September 15, 2024

ርዕሰ አንቀጽ

በአሁኑ ጊዜ ለሕዝብና ለአገር ፋይዳ ከሌላቸው ድርጊቶች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱት ዓይን ያወጣ ሌብነትና ሙስና፣ ጽንፈኛ ብሔርተኝነት፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን አለማክበር፣ የግልጽነትና የተጠያቂነት መርህ መጣስ፣ ለሕግ የበላይነት ፀር መሆን፣ ጥቅም የሌላቸው አሰልቺ ነገሮች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ማድረግና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ በአንድ በኩል ለአገር ልማት ይበጃሉ የሚባሉ በርካታ ዕቅዶች ተነድፈው ወደ ሥራ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ልማቱ አካታችነት የሌለውና የጥቂቶች መጠቃቀሚያ ነው ተብሎ ትችት ይሰነዘራል፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች እየተጀመረ ነው በሚባለው የኮሪደር ልማት የአገርን ገጽታ የሚለውጡ ተግባራት ይከናወናሉ ሲባል፣ ልማቱ ነዋሪዎችን ወደ ዳር እየገፋ ከተማ ማሳመር ነው የተያዘው የሚባል ሙግት አለ፡፡ በሌሎች መስኮችም ከአካታችነት ጋር የሚያያዙ በርካታ ጥያቄዎች ስላሉ፣ የሚመለከተው የመንግሥት አካል በቂ ማብራሪያ መስጠት ይኖርበታል፡፡

ሙስና አገሪቱን እንደ ነቀዝ እየበላ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ጊዜ ቢነገርም ትኩረት አላገኘም፡፡ ከሕዝብ በተሰበሰበ ግብር ወጪያቸው የሚሸፈንላቸው ብዙዎቹ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ የተሰገሰጉ ግለሰቦች፣ ተገልጋዮችን በጉቦ ካልሆነ በስተቀር ለማስተናገድ ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተቋማቱን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማዘመን አገልግሎቶችን ከሰው ንክኪ ማድረግ ይፋ በተደረገባት አዲስ አበባ፣ ከቢሮ ውጪ በደላሎች አማካይነት በመደራደር ወይም ‹ሲስተም የለም› በሚል ሰበብ ተገልጋዮችን በጉቦ ማጨናነቅ ጉዳይ በከንቲባዋ ጭምር በምሬት የተነገረለት ነው፡፡ በመንግሥት የተበጀተ ገንዘብና ንብረት በኔትወርክ ተቧድኖ ከመዝረፍ በተጨማሪ፣ ሕዝብ ለማገልገል የተሰጠን ሥልጣን ለግል ጥቅም ማዋል የተለመደ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ የመንግሥት ግዥ አፈጻጸም ሕግን የሚቃረኑ ተግባራት ከመብዛታቸውም በላይ፣ በየተቋማቱ አለቃና ምንዝር እየተመሳጠሩ ሌብነትና ሙስናን እያደሩት ጠያቂ መጥፋቱ አስተዛዛቢ ነው፡፡

ዜጎች በተፈጥሮም ሆነ በሕግ የተረጋገጡላቸው መብቶች በጠራራ ፀሐይ ሲጣሱ መመልከት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ አንድ ዜጋ ለልማት ሲባል ከመኖሪያው ወይም ከሥራ ቦታው ሲነሳ ሰብዓዊ ክብሩ መጠበቅ አለበት፡፡ በድንገተኛ ውሳኔዎች በሁለትና በሦስት ቀናት ማስጠንቀቂያ አፍራሽ ግብረ ኃይል እየላኩ ዜጎችን ማሳቀቅ፣ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት አኳያ ሲታይ በሕግ የሚያስጠይቅ ወንጀል መሆን ነበረበት፡፡ የቀበሌ ቤቶች ተከራይ የነበሩም ሆኑ ባለንብረቶች ከነበሩበት አካባቢ ሲነሱ፣ በፍፁም ፈቃደኝነት ተረጋግተው ወደ አዲሱ አካባቢያቸው እንዲሄዱ መንግሥት ከፍተኛ ዕገዛ ማድረግ አለበት፡፡ ልማቱንም ሆነ ሒደቱን አስመልክቶ ድጋፍ ብቻ ከመፈለግ፣ ለወደፊቱ ሥራ የሚጠቅሙ ገንቢ ትችቶችንና ምክረ ሐሳቦችን ማዳመጥ ተገቢ ነው፡፡ ‹ውጤታማ መሆን ከፈለግክ የደጋፊዎችህን ብቻ ሳይሆን የነቃፊዎችህንም ሐሳብ ስማ› የሚባው ያለ ምክንያት እንደሆነ መገንዘብ ይገባል፡፡

