አስተያየት

September 15, 2024

በሽብሩ ተድላ (ፕሮፌሰር ኤሜሪተስ) እና ገዛኸኝ ይርጉ (ፕሮፌሰር)

መግቢያ

ሳይንሳዊ አስተሳሰብን፣ ብሎም የሳይንስን ዕውቀት በማኸዘብ (ብዙ ሰው በቀላል መንገድ እንዲገነዘብ ማድረግ)፣ በምክንያት ላይ የተመሠረቱ፣ ብዙ ጠቃሚ ተግባራትን የሚያከናውን ኅብረተሰብን ለመመሥረት ይረዳል፡፡ ለሰው ልጅ ጥቅምን የሚያበረክቱ የቁስ አካል ይዘትና ሁኔታ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መተንተንና ለንባብ ማቅረብ፣ የሳይንሳዊ አስተሳሰባችንን እና ሳይንሳዊ  እውቀታችንን ለማዳበር ያግዛል፡፡ በዚህች ጽሑፍ በ ሥነ ምድር የዘመን መተመን ስልት፣ ብሎም በዚህ ስልት የሚገኘው ውጤት ሳይንሳዊ ጠቀሜታ ምን ይመስላል የሚለው ይዳሰሳል፡፡ ስለ ዘመን መተመን ስልት ስናወሳ፣ ስለ አካባቢው ውስን ሳይንሳዊ ግንዛቤ እናወሳለን፣ ይኸም የሳይንሳዊ አስተሳሰብን ተግባር ያዳብራል፡፡

በሥነ ምድር የዘመን አቆጣጠር ስልትና ቅርሰ ሕይወት (fossils) ዕድሜ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የምድር ዕድሜ 4.6 ቢሊዮን ዓመታት ገደማ ነው። እንዲሁም፣ ዳይኖሶሮች (Dinosaurs) በዓለም ላይ ገነው የነበረው ከ60 ሚሊዮን ዓመታት በፊት ነበር ተብሎ ሲወሳ፣ እንዴት ነው እዚያ ዘመን ስሌት ላይ የተደረሰበት?፣ ዘመኑ እንዴት ተሰላ፣ የሚል ጥያቄ አብሮ ይወሳል፡፡ መልሱ ምንም ውስብስብ ሳይንሳዊ ይዘት ያለውና በረቀቀ የሒሳብ ስሌት እንዲሁም የጠለቀ የፊዚክስ ዕውቀት ላይ የተመሠረተ ቢሆንም፣ በዚህች ጽሑፍ የረቀቀውን የሒሳብ ስሌትም ሆነ የፊዚክስ ዕውቀት በግርድፉ ዳሰን ዘመን እንዴት  እንደሚተመን ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡ ዋናው የመረጃ ምንጭ ምድር የተገነባችበት  ጥሬ ዕቃ ማለትም  ከአለቶችና ማዕድናት ባህርያት ናቸው፡፡

በምድራችን የተከሰቱ ኩነቶችና አጠቃላይ ገጽታ

በምርምር ሒደት እንደተደረሰበት፤ ምድር  እውን የሆነችው ከእኛ ፀሐይና ከሌሎቹ ስምንት ፕላኔቶች ጋራ በአንድ ጊዜ ከ4.6 ቢሊዮን ዓመታት በፊት ከነበረ ብናኝ/ደቂቅ ቁስ አካል ስበታዊ ስብስብ ነው፡፡ ከዚያም ምድር ከጊዜ ብዛት በአካባቢው ይንቀሳቀሱ ከነበሩ ደቃቅ “ፕላኔታዊ” አካላትን ወደራሷ በመሳብ መንስዔ መጠነ ብዙ ቁስ በገላዋ ላይ አከማችታለች፡፡ ከጥቂት ዘመን በኋላም የምድራችን አጃቢ ጨረቃ ተመሠረተች፡፡

በሥነ ምድር የዘመን አቆጣጠር ስልትና ቅርሰ ሕይወት (fossils) ዕድሜ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ምድራችን በእጅግ ከፍተኛ ሙቀት ስትመሠረት የቀለጠ አለት ይዘት ነበራት። ከጊዜ ብዛት የላይኛው/ውጫዊው ሽፋን ቀስ በቀስ ቀዝቅዞ ወደ ድንጋይነት/ጠጣር አለትነት፣ በስተመጨረሻም አለቱ በአየር እና በውኃ ተጽዕኖ ወደ አፈርነት ተቀየረ፡፡ የላይኛው የምድር ቅርፊት (crust) በታች በከርሰ ምድር ካለው ጠንካራና ግል አለት ጋር ተጣምሮ ግዙፍ የአለት ሰፌዶችን ፈጥሯል፣ እነሱም “ስፍሃኖች” ወይም “ቴክቶኖቸ ፕሌትስ” (Tectonic

በሥነ ምድር የዘመን አቆጣጠር ስልትና ቅርሰ ሕይወት (fossils) ዕድሜ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

plates) ይባላሉ፡፡ ከነሱ በታች (ወደ ውስጥ) የሚገኘው የምድር ይዘት አሁንም ቢሆን በእጅጉ የጋለ ጠጣርና ልል አለት ጥርቅም ሲሆን፡ ከዚያም በታች የምድር የውጭ እምብርት (outer core) ሙሉ በሙሉ የቀለጠ ፍስ-አለት ሆኖ ይገኛል፡፡  ከርሰ ምድር ያለው በእጅጉ የጋለው ጠጣር የምድር አካል አንዳንድ ጊዜ ይቀልጥና በተለያዩ አከባቢዎች ወደ ገጸ ምድር ወጥቶ የእሳተ ገሞራ መንስዔ ይሆናል፡፡ ከርሰ ምድር ያለው ግል አለት የተለያዩ የአቶም ዓይነቶች ይገኙበታል፣ በብዛት የሚገኙት “ሲሊኮን” (Silicon)፣ “ኦክሲጂን” (Oxygen)፣ “ማግኔዚየም” (Magnesium)፤ ብረት (Iron)፣ “ካልሲየም” (Calcium)፡ “አሉሚኒየም” (Aluminum)፣ “ሶዲየም”  (Sodium) እና “ፖታሲየም” (Potassium) ናቸው፡፡

በሥነ ምድር የዘመን አቆጣጠር ስልትና ቅርሰ ሕይወት (fossils) ዕድሜ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

