ የሚገኘውን አሸባሪውን አልሸባብን በመዋጋት ከፍተኛ ዋጋ መክፈላቸውን፣ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር (አምባሳደር) ተናገሩ፡፡ የአሜሪካ መንግሥት አሸባሪውን አልሸባብ ለመውጋት ምን ማድረግ አለበት የሚለው ጉዳይ እንደሚያሳስባትም አስታውቀዋል፡፡

ልዩ መልዕክተኛው ከሰሞኑ በአውሮፓና በአፍሪካ ለሁለት ሳምንታት በጀመሩት ጉብኝት፣ በኢትዮጵያ ከትግራይ ክልልና የፌዴራል መንግሥቱ ተወካዮች ጋር መነጋገራቸውን ዓርብ መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

የአሜሪካ መንግሥት ግልጽ ዕሳቤ አልሸባብን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት የሁለቱን አገሮች መልካም ግንኙነት ያስፈልጋል የሚል ነው ብለዋል፡፡ አክለውም ከኢትዮጵያና ከሶማሊያ መሪዎች ጋር በሚያደርጉት ንግግር ችግራቸውን በውይይት እንዲፈቱና የአፍሪካ ኅብረትን የድንበር ሉዓላዊነት፣ አንድነትና ኅብረት መሠረታዊ ቻርተር ለአገሮቹ ዋነኛ ዋስትና መሆኑን ማክበር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

ከ15 ዓመታት በላይ በአልሻባብ የምትታመሰውን ሶማሊያ ደኅንነት ለማረጋገጥ የኢትዮጵያ ወታደራዊ ድጋፍ ሚና ቁልፍ እንደነበር፣ የኢትዮጵያን መንግሥት ጨምሮ በርካቶች በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡

የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ በዚሁ መግለጫቸው በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል እንደገና ጦርነት እንዲቀሰቀስ እንደማይፈለግ፣ እንዲሁም በሁለቱም አገሮች ዘንድ ምንም ዓይነት የድንበር ቅሬታ ሊኖር አይገባም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት ተወካዮች እ.ኤ.አ. በ2000 በአልጀርስ የተፈራረሙትን የድንበር ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዲያደርጉ መርዳት ቢቻል፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ምንም ዓይነት ውዝግብ ሊፈጠር አይችልም ሲሉም አስረድተዋል፡፡

በትግራይ ክልል በተካሄደው ጦርነት ለተፈጸሙ ጥሰቶች ተጠያቂነት መረጋገጥ ወሳኝነት አለው ያሉት ሐመር (አምባሳደር)፣ የተካሄደው ጦርነትም በምድራችን የከፋው ነበር ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ጦርነቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲገታ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተካሄደው ስምምነት ተዋዋይ ወገኖች ዘንድ የነበረው ተነሳሽነት፣ ብርታትና የፖለቲካ ቁርጠኝነት በአፈጻጸሙ ላይም ተመሳሳይ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

‹‹የፕሪቶሪያ ስምምነት ሲካሄድ በነበርኩበት ወቅት ብዙዎች የተኩስ አቁም ስምምነቶች እምብዛም ሲዘልቁ እንደማይታዩ ነግረውኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ይኼኛው እዚህ ደርሷል፡፡ በመሆኑም ይህንን ውጤት እንደ ቀላል ልናየው አይገባም፤›› በማለት ሁለቱ ወገኖች ለስምምነቱ ተገዥ እንዲሆኑ ጥሪት አቅርበዋል፡፡ አክለውም በትግራይ ክልል ሰላም መታየቱ ለመላው ኢትዮጵያ መልካም ነው ብለው፣ ነገር ግን አሁንም የሰላሙ ጉዳይ ይቀረዋል ብለዋል፡፡  

ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ምክትሉ ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ፣ እንዲሁም ከሕወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ጋር መነጋገራቸውንና ለክልሉ ሰላም ቁርጠኛ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በድጋሚ ወደ ጦርነት የሚያስኬድ ምንም ዓይነት ጉዳይ አይኖርም ሲሉ አክለዋል፡፡ 

ይሁን እንጂ ልዩ መልዕክተኛው በፓርቲ ደረጃ በሚታየው አለመግባባት አገራቸው አሜሪካ ጣልቃ መግባት እንደማትፈልግ ገልጸው፣ ችግሩ በአገር ውስጥና ቀጣናዊ የመፍትሔ አማራጮች ሊፈታ ይገባል ብለዋል፡፡