በኢትዮጵያውያን መካከል ለዘመናት የዘለቁ አኩሪ ማኅበራዊ መስተጋብሮች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ መተሳሰብና መረዳዳት ይጠቀሳል፡፡ ብሔር፣ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ቋንቋና ሌሎች ልዩነቶች መኖራቸው እስከማይታወቅ ድረስ በጋብቻ ጭምር ተሳስረውና ተዋልደው የኖሩ ኢትዮጵያውያን ውስጥ እየሰረገ ያለው ጽንፈኝነት ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በተለይ በፖለቲካ ልሂቃንና አጃቢዎቻቸው አማካይነት በየማኅበረሰቡ ውስጥ የሚነሰነሰው መርዝ፣ በተለያዩ መለስተኛ ግጭቶችና ጥቃቶች ካደረሰው ጥፋት ባሻገር አውዳሚ ጦርነቶችን እየገባዘ ነው፡፡ ከሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት በተወጣ ማግሥት በአማራ ክልል በመካሄድ ላይ ያለው ውጊያ፣ በኦሮሚያ ክልል ከዕገታ ጋር ጭምር የተሸራረበው ውጊያና በሌሎች አካባቢዎች የሚስተዋሉ የሰላም መደፍረሶች አገርን ለማፍረስ ጫፍ እያደረሱ ነው፡፡ ጽንፈኞች በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ጭምር የሚጭሯቸው እሳቶች፣ በፍቅርና በሰላም ይኖሩ የነበሩ ማኅበረሰቦችን ከማጥፋታቸው በፊት መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡

በመንግሥት ተቋማትም ሆነ በተለያዩ የሥራ መስኮች ለግልጽነት፣ ለተጠያቂነትና ለኃላፊነት መርህ ቦታ ባለመሰጠቱ ሕገወጥነት እየተንሰራፋ ነው፡፡ ለሕግና ለሥርዓት መጥፋት ምክንያት በመሆኑም በየቦታው ግጭት የሚጭሩ በዝተዋል፡፡ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆነው ሥልጣናቸውን በሕግ ላልተሰጣቸው ድርጊት የሚጠቀሙበት ብዙ ናቸው፡፡ በኮንትሮባንድ ንግድ ውስጥ ዋነኛ ተሳታፊ መሆን፣ የግብይት ሥርዓቱን ጤና ማሳጣትና ሥርዓተ አልበኝነት ማስፈን፣ ግብር በሥርዓትና በሚፈለገው መጠን እንዳይሰበሰብ ማድረግ፣ ሕገወጥ የመሬት ወረራን ማባባስ፣ ለግብር ከፋዮች ተገቢውን አገልግሎት አለመስጠት፣ የመንግሥት የሥራ ሰዓትን ለግል ጥቅም ማዋልና በመሳሰሉት ብልሹ አሠራሮች የተዘፈቁ አገር እየጎዱ ናቸው፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ሲጠፋ ግለሰቦች እንደፈለጋቸው እየፈነጩ ብዙኃኑ ግን ጉስቁልናቸው ይቀጥላል፡፡ ይህ በሽታ ከዚህ ቀደም በስፋት የሚስተዋል የነበረ ሲሆን፣ አሁንም በስፋት መቀጠሉ ከማሳዘን አልፎ የሚያስቆጭ የአገር መከራ ነው፡፡

መንግሥት ለአገር ልማትና ዕድገት የሚጠቅሙ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ይደመጣል፡፡ የሚያከናውናቸው ሥራዎች ፍሬ አፍርተው በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት የሚኖራቸው ግን፣ ውስጡ ለዓመታት የተከማቹ ብልሹ አሠራሮችን ሲያስወግድ ነው፡፡ ለምሳሌ በኮሪደር ልማቱ ከሙስና የፀዳ ሥራ ለማከናወን ቆርጦ መነሳቱን ከማስታወቁ በፊት፣ በፕሮጀክቶቹ ዙሪያ የተኮለኮሉ በጓሮ በር የሚደራደሩ ሌቦችን ቆርጦ መጣሉን ማረጋገጥ አለበት፡፡ አሉኝ የሚላቸውን የቴክኖሎጂ ግብዓቶች ይዞ ማኅበረሰቡ ውስጥ በቁርጠኝነት መግባት ሲችል፣ እነማን ምን እያደረጉ እንደሆነ ከእነ ማስረጃው ያገኘዋል፡፡ በተቋማቱ ውስጥ የመሸጉ ሌቦችንም እንዲሁ፡፡ ለሕዝብና ለአገር ምንም ጥቅም የሌላቸው ነገር ግን የጥቂቶችን ፍላጎትና ጥቅም የሚያሟሉ ብልሹ አሠራሮች በቁርጠኝነት ካልተዘመተባቸው፣ ለሚዲያ ፍጆታ የሚውሉ የፕሮፓጋንዳ ጋጋታዎች እውነታውን አይሸፍኑትም፡፡ ለሕዝብና ለአገር ፋይዳ የሌላቸው ድርጊቶች ልጓም ያስፈልጋቸዋል!