በቀድሞ ዘመናት የምድርን ዕድሜ ለመተመን የሳይንስ ምሁራን ተጠቅመውበት የነበረ፣ የቀለጠ አለት ይዘት  የነበራት ምድር ቀስ በቀስ ለመቀዝቀዝና አሁን ባለችበት ሁኔታ ለመድረስ ስንት ዘመን ይፈጅባታል በሚል ስሌት ነበር፡፡ በዚያ ስልት ላይ ተመርኩዘው፣ የሳይንስ ምሁራኑ ዕድሜዋን ከ20 እስከ 400 ሚሊዮን ዓመታት ይሆናል ብለው ገምተው ነበር፡፡ ይህ ግምት ለጊዜው ተቀባይነት ቢያገኝም ወዲያው ብዙ ክርክር ገጠመውና አማራጭ ዘዴዎች ይፈለጉ ጀመር፡፡

የምድራችንን ውስጣዊ እንቅስቃሴ በመጠኑም ቢሆን ለመረዳት አንዲቻል ሒደቶችን ዘርዘር ባለ መንገድ እናውሳ፡፡ በመጀመሪያ ከከርሰ ምድር የወጣ የቀለጠ አለት ገፀ ምድር ላይ ከፈሰሰ በኋላ ቀዝቅዞ የጠጣር አለት መከሰት መንስዔ ሆኗል፡፡ እንዲሁም  በአንድ ወቅት አንድ ግዙፍ አህጉር/የብስ የነበረው ቀስ በቀስ በመሰነጣጠቅና በመለያየት ተከፋፍሎ፣ ብዙ ባህሮች፤ ውቅያኖሶችና አህጉራት/ክፍለ ዓለማት  ተመሥርተዋል፡፡  እስከ ከርሰ ምድር በሚዘልቁ በግዙፍ “ስፍሃኖች” መጋጨትና መገፋፋት፣ የዓለማችን ከፍተኛ የተራራ ሰንሰለቶች ተመሥርተዋል፡፡ እነሱም በአካባቢው አየር ባህርይ/ጠባይ (ዝናብ/ፀሐይ) ይቆጣጠራሉ፣ በተለዋዋጭ የአየር ጠባይ (በዝናብ/ በፀሐይ)  መንስዔ አለቶች ተሰባበረዋል፣ ተሸርሽረዋል፣ እንዲሁም በዝናብ ውሃ ታጥበው ከአካባቢው ተከልተዋል፡፡ በመጨረሻ አብዛኛው ስብርባሪ ኮረት አሸዋና ልም አፈር ውቅያኖስ ደርሶና ዘቅጦ የውቅያኖሶች ወለሎች አካል ሆኖ ወደ ጠጣርነት ተቀይሯል፡፡  የውቅያኖሶች ወለሎች የነበሩ ጠጣር አካል (አለት) በተለያዩ የመሬት አንቅስቃሴዎች የየብስ አካል ሆነዋል (ለምሳሌ አሸዋ ድንጋይ/sandstone እና ቦረንቅ/ Limestone ከውሃ አካል/ውቅያኖሶች ወለል የነበረ አለት ነው)፡፡

ምድራችን የተለያዩ የአለት ድንጋይ ዓይነቶች ይገኙባታል (ሥዕል አንድ)፣ አመጣጣቸውም/ አፈጣጠራቸውም እየቅል  ነው፡፡ የመጆመሪያው ዓይነት አለት “ቡልድ/ግይ ድንጋይ/አለት” (Igneous rock)፣ ሁለተኛው ዓይነት “ደለሌ አለት” (Sedimentary rock)  እና ሦስተኛው ዓይነት “ልውጥ ድንጋይ”  (Metamorphic rock) በመባል ይታወቃሉ፡፡ በመሠረቱ አለት የሚገነባው በሁለት ወይም ከዚያ በቁጥር በሚልቁ ማዕድኖች/ የሚኒራሎች ውህደት ነው፡፡ አንዱና ዋናው የዘመን መተመኛ መረጃ የሚገኘው ከቡልድ አለቶች ጋር በተዘማዱ ኩነቶች ነው፡፡

  1. ከመሬት ላይ የተከላው ግስንግስ ውኃ ውሰጥ ዘቅጦ ደለል (Sediment) ይሆናል፣ ከዚያም በራሱና ከላይ ባለው የውኃ ክብደት ተጨምቆ ተደፍጥጦ ወደ ጠጣርነት/አለትንት ይቀየራል።
  2. እንዲሁም በሌላ ጊዜ ተጨማሪ ግሳንግሰ ወደ ውኃው ገበቶ ቀድሞ ከነበረው ደለል ላይ ያርፋል፣ ይኸም በተራው ተጨፍልቆ ወደ ጠጣርነት ይቀየራል።
  3. ከዚያም ሌላ ተጨማሪ ግሳንግስ ወደ ውኃው ይገባና ቀድሞ ከነበረው ደለል ላይ አርፎ በተራው ወደ ጠጣርነት ይቀየራል፡፡

ወደ ዘመን ስሌቱ እንመለስና ስሌቱ የተመሠረበትን ሳይንሳዊ መሠረት እናውሳ፡፡ ዋና ዋናዎች በሥነ ምድር የዘመን ስሌት ዘዴዎች ሁለት ናቸው፡፡ አንዱ “አንፃራዊ ስሌት” (Relative Dating) ነው፡፡ ይህም አለቶች በተለያየ ጊዜ እንደሚፈጠሩና አንዱ በአንዱ ላይ በቅደም ተከተል እንደሚደራረቡ በመረዳት ነው፡፡ በመስክ እይታ (Observation) ብዙ ድርብርብ አለቶች ባሉበት አንዱ እርከን የተገነባበት አለት ከላዩ ከሚገኘው ሌላ እርከን የተገነባበት አለት የቀደመ አፈጣጠር ስለሚኖረው የረዘመ ዕድሜ አለው ለሚለው መረጃ በቀላሉ (በእይታ) ስለሚገኝ፣ እንፃራዊ ዕድሜን መተመን ይቻላል፡፡ ሆኖም በመረጃው የትኛው አለት የበለጠ ወይም ያነሰ ዕድሜ አለው ከሚል ድምዳሜ ብቻ ላይ ነው ለመድረስ የሚቻለው እንጂ አለቱ የተፈጠረበትን ትክክለኛ ጊዜ ማወቅ አያስችልም፡፡ ሁለተኛው በውስብስብ ሒሳብ ስሌት የሚገኝ መረጃ (Absolute Dating) ነው፡፡

