የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ

ዜና በኢትዮጵያ የፖለቲካ አመራሩ ዴሞክራሲን ማስፈን ከፈለገ እንደሚችል ተሰናባቹ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ተናገሩ

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: September 15, 2024

‹‹ታሪክ እንደሚያሳየው ፈላጭ ቆራጭ መንግሥታት ከዴሞክራሲ መንግሥታት ያጠረ ዕድሜ አላቸው? በማለት የሚታወቁት ተሰናባቹ የአውሮፓ ኅብረት ሮላንድ ኮቢያ (አምባሳደር)፣ ‹‹የኢትዮጵያ መሪዎች ዴሞክራሲን ማምጣት ከፈለጉ አገሪቱ ይህንን ማድረግ በምትፈለግበት ወቅት ማሳየት እንደምትችል አይተናል፤›› በማለት ተናገሩ፡፡  

በኢትዮጵያ የነበራቸውን ቆይታ ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ፣ በኢትዮጵያ ከሚገኘው የአውሮፓ ቻምበር ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ በርካታ ጉዳዮችን ዳሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ የምታደርገው ጉዞ ከሌሎች የሰው ልጆች ሒደት ጋር የተለየ አለመሆኑን፣ ነገር ግን ጅማሮው የዘገየ መሆንና ሒደቱ ቀላል ባይሆንና ወጥነት ባይኖረውም ጉዞው የራሱ መንገድ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2021 የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሆነው ወደ አዲስ አበባ የመጡት ኮቢያ፣ በትግራይ ክልል የነበረው ጦርነት ቢቆምም በሌሎች አካባቢዎች ግጭቶች ተባብሰው መቀጠላቸውን አስታውቀዋል፡፡

በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ለሰላም ዕጦቶች ስምምነት እንደሚያስፈልግ፣ ነገር ግን ሁልጊዜም ተመሳሳይ ዓይነት የመፍትሔ አማራጭ እንደማይኖር አስረድተዋል፡፡  

‹‹በኢትዮጵያ ሙስና፣ እንዲሁም የሲቪክና የሚዲያ ምኅዳር በሚያሳዝን ሁኔታ መሻሻል አልቻለም፤›› ያሉት ተሰናባቹ አምባሳደር፣ ችግሩ በፍጥነት ቶሎ ካልተገታ አስቸጋሪ እንደሚሆንና አዝማሚያው የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ገጽታ የሚንድ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ወዳጅነቷን ለማስተካከል እየሞከረች እንደሆነችና አዳዲስ ሞዴሎችን፣ በተለይም ብሪክስ የተሰኘውን ቡድን መቀላቀሏ የዚህ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ እያካሄደችው ያለው የኢኮኖሚ ሪፎርም ከተለመዱት የፋይናንስ ምንጮች፣ በተለይም በአውሮፓ ኅብረትና በአውሮፓ ኅብረት አገሮች በሚደገፉት የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ ውጪ ትርጉም ያለው የፋይናንስ አማራጭ ከሌሎች አታገኝም ሲሉም ተናግረዋል፡፡

አምባሳደሩ በርካታ ጉዳዮችን በነካኩበት በዚህ ቃለ መጠይቅ፣ ኢትዮጵያ በቀጣናው ተቀባይነቷን ለመጨመር ከጎረቤት አገሮች ጋር ከውጥረት ነፃ የሆነ ግንኙነት ልትፈጥር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ምቹ የኢንቨስትመንት ምኅዳር ለመፍጠር ብዙ ሥራዎች ይቀሯታል፤›› ያሉት አምባሳደሩ፣ ‹‹በግልጽ ለመናገር ተመራጭ አይደለችም፡፡ አውሮፓውያን ብቻ ሳይሆኑ የእስያና የመካከለኛው ምሥራቅ ኩባንያዎች ኢትዮጵያን ጥለው ሄደዋል፡፡ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ዋስትና ባለማግኘታቸው ምክንያት ጥለው ወጥተዋል፡፡ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2023 688 ሚሊዮን ይሮ የሚያወጡ ምርቶችን ወደ አውሮፓ ገበያ ልካለች፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የመርካቶ ገበያን እንደጎበኙ የተናገሩት አምባሳደሩ፣ በዚህ ገበያ ጥቅም ላይ የዋሉ ቁሳ ቁሶችን እንደገና የመጠቀም ባህል አድንቀው በዚህም መርካቶ ባይኖር ኖሮ ከተማዋ ትቆሽሽ ነበር ብለዋል፡፡

‹‹መርካቶ ባይኖር ኖሮ ብዙ ሰዎች ሥራ አጥ ይሆኑ ነበር፡፡ የኑሮ ውድነት ድህነትን ይጨምራል፡፡ በመሆኑም መርካቶ እንደ ቅርስ ቢጠበቅና መልሶ ማልማት ወይም የኮሪደር ልማት ባይነካው እመኛለሁ፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ አክለውም አርቲስቶችና ሙዚቀኞች በውጭ አገሮች ምርጥ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ናቸው ብለው፣ ባህላዊ ቦታዎችን መጠበቅ ኢትዮጵያን እንደሚያደምቅ ተናግረዋል፡፡