ዝንቅ ምን ያለው ነው! ሳልሞት ይፈታኛል!

አንባቢ

ቀን: September 15, 2024

ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ባል ሳይወጣላቸው ነው የሞቱት ይባላል፡፡ በመጀመሪያ ገና በጨቅላነታቸው በዕድሜ አቻቸው ያልሆኑ ራስ አርአያ ዮሐንስን (የአፄ ዮሐንስ ልጅ) እንዲያገቡ ተደረገ፣ ራስ አርአያ ከሞቱ በኋላ ደግሞ የሰሜኑን ኢትዮጵያ ፖለቲካ ለመጠበቅ ሲባል ለራስ ጉግሣ ተዳሩ፡፡

ራስ ጉግሣ ብዙውን የሌሊት ጊዜያቸውን በጸሎት ያሳልፉት ነበር፤ ንግሥት ዘውዲቱ ለአቅመ ሄዋን ደርሰው የወንድ ክንድ ተንተርሰው ለመተኛት በሚፈልጉበት አፍላ የወጣትንት ዕድሜያቸው ሽማግሌው ራስ ጉግሣ ከሚስታቸው ይልቅ ዳዊታቸውን ያስቀድሙ ነበር፡፡

አንድ ቀን ንግሥቲቱ ባለቤታቸውን ከአሁን አሁን ጸሎታቸውን ጨርሰው ከጎኔ ጋደም ይላሉ ብለው ቢጠበቁ ቢጠብቁ ጸሎታቸውን አልጨርስ አሉ፡፡ በዚህን ጊዜ ዳዊት ይደግሙ ወደ ነበሩት ባለቸው እያፈጠጡ ‹‹ምን ያለው ነው ይህ ደግሞ ሳልሞት ይፈታኛል›› አሉዋቸው ይባላል፡፡