ይኸን ካልን በኋላ የተለያዩ የአለት ዓይነቶች እንዴት እንደተመሠረቱ/እንደተገኙ እናውሳ፡፡ የመጆመሪያው ዓይነት አለት “ቡልድ/ግይ ድንጋይ (Igneous rock) በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ ይህ ዓይነት ድንጋይ ከከርሰ ምድር ውሰጥ ወይም በገፀ-ምድር ላይ በእሳተ ገሞራ መልክ  ፈሶ ወይም ተበትኖ ሲቀዘቅዝ የሚገኘው የአለት ዓይነት ነው፡፡ አንዳንድ የቀለጠ ይዘት የነበረው አለት በውስጡ አየር ስለሚይዝ፣በአጭር ጊዜ ውስጥ ከቀዘቀዘ፣  ክብደቱ በጣም ውስን ነው (ለምሳሌ ኦፊ-ኦሮምኛ/ፑሚስ/ Pumice)፣ ክብደተ-ቀላል ኦፊ በውኃ ላይ ይንሳፈፋል፡፡  አየር ያነሰው የቀለጠ አለት ዝግ ብሎ ከቀዘቀዘ ግን ከባድ ይሆናል (ለምሳሌ ለጠጠርነት የሚፈጨው ጥቁር ድንጋይ ዓይነት)፡፡

ሁለተኛው የአለት ዓይነት፣ “ደለሌ/ዝቅጤ አለት” (Sedimentary rock)፣ የብስ ላይ ካለው የመሬት አካል ማንኛውም አይነት አለት ተሰባብሮና ታጥቦ ወደ ውኃ አካል ውስጥ ገብቶ ሲዘቅጥና ወደ ደለልነት ከዚያም ቀስ በቀስ ወደ አለትነት የሚቀየረው ዓይነት ድንጋይ  ነው (ሥዕል ሁለት)፡፡ ወደ ውኃው አካል ታጥቦ የሚገባው ግባሶ/የተግበሰበሰ (Debris) ስብርባሪ ድንጋይ ሁሉ ውኃው ወለል ላይ በመዝቀጥ ደለል ይመሠርታል፣ ደለሉም አንዱ በአንዱ ላይ ተነባብሮ ከጊዜ ብዛት በራሱና ከላይ ባለው የውኃ ክብደት ተጨፍለቆ/ተጨምቆ ወደ ጠጣርነት/ አለትነት ይቀየራል፣ ለምሳሌ ብዙ ጊዜ ለግንባታ የሚጠረበው አሹዋማው የድንጋይ ዓይነት (አምቦ ድንጋይንም ያካትታል) ይኸን ዓይነት አለት ነው፡፡

በአንድ ወቅት የባህር/ውኃ ወለል አካል ውስጥ የነበረው አለት በተለያዩ የምድረችን ዘገምተኛ እንቅስቃሴዎች፣ ወደ ምድር ገጽ ሲወጣ፣ በጊዜ ብዛት የተነባበረውን አለት የብስ ላይ ማየት ይቻላል፡፡ ስለሆነም  ሥዕል ሁለትን ተመልከትን አንፃራዊ የዕድሜ ግንዛቤ ልናገኝ እንችላለን፡፡ሥዕሉ ላይ  ያለው (ቁጥር 3)፣ ከሱ በላይ ካለው (በኋላ ከገባው)  የላቀ ዕድሜ እንዳለው፣ እንዲሁም ሁለተኛው ደለል (ቁጥር 2) ከሱ በላይ ካለው (ቁጥር 1) ደለል  ዕድሜ እንደሚረዝም ይታወቃል፡፡ በዚህ ላይ ተመሥርቶ አንፃራዊ ዘመን ይታወቃል፣ ትክክለኛው የአለቱ ዕድሜ ግን አይታወቅም፡፡

ሦስተኛው ዓይነት  “ልውጥ ድንጋይ”  የሚመሠረተው ለየት ባለ ሒደት ነው፡፡ ከደለል የተገኘ ድንጋይ (“ደለሌ አለት”) ወይም ከከርሰ ምድር ወጥቶ ከቀዘቀዘ የቀለጠ አካል የተገኘ አለት (“ቡልድ/ግይ ድንጋይ”)፣ በመሬት እንቅስቃሴ መንስዔ ወደ ከርሰ ምድር ዘልቆ ይገባል፡፡ ከርሰ ምድር ውስጥ በከፍተኛ ግፊት (Pressure) እና ሙቀት መንስዔ የማዕድናቱ ብሎም የአለት አይነቶች ነባር ይዞታቸውን ቀይረው አዲስ ይዘትና ቅርፅ ይይዛሉ፡፡ አንዱ ጥሩ ምሳሌ ቦረንቅ/ Limestone አለት፣ በጥልቅ ከርሰ ምድር ውስጥ ሲደርስ በከፍተኛ ሙቀትና ግፊት (Pressure) ወደ እብነ በረድ ተለውጦ ይገኛል፡፡ እነዚህ በከርሰ ምድር ውስጥ የተፈጠሩ ልውጥ አለቶች በተለያዩ የምድራችን ዘገምተኛ እንቅስቃሴዎች፣ እንደገና ወደ ገፀ ምድር ወጥተው ይገኛሉ፡፡  

የቅርሰ/ቅሪተ ሕይወት (fossils) መገኘት ሁኔታ

ቅርሰ/ቅሪተ ሕይወት ያለፉ ዘመናት ማያ መስተዋት ሆነው ያገለግላሉ፡፡ ሕያው/ዘአካላት (ዕፀዋትና እንስሳት) ለሕልፈት በሚዳረጉ ጊዜ ጭቃ፣ ዝቃጭ ደለል ወይም ድንጋይ ውስጥ ከተቀበሩ (ከተዳፈኑ) አካላቸው/አስከሬኑ/ሬሳው “ከበክተ-በል” እንስሳት ወይም የአየር ጠባይ ከሚያስከትለው ውስብስብ ሁኔታ የተዳፈኑት መቃብር ይከላከልላቸዋል፡፡ እንስሳት ሥጋቸው ይበሰብሳል፣ ከረዥም ጊዜ በኋላ በአጽማቸው ላይ በሚከሰተው የአካል መዋቅር ክፍትት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በኬሚካሎች ይተካል/ይሞላል/ይደፈናል፣ ማለት አጽሙ “ሚኒራል-ልውጥ”(permineralization) ሆኖ የቀደመ ቅርፁን እንደያዘ ወደ አለትነት ይቀየራል፡፡ ይኸም ልውጥ አጽም “ቅርሰ-ሕይወት”  ይባላል፡፡ በአፋር ክልል “ሃዳር” በሚባል ስፍራ “የሉሲ/ድንቅነሽ” ቅርሰ/ቅሪተ-ሕይወት የተገኘው በዚህ ሁኔታ ነው፡፡ በዚህ “በቅርሰ-ሕይወት” እውን መሆን ሒደት፣ በሕልፈተ ሕይወት አካሉ/ሬሳው የወደቀበት አካባቢ ይዘት  ከፍተኛ ሚና አለው፣ ያም ይዘት አጽሙ በአየር ቅጥ ባህርያት መከላከልን ያካትታል፡፡

