ዜና ‹‹በጦርነቱ በሚሳተፉት በሁለቱ ኃይሎች መካከል ያለው ሥር የሰደደ አለመተማመን ፈተና ሆኖብናል›› የአማራ…

ሔለን ተስፋዬ

ቀን: September 15, 2024

በአማራ ክልል በሚፋለሙት የፌዴራል መንግሥትና የፋኖ ኃይሎች መካከል ያለው ሥር የሰደደ አለመተማመን ሰላም ለማውረድ የሚያደረገው ጥረት ፈተና እንደሆነበት፣ የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል አስታወቀ፡፡

የካውንስሉ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያቸው ተሻለ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች መካከል መተማመንን ለመፍጠር የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ዕገዛ ለማግኘት በቅርቡ ወይይት ተደርጓል።

የፌዴራል መንግሥት አመራሮችን ለማግኘት የካውንስሉ ጥረት አለመሳካቱን፣ እስካሁን ከፌዴራል መንግሥት በኩል ተገናኝቶ መወያየት የቻለው ከሰላም ሚኒስቴር ጋር ብቻ እንደሆነ፣ የሰላም ሚኒስቴርም ካውንስሉ የሚያቀርበውን ጥሪ እንደሚቀበል ማሳወቁን ገልጸዋል። 

‹‹ከተለያዩ የፋኖ ኃይሎች ጋር ተነጋግረናል፣ ወደ ድርድር መግባትን በመርህ ደረጃ ይቀበሉታል፡፡ ነገር ግን በመንግሥት ላይ እምነት የላቸውም። ጊዜ መግዣ ነው ብለው ያምናሉ፣ እኛንም የፈተነን ይኸው ያለመተማመን ችግር ነው፤›› ብለዋል።

‹‹ከፌዴራል መንግሥት በኩል ተጨማሪ ሥራዎች ይጠብቁናል፤›› ያሉት አቶ እያቸው፣ ‹‹የፌዴራል መንግሥት ለሰላም ዝግጁ መሆኑን መናገር ብቻ ሳይሆን ምቹ ሁኔታን መፍጠር አለበት፤›› ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል። 

በሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች መካከል መተማመንን ለመፍጠር ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዕገዛ ለማግኘት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር፣ ከኢጋድና ከአፍሪካ ኅብረት አመራሮች ጋር በቅርቡ መወያየታቸውን አስረድተዋል።

‹‹ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር ተነጋግረናል፣ ለማገዝም ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸውልናል፡፡ በእኛ በኩል ደግሞ እየደረሰ ካለው ጉዳት አንፃር የአማራ ክልል ሁኔታን ችላ ብላችሁታል ብለናቸዋል፤›› ሲሉ አስረድተዋል።

የአሜሪካ አምባሳደርን ጨምሮ ከስድስት ዲፕሎማቶች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን፣ በውይይቱም የክልሉን የሰላም ዕጦት ችላ ማለታቸውን በመጠቆም ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ ማሳደር እንደሚገባቸው ካውንስሉ ማሳሰቡን ጠቁመዋል፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ባለቀበት መንገድ የአማራ ክልል ጉዳይንም በዚያው መንገድ ማጠናቀቅ እንደሚገባ ማስረዳታቸውን፣ ካውንስሉ የገጠመውን የቅቡልነት ችግርና በሁለቱ ተፈላሚ ኃይሎት መካከል ሥር የሰደደ አለመተማን መኖሩን ማስረዳታቸውን ተናግረዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ካውንስሉ የሚያደርገውን ጥረትም ሆነ ድርድሩ እንዲሳካ ለማገዝ ፈቃደኛ መሆኑን፣ ነገር ግን በፋኖ አደረጃጀት ላይ ጥያቄ ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡ 

ከየትኛው የፋኖ አደረጃጀት ጋር ተገናኝተው እንደተወያዩ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ይህንን መናገር አያስፈልግም፣ ምክንያቱም አንዳንዶች ነገሩን እገሌ ሊደራደር ነው በማለት መበሻሸቂያ አድርገውታል፡፡ በመሆኑም ከየትኛው የፋኖ አመራር ጋር እንደተወያየን መግለጽ ጠቃሚ አይደለም፤›› ብለዋል።

‹‹እገሌ ሊደራደር ነው የሚለውን ጉዳይ የፋኖ ኃይሎች እንደ መበሻሸቂያ እየተጠቀሙበት ስለሆነ፣ ካውንስሉ የተደራጀ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ በፋኖ በኩል እገሌ እንዲህ ብሏል ከማለት እንቆጠባለን፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

በፋኖ ኃይሎች በኩል ከሚነሱ ጥያቄዎች መካከል ዋነኛው የፌዴራል መንግሥት ድርድሩን ‹‹እንደ ጊዜ መግዣነት ሊጠቀምበት ነው›› የሚል ጥርጣሬ መሆኑን የገለጹት አቶ እያቸው፣ ከዚህ በተጨማሪም ካውንስሉ ሀቀኛ ድርድር ለማድረግ ሳይሆን ለማምታታት ነው የሚል ሐሳብ እንዳላቸው፣ ይሁንና አለመተማመኑን ለመቅረፍ የሁሉንም አካላት ቅንነት ካውንስሉ እንደሚፈልግ ተናግረዋል፡፡

ካውንስሉ ከፌዴራል መንግሥት በኩል እስካሁን መወያየት የቻለው ከሰላም ሚኒስቴር ጋር ብቻ መሆኑን አቶ እያቸው አስታውሰው፣ ይሁንና መንግሥት የድርድር ጥሪውን እንደሚቀበል መናገሩ ብቻ በቂ ስላልሆነ፣ ለሰላም የሚያስፈልጉ ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠር ጀምሮ ተጨማሪ ዕርምጃዎችን መውሰድ እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡

ከአሜሪካ ኤምባሲ በተጨማሪ ከኢጋድ የፀጥታ ዳይሬክተር ጋር መወያየታቸውንና የአውሮፓ ኅብረት፣ የአፍሪካ ኅብረትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትን ለማግኘት ቀጠሮ መያዛቸውን አስረድተዋል፡፡

በአገር ውስጥ ከሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጋር መወያየታቸውን፣ ከጉባዔው ጋር በነበራቸው ውይይት እንደሚያግዟቸው ቃል መግባታቸውን ኃላፊው አክለዋል፡፡