ደለሌ አለት ውስጥ የተገኝ ቅርሰ ሕይወት/ የሕያው ቅሬት (የባለአከርካሪዎች ዝርያ) ሕያው ሲሞቱ “ቅርሰ ሕይወት” ትተው የማለፍ አጋጣሚ በጣም ውስን ነው፣ ከብዙ ሺዎች እንስሳትና ዕፀዋት አስከሬኖች፣ በጣም ጥቂት የሆኑ ናቸው ቅሪቶቻቸው የሚገኙ፡፡ ደረቅ አካባቢዎች (ምድረ በዳ) ለዚህ ኩነት መከሰት አመች ናቸው፡፡ በጣም ዕድሜ ጠገብ የሆኑ ቅሬቶች የተገኙ በአውስትራልያ ምድረ በዳ ውስጥ ሲሆን፣ ብዙ አካባቢ ያልተገኙ የንዑስ አካላት/ሚክሮብ ቅሬቶችም በአውስትራሊያ ተገኝተዋል፡፡

የተለያዩ የሥነ ምድር/ጂዮሎጂ የዘመን አቆጣጠር የሚስተናገድበት የአቶሞች ባህርያት

በመሠረቱ የማንኛውም ንጥረ ነገር/element/ አቶሞች የተገነቡት “በፕሮቶኖች” (Protons)፣ “ኒውትሮኖች”  (Neutrons) እና “በኤሌክተሮኖች” (Electrons) ነው፡፡ የአቶሞች አስኳል (እምብርት) “በፕሮቶኖች” እና “ኒውትሮኖች”  የተገነባ ሲሆን፣ በውጭ አካላቸው ነው “ኤሌክተሮኖች” የሚሾሩት፡፡በአቶሞች ይዘት፣”የፕሮቶኖች” እና “የኒውትሮኖች” ተመሳሳይ ከሆነ፣ አቶሙ የተረጋጋ ይሆናል (አይቀየርም)፣ቁጥራቸው ተመሳሳይ ካልሆነ ግን  (“የፕሮቶኖች” ወይም “የኒውትሮኖች” ቁጥር ሊልቅ ይችላል)፣ አቶሞቹ የተለዋዋጭነት (የመለወጥ) ባህርይ አላቸው፡፡ ለምሳሌ “ሃይድሮጅን” አንድ “ፕሮቶን” እና አንድ “ኒውትሮን”፣ “ሂሊየም” ሁለት “ፕሮቶኖች” እና ሁለት “ኒውትሮኖች”፣ “ሊቲየም” ሦስት “ፕሮቶኖች” እና ሦስት “ኒውተሮኖች”  ነው ያሉዋቸው፡፡ እንዳንድ አቶሞች ያልተመጣጠነ “የፕሮቶኖች” እና “የኒውተሮኖች” ቁጥር አሉዋቸው፡፡ ቁጥሮቻቸው ተመጣጣኝ ያልሆኑት የአንድ አቶም ዓይነቶች “አይሶቶፕስ” (Isotopes) ይባላሉ፡፡ ለምሳሌ ሶድየም (Sodium/Na)  “የፕሮቶኖች” እና ” የኒውተሮኖች” ቁጥር ያልተመጣጠኑ ያሉዋቸው አቶሞች አሉት (ብዙ ዓይነት “አይሶቶፖች” አሉት)፡፡

በተሻለ ደረጃ ግልጥ እንዲሆን ሒደቱን በመጠኑም ቢሆን ዘርዘር እድርገን እናቅርበው፡፡ የተረጋጋ “አይሶቶፕ” የሌለው አቶም ዓይነት “ራዲዮ አክቲቫዊ” (radio active) ይባላል፣ ያም ዓይነት አቶም በሒደት ቀድሞ ያልነበረ ሌላ አቶም በመፍጠርና ጨረር ያለማቋረጥ በመርጨት ባህርዩን በራሱ ይቀይራል። ባህርይ የመቀየር ሑደቱም፣ የአቶም መለወጥ/መበስብስ (radio active decay) ይባላል ፡፡  የአቶሙ ይዘት (መጠን) ከመጀመሪያ ከነበረው  ግማሹ ወደ ሌላ አዲስ አቶም ሲቀየር፣ ሲበሰብስ (ለምሳሌ 100 ግራም የነበረው አንድ ዓይነት “አይሶቶፕ” ባህርዩን ለውጦ፣ የነባሩ ባህርይ ያለው 50 ግራም፣ የተቀየረው አዲስ አቶም ደግሞ 50 ግራም ሲሆን፣ “አይሶቶፖች” ግማሽ ዘመን/ ግማሽ ዕድሜ (Half-life)  ላይ ደረሰ ይባላል፡፡ ያም የመጀመሪያው ግማሽ ዕድሜ በመባል ይታወቃል፡፡ እንደገና ከቀሪው የመጀመሪያውን ዓይነት ባህርይ ያሉዋቸው አቶሞች ግማሹ ሲቀየር፣ ሁለተኛው ግማሽ ዕድሜ ደረሰ ይባላል፣ ሒደቱ ይቀጥላል፡፡ የአንድ አቶም ያልተረጋጋ “አይሶቶፖ” (Isotope)  በ”ራዲዮ አክቲቫዊ” ሒደት ግማሽ መጠኑ/ ግማሽ ዕድሜ (Half-life) ለመድረስ የሚወስድበት ጊዜ (ሰከንዶች/ደቂቃዎች/ ቀናት/ ዓመታት) በፊዚክስ ስሌት በትክክል ይታወቃል፡፡ ይህም ማለት የአንድ አቶም “አይሶቶፖ” (Isotope) በማዕድናት/በአለት ውስጥ ከተፈጠረ ጀምሮ  ማንም የማያቆመው ቆጣሪ ሰዓት በውስጡ ይዞ ይኖራል፡፡

የካርቦን አቶም ሁለት “አይሶቶፖች” አሉት፣(C-12) እና ሲ14 (C-14)፣ እነሱ ለዘመን መተመን ያገለግላሉ፡፡ አንዱ ዓይነት “አይሶቶፕ” (C-12) የተረጋጋ ነው፣ አይቀየርም፡፡ ሌላኛው “አይሶቶፕ” (C-14) ያልተረጋጋ ስለሆነ ባህርዩን ቀይሮ የ(C-12)ን ባህርይ ይወርሳል፡፡ የመቀየሩ ሒደት በሺ ዓመታት ነው የሚተመን፡፡ ለምሳሌ የተወሰነ መጠን ያለው (C-14) ግማሹ ወደ (C-12)  ለመቀየር (ማለት C-14 ወደ C-12 ለመቀየር)  5730 ዓመት ይወሰድበታል፡፡

“ዩራኒየምም” (Uranium/U) የተለያዩ “አይሶቶፖች” “ዩራኒየም 235 (U 235) ” እና “ዩራኒየም 238 (U 238)” የሚባሉ አሉት። የነኝህም የተለያዩ “አይሶቶፖች” ግማሽ ዕድሜ ይለያያል፡፡”ዩራኒየም 235″  ግማሽ ዕድሜ 700 ሚሊዮን ዓመት ሲሆን፣ “የዩራኒየም 238” ግማሽ ዕድሜ ደግሞ 4.5 ቢሊዮን ዓመት ነው፡፡ የካርቦን፣ የፖታሲየም፣ የዩራኒየም፣ እንዲሁም የሌሎች አቶሞች “አይሶቶፖች” ለዘመን ስሌት መተመን ያገለግላሉ፡፡ በአጭር ጊዜ የሚለወጡት፣ ለምሳሌ አንዳንድ “የሶዲየም አይሶቶፖች” ዓይነቶች ከላይ እንደተወሳው በሽርፍራፊ ሰከንድ/ደቂቃ/ሰዓት /ቀናት የሚተመን ግማሽ ዕድሜ ስላላቸው ለጂኦሎጂ/ሥነ ምድር ዘመን ትመና አያገለግሉም፡፡

የጂኦሎጂ/ሥነ ምድር ዘመን መተመኛ ሳይንሳዊ ዘዴዎች

ዋና ዋናዎች የጂዮሎጂ/ሥነ ምድር የዘመን መተለሚያ ስሌቶች፣ ዘዴዎች ሁለት ናቸው፡፡ አንዱ ከታወቀ ስሌት ጋር ማነፃፀር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ቀጥተኛ ግምት መስጠት ነው፡፡ ዘአካላት (ዕፀዋትና እንስሳት) ከምን ጊዜ በፊት ይኖሩ እንደነበረ ለማወቅ በሚሰላበት ጊዜ፣ የዘአካላቱ ቅሬት የተገኘው ከታወቁ ሌሎች ቅሬቶች ጋር አብሮ ከሆነ፣ ተመሳሳይ ዘመን አለው ብሎ በመገመት፣ ተማሳሳይ የዕድሜ ግምት ይሰጠዋል፡፡ ለምሳሌ የዕድሜ ዘመኑ ሊሰላ የተገኘው የአካል ቅሬት አለት ውስጥ ከሆነ፣ እና የአለቱ (rock) ዕድሜ/ ዘመኑ የሚታወቅ ከሆነ፣ ቅሬቱም ተመሳሳይ ዕድሜ (የአለቱ ዕድሜ) እንዳለው ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

ባጭሩ አንዱ ዘዴ ዘመኑ ከታወቀ ከሌላ አካል ጋር አብሮ ለሚገኝ የአካል ቅሬት፣ ያንን የታወቀውን ዕድሜ መስጠት ነው፡፡ “ሃዳር” በሚባል ስፍራ የተገኘችው “የሉሲ/ድንቅነሽ” ቅሪተ-ሕይወት ዕድሜ (3.2 ሚሊዮን ዓመት) የታወቀው በዚህ ሁኔታ ነው፡፡

ሁለተኛውና በከፍተኛ ደረጃ አስተማማኝ የሆነው የስሌት ዘዴ፣ ቡልድ/ግይ አለቶች (igneous rock) ከተገነቡባቸው ማዕድናት ውስጥ በሚገኙ በተወሰኑ አቶሞች ሁኔታ ላይ የተመሠረተ የዘመን መገመቻ ዘዴ ነው፡፡ በቀጥተኛ መንገድ ከላይ ከተብራራው በአቶሞች “ራዲዮ አክቲቫዊ” ባህርይ መቀየር (radio active decay) ተመሥርቶ የዘመን ስሌት ይደረጋል፡፡ የዚህ ስሌት ሁለተኛው መሠረት የቡልድ/ግይ አለት (igneous rock) አፈጣጠር ነው፡፡ እያንዳንዱ ቡልድ/ግይ አለት (igneous rock) የሚፈጠረው በእጅግ ከፍተኛ ሙቀት በከርሰ ምድር ውስጥ ከቀለጠ አለት መሆኑ ከላይ ተብራርቷል፡፡ ቅላጩ አለት በከርሰ ምድር ተከማችቶ እንዳለ ወይም በገፀ ምድር ላይ ፈሶ እንደወጣ በሒደት ሲቀዘቅዝ በውስጡ የሚገኙ የተለያዩ ንጥረ ነገር /elements (“ሲሊኮን” (Silicon)፣ “ኦክሲጂን” (Oxygen)፣ “ማግኔዚየም” (Magnesium)፤ ብረት (Iron)፣ “ካልሲየም” (Calcium)፡ “አሉሚኒየም” (Aluminum)፣ “ሶዲየም”  (Sodium እና “ፖታሲየም” (Potassium) እርስ በርሳቸው በመጣመር ልዩ ልዩ ጠጣር ማዕድናትን መፍጠር ይጀምራሉ፡፡ የተፈጠሩት  አዳዲስ ማዕድናትም ተሰባስበውና ተቀናጅተው ቡልድ/ግይ አለት (igneous rock) ይፈጥራሉ፡፡ ይህም የቡልድ/ግይ አለቱ የውልደት ቀን ተብሎ ይወሰዳል፡፡ በአዳዲስ ማዕድናቱ ውስጥ የሚገኙት የተለያዩ አቶሞች “ራዲዮ አክቲቫዊ” (radio active) “አይሶቶፖች” ወዲያውኑ የዕድሜ ቆጠራ ሥራቸውን ይጀምራሉ፤ ይህ ቆጠራ በምንም ሁኔታ ሳይቌረጥ አሁን ላይ ደርሷል፡፡ እነዚህን “ራዲዮ አክቲቫዊ” (radio active) “አይሶቶፖች” በቡልድ/ግይ አለቶች (igneous rock) ውስጥ ከሚገኙ ማዕድናት ውስጥ በረቀቀ ዘዴ በላቦራቶሪ በመለየትና በመርመር የቀለጠው አለት በምድር ላይ ያሳለፈውን ዕድሜ/ዘመን ለመተመን ተችሏል፡፡

ለዚህ ሒደት ምሳሌነት “የካርቦን” አቶምን ወስደን በዝርዘር እናወሳለን፡፡ በነባራዊ የተፈጥሮ ሒደት፣ “C-12 እና C-14” ከኦክስጅን ጋር ተጣምረው “የካርቦን ዳይኦክሳይድ-CO2” አካል ይሆናሉ፡፡ ከዚያም “ካርቦን ዳይኦክሳይድ” ምድር ላይ ባሉ ዕፀዋት ተምጎ የዕፀዋቱ አካል ይሆናል፡፡ ዕፀዋቱ ሕያው እስከሆኑ ድረስ፣ በውስጣቸው ያለው C-14 በሒደት ባህርዩን ሲቀይር (ሲበሰብስ) ሕዋ ውስጥ ባለው C-14 ይተካል፡፡ ስለሆነም ዕፀዋት በሕይወት እስካሉ ድረስ፣ በውስጣቸው ያለው የC-12 እና የ C-14 አንፃራዊ መጠን (ንፅፅር/ratio) አይዛባም፣ አይቀንስም አይጨምርም፡፡

ዕፀዋት ሲሞቱ (ሕያውነታቸው ሲቋጭ) ባህርይውን የሚቀይረው (decay) C-14 ወደ C-12 ይቀየራል፣ ሆኖም C-14 ከአየር ተወስዶ አይተካም፡፡ ምክንያቱም፣ ዕፀዋት ከሞቱ ወዲያ “ካርቦን ዳይኦክሳይድ” አይምጉም፣ ያም ማለት፤ ቅሬቱ ከአየር “በካርቦን ዳይኦክሳይድ” መልክ ተጨማሪ C-14 አያገኙም፡፡ ሕያው መሆናቸው ሲቋጭ “በካርቦን ዳይኦክሳይድ” መልክ የነበረው C-14 እየበሰበሰ ወደ C-12 ይቀየራል፣ መጠኑም ይቀንሳል፡፡

ከላይ እንደተወሳው እያንዳንዱ የC-14 “አይሶቶፕ” በስብሶ (ተቀይሮ) ሳያልቅ የሚኖርበት ዘመን አለው፡፡ ስሌት የሚካሄድ በግማሽ ዘመን/ ግማሽ ዕድሜ (Half-life) ተብሎ በሚወስደው ጊዜ መጠን ነው፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው ከ5730 ዓመት በኋላ የሚገኘው C-14 (ዕፀዋቱ ሕያው በነበሩበት ጊዜ ከነበረው መጠን) በግማሽ ይቀንሳል፣ ለምሳሌ 100 ግራም ከነበረ ወደ 50 ግራም ዝቅ ይላል፡፡ ይኸም አንደኛው ግማሽ ዕድሜ ይባላል፡፡ ያልተቀየረው 50  ግራም ግማሹ ለመቀየር (ግማሽ ለመሆን /25 ግራም ለመሆን) እንደገና  ሌላ ተጨማሪ 5730 ዘመን ያስፈልጋል፡፡ ይኸም ሁለተኛው ግማሽ ዕድሜ ይባላል፡፡ በዚህን ጊዜ ያልተቀየረው 25 ግራም የተቀየረው 75 ግራም ይሆናል፣ ማለት ከ11,460 ዓመት በኋላ 100 ግራም የነበረው 25 ግራም፣ ወይም ሩብ ይሆናል፡፡ ያልተቀየረው (25 ግራም) ግማሹ ለመቀየር፣ ወደ ሩብ ግማሽ ለመምጣት (12.5 ግራም) ያንኑ ያህል ተጨማሪ ዓመታት ያስፈልጋል፡፡ ይኸም ሦስተኛ ዕድሜ ግማሽ ይባላል፡፡ ሦስተኛ ዕድሜ ግማሽ ለመድረስ በድምሩ 17,190 ዓመት ይወስዳል፡፡

ከላይ እንደተወሳው፣ ሕያው ዕፀዋት ውስጥ የበሰበሰው (የተቀየረው) በአዲስ ስለሚተካ የC-14 እና የ C-12 አንፃራዊ መጠን (ንጥጥር/ratio) አይዛባም፡፡ ግን ዕፀዋት ሕይወት አልባ ሲሆኑ (ሲሞቱ) ምግብን ማምረት ይቋጫል፤ በሙት አካላቸው (በቅሬቱ ውስጥ) ያለው  C-14 መተካቱም አብሮ ይከስማል፡፡ በተቀየረው ምትክ (C-14 ወደ C-12) አዲስ  C-14 አይተካም፤ ስለሆነም ያለው  C-14  ለራዲዮ  አክቲቫዊ ብስብሰት (radio active decay) ተጋልጦ መጠኑ እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ ሌላው ዋናው የስሌት ግብዓት አየር ውስጥ ያለው የC-14 እና የC-12 አንፃራዊ መጠን (ratio) ከዘመን ዘመን አለመቀያየሩ ነው፡፡

ይህንን መሠረታዊ የተፈጥሮ ሕግ በመንተራስ ተመራማሪዎች ከንብርብር አለቶች ውስጥ የዕፀዋት ወይም የእንስሳት ቅሬቱን ናሙና ፈልገው  ይወስዳሉ። ከዚያም በቅሬቱ ውስጥ ያለውን የC-14 መጠን ለመለካት፣ የቅሬቱን ብጣሽ (በትንሹ) ልዩ በሆነ፤ የላቦራቶሪ መሣሪያ (ዕቃ) ውስጥ አቃጥለው፣ ከቃጠሎው በሚገኘው “ካርቦን ዳይኦክሳይድ” ውስጥ፣ C-14 በምን መጠን እንዳለ ይለካሉ፡፡ አሁን በዙሪያው አየር ውስጥ የሚገኘው የC-14 / C-12  ቅንጅት መጠን (ንጥጥር/ratio) ይታወቃል፤ ቅሬቱ በተከሰተበት ጊዜ የነበረው የቅንጅቱ አንፃራዊ መጠንም ተመሳሳይ እንደነበረ ይገመታል (ያንን ሁኔታ ሳይንሳዊ የኬሚካሎች ግንኙነት ነው የሚወስነው)፡፡ ምንም  ይሁን ምን ፣ የያንዳንዳቸው  ድርሻ መጠን አይዛባም (በአየር ውስጥ ይህን ያህል እጅ  C-14፣ ያንን ያህል እጅ C12 የሚለው አይዛባም)፡፡ ስለዚህ በቅሬቱ ውስጥ ያለው የC-14 መጠን ቀንሶ ስለሚገኝ፣ እዚያ መጠን ላይ (የቀነሰ መጠን) ለመድረስ የፈጀውን ጊዜ በሒሳብ ስሌት ለማወቅ ይቻላል፡፡

በዚህ ረገድ በእርግጠኛ የቅሬቶች ዕድሜ ስሌት በካርቦን አቶም ላይ መሥርቶ እስከ 50,000 ዘመን ድረስ ሊሰላ ይችላል፡፡ ቅርሰ ሕይወት ከሆነው የዕፀዋት ቅሪቱ) ውስጥ ያለው C-14፣ ከዕፀዋት ወደ ሳር በል እንስሳት፣ ከዚያም ቅርሰ ሕይወት ከሆነው የዕፀዋት ወደ ሥጋ በል እንስሳት በምግብ ሰንሰለት ውስጥ ተጉዞ ለሁሉም ባለሕያው ይዳረሳል፡፡ ስለሆነም ይህ የዘመን ስሌት ለእንስሳትም ሆነ ለዕፀዋት ቅሬት ያገለግላል፡፡

በጂኦሎጂ/ሥነ ምድር የዘመን አቆጣጠር መሠረት የተገኙ አንኳር አንኳር ሳይንሳዊ ኩነቶች

የዓለማችንን ዕድሜ መተመን ከዕፀዋትም ሆነ ከእንስሳት ቅሬት በተገኘ መረጃ፣ በሕይወት የነበሩበትን ዘመን ለመተመን ተችሏል፡፡ እንዲሁም አለቶችን በማጥናት፣ ከተገነቡባቸው ማዕድናት ውስጥ በሚገኙ አቶሞች ተመሥርቶ የአለቱን ዕድሜ/ዘመን ለመተመን ተችሏል፡፡ “በዩራኚየም” መለወጥ ባህርይ ላይ መሥርተን ምድራችን እውን ሆነችበት ዘመን (4.6 ቢሊዮን አመታት) ለመተመን በቅተናል፡፡ ከላይ እንደተወሳው “ዩራኒየም 235 (U 235) ” ግማሽ ዕድሜ 700 ሚሊዮን ዓመት ሲሆን፣ “ዩራኒየም 238 (U 238) ” ግማሽ ዕድሜ ደግሞ 4.5 ቢሊዮን ዓመት ነው፡፡ ይኸን ዓይነት ባህርይ ስላላቸው ነው “የዩራኒየም አይሶተፖች” ረዥም ዘመናት ለመተምን የሚያገለግሉን፡፡

የሕያው ዝግመተ ለውጥ ዘመን ለመረዳት

በጂኦሎጂ/ሥነ ምድር የዘመን አቆጣጠር መሠረት በተገኘ መረጃ አሁን በሕይወት የሚገኙ ሕያው ዝርያዎች ሁሉ (ዕፀዋትና እንስሳት) ቀደምቶቻቸው፣ አዲስ የውጭ ሁኔታ ሲከሰት፣ በተጎናጸፉት ተፈጥሮያዊ የተለያዩ የበራሂ መሰናዶ የተፈጠረውን አዲስ ሁኔታ ለመቋቋም የሚችሉት በሕይወት እየቀጠሉ፣ አዲሱን ሁኔታ ለመቋቋም የተሳናቸው ግን ለውድምት እየተዳረጉ እንደሆነ ተገንዝበናል፡፡ ቀስ በቀስ በምደር ላይ የሚገኙትም የሕያው ዝርያዎች ይቀያየራሉ፡፡ ይኸም ሂደት 3.2 ቢሊየን ዓማታትን ፈጅቷል፡፡ ይህ መረጃ የተገኘው በጂኦሎጂ/ሥነ ምድር የዘመን አቆጣጠር መሠረት ነው፡፡

የክፍለ ዓለማት/አህጉራት አመሠራረት

ምድራችን በተለያዩ ዘመናት ግዙፍ የተንጣለሉ አህጉራት የነበራት ሲሆን፣ እያንዳንዱ ግዙፍ አህጉር ቀስ በቀስ በመሰነጣጠቅና በስምጥ ሸለቆዎች ተከፋፍሎ በመለያየት ብዙ ባህሮችን፤ ውቅያኖሶችና አህጉራት ተመሥርተዋል፡፡ ይህም የሚሆነው “በስፍሃኖች” መለያየት የተነሳ በባህር ወለል መስፋፋት ሒደት ነው፡፡   አሁን የተከፋፈሉ አህጉራት የተገኙትም በ”አሁገራዊ ሽርተታ” (Continental Drift) እንደሆነ ተደርሶበታል፡፡ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ጀምሮ የሳይንስ ተመራማሪዎች “አሁገራዊ ሽርተታ” (Continental Drift) እንደተከሰተ መገመት ጀምረው ነበር፡፡ ለዚህም ሒደት እንደመረጃነት የተጠቀሙት የአንድ ዓይነት ዝርያ ሕያው አካላት ቅሬት በተለያዩ ክፍለ ዓለማት መገኘታቸው፣ እንዲሁም ተለዋዋጩ የጥንት ዘመን የአየር ቅጥ ባህርይ ጥሎት የሄደው አሻራ እንደ መረጃነት ተጠቅመው ነበር፡፡

ከ250 ሚሊዮን ዓመታት በፊት አሁን ያሉት የዓለም አህጉራት/ክፍሎች አንድ ግዙፍ “ፓንጌያ” (Pangaea) በመባል የሚታወቅ ዓለም ነበር፡፡ ያም ግዙፍ የተንጣለለ የመሬት አካል፣ ቀስ በቀስ መከፋፈል ጀመረ፣ ከዚያም የተከፋፈሉት በየፊናቸው መራራቅ ጀመሩ፡፡ የመገነጣጠሉ/የመለያየቱ መንስዔ ከመሬት ከላይኛው ሽፋን በታች የሚገኙት “በስፍሃኖች” (ግዙፍ የአለት ሰፌዶች) “ቴክቶኒክ ፐሌቶች” (Tectonic plates) በመባል የሚታወቁት እየተንቀሳቀሱ፣ ብሎም እየተራራቁ በመሄዳቸው ነው፡፡ ለዘህም እንደ ማስረጃነት የሚያገለግሉ ተመሳሳይ ዕድሜ ያሉዋቸው የአለት ዓይነቶች በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ባሀር ጠረፎች ላይ መገኘታቸው ነው፡፡

እንዲሁም የሕያው ቅሪቶችም ለዚህ ኩነት እንደማስረጃ ሆነው ያገለግላሉ፡፡ “የሊስትሮሳውረስ” (Lystrosaurus)  የሚባሉ “የገበሎ እስተኔ” ዝርያዎች (Reptiles) ቅሬት በአንታርክቲካ (Antarctica)፣ በእስያ እና በአፍሪካ ደቡብ አካባቢ ተገኝቷል፡፡ ሌሎችም የእንስሳት ቅሪቶች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡  ቅሬቶቻቸው የተገኘው እንስሳት ሕያው በነበሩበት ዘመን በምንም መንገድ ባህርና ውቅያኖስ አቋርጠው ከአንድ ክፍለ ዓለም ወደ ሌላ ክፍለ ዓለም ዘልቀው ሊሄዱ የሚችሉበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ይኸም እነኝህ አሁን የተለያዩ ክፍለ ዓለማት በአንድ ዘመን የተገናኙ እንደነበሩ ያስረዳል፡፡ እንዲሁም በአለቶች ዓይነትና በሕያው ቅሬቶች ተመሥርተን ባገኘነው መረጃ፣ ዓለማችን ቀድሞ ከነበረችበት ይዘት በጣም የተቀየረች መሆኗንም ደርሰንበታል፡፡

መደምደሚያ

የሳይንስ ዕውቀት ቋት ሙሊቱ ከፍ እያለ በሄደ መጠን፣ ስለ አካባቢያችን ያለን ግንዛቤ በዚያ ዕውቀት ላይ ተመሥርቶ እየዳበረ ይሄዳል፡፡ ይህንም የመዳበር ሒደት እንደጎህ ልንመስለው እንችላለን፡፡ ጎህ ገና ከመቅደዱ በፊት የምናየው አካል ሁሉ ጨለማ የተላበሰ ነው፡፡ ለምሳሌ ዛፍን ብንወስድ፣ ዛፍ መኖሩን  እንዲሁም ግርድፍ ቅርፁን እንረዳለን፡፡ ጎህ ቀስ በቀስ እየቀደደ ሲሄድ ዛፉ ብዙ ቅርንጫፎች እንዳሉት፣ እንዲሁም ትላልቅ ቅርንጫፎችም ትናንሽ ቅርንጫፎች እንዳሉዋቸው፣ ከዚያም የአካባቢው ብርሃን ሲጨመር፣ ትላልቅ ቅርንጫፎችም ከነሱ የሚያናንሱ ቅርንጫፎች እንዳሉዋቸው ለመረዳት እንችላለን፡፡ ፀሐይ ወጥታ አካባቢው ሁሉ ብርሃን ሲሆን፣ ቀደም ብለን ለማየት ያልቻለውን የዛፉን የተለያዩ አካላት የተለያዩ ቀለማት እንደተጎናፀፉ ለመረዳት እንበቃለን፡፡ የሳይንስም የዕቀውቀት ቋት መዳበር ይኸንኑ ዓይነት ግንዛቤን ነው የሚያበረክትልን፡፡

በጂኦሎጂ/ሥነ ምድር ስሌት የሕያው የዘር ሐረግ መዋቅር፣ አመሠራረት፣ በየትኛው የጂኦሎጂ/ሥነ ምድር ዘመን የትኞች ዕፀዋት/እንስሳት ሕያው እንደነበሩ ለመገንዘብ ችለናል፡፡ እንዲሁም “በዝግመተ-ለውጥ” ላይ መሥርተን፣ የሕያውን ዝምድና ለመረዳት በቅተናል፡፡ የሰው ልጅ አመጣጡን በመገንዘብ፣ ከሌሎች እንስሳት ጋር ያለውን የሩቅ ዝምድና፣ ከመሰሎቹ ከ”ሰብ-አስተኔ” (Primates) አባላት ጋር ከ55 ሚሊዮን ዓመት በፊት የዝምድና ሐረግ ይጋሩ እንደነበረ፣ ዝምድናቸው ቀረብ ካለው ቀደምቶች፣ “ቅድመ-ሰብ” (Hominids)፣ ዝምድና ይጋራ የነበረው  ከ6-7 ሚሊዮን ዓመታት በፊት እንደነበረ ለመረዳት ችለናል፡፡

ምንም የመሬት/ምድር ገጽታ የተረጋጋ መስሎ ቢታየንም፣ በቢሊዮን ዓመታት በተከናወኑ ሒደቶች፣ ከመጀመሪያ ይዘቱ በጣም ተቀይሯል፡፡ ዓለም በጠቅላላ አንድ የተገናኘ፣ የተንጣለለ ምድር እንደነበረ፣ ያም አካል በመገነጣጠል ክፍለ ዓለማት እንደተመሠረቱ  ለመረዳት ችለናል፡፡ ይህ ሒደት በጣም ዝግምተኛ በመሆኑ ግልጥ ሆኖ አይታየንም እንጂ ዓለማችን አሁንም በመቀየር ላይ ትገኛለች፣ ይኸም የተፈጥሮ ሒደቱ አይገታም፡፡

በዘመናችንም በአፋር አካባቢ ከቀይ ባህር ጀምሮ፣ መሬት እየተሰነጠቀና እየተከፈተ ነው፡፡ ታላቁ “የአፍሪካ ሪፍት/ስምጥ ሽለቆ”  በመባል የሚታወቀው ረባዳ የመሬት ክፍል በሁለት “ስፍሃኖች” (ሰፋፊ “የአለት ሰፌዶች”/ (የኑብያና የሶማሌ “ቴክቶኒክ  ፕሌቶች”) የመለያየት እንቅስቃሴ መንስዔ፣ በዘመናችንም አፍሪካን በሁለት በመክፈል በጣም ዝግምተኛ ሐደት ላይ ይገኛል፡፡ የመለያየቱም መጠን በዓመት ከ6 እስከ 7 “ሚሊሜትር” ገደማ ስለሆነ፣ የጂኦሎጂ/ሥነ ምድር ተመራማሪዎች በዚህ ሒደት በ 5 እስከ 10 ሚሊዮን ዓመታት ወስጥ፣ የአፍሪካ ክፍለ ዓለም/አህጉር ለሁለት  ይከፈላል ብለው ተንብየዋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዎቹን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