እኔ የምለዉ ለብሔራዊ ፍላጎትና ጥቅም ሲባል ማዕቀቡ ይቀጥላል!!

አንባቢ

ቀን: September 15, 2024

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር)

የተባበሩት አሜሪካ ግዛቶች (በእንግሊዘኛ ምህፃረ ቃል ዩኤስኤ) ከዚህ በኋላ አሜሪካ እያልኩ የምገልጻት አገር ፕሬዚዳንት ቀደም ሲል የአሜሪካ መንግሥት ጥሎት የነበረን፣ በቅርቡም የተጣለበት የጊዜ ገደብ ያበቃ የነበረን፣ የኢኮኖሚ ጉዳዮችን፣ የባለሥልጣናት ጉዞን፣ ወዘተ የሚያካትት ማዕቀብ በኢትዮጵያ ላይ ሊያስቀጥሉ መፈረማቸውን የብዙኃን መገናኛ ሚዲያዎች (የኅትመትና የኤሌክትሮኒክስ) አሳውቀውናል፡፡ ይህን የሚያደርጉትም በኢትዮጵያ ውስጥ ያላቸውን ብሔራዊ ፍላጎትና ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ይህ የትኛውን ብሔራዊ ፍለጎትና ጥቅም? የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ ወይስ በሌላ ዓውድ ውስጥ ያላቸውን ፍላጎትና ጥቅም ለማስጠበቅ? የሚሉትንና ተዛማጅ ጥያቄዎችን እንዳነሳ ገፋፍቶኛል፡፡ በተደጋጋሚ በምጽፋቸው ጽሑፎችና በተለያዩ መድረኮች ለሚቀርብልኝ ቃለ መጠይቅ በምሰጠው ማብራሪያ ላይ እንደምገልጸው፣ የአንድ አገር ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች በአምስት ዓውዶች ተከፋፍለው ሊጠኑ፣ ሊመረምሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህም ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ዓውዶች ናቸው፡፡

የአሜሪካ መንግሥት ጥሎት የነበረው ማዕቀብ ከሚያካትታቸው ጉዳዮች መሀል አንዱ በእንግሊዝኛ ምህጻረ ቃለ አጎዋ እየተባ የሚጠቀሰው African Growth and Opportunity Act (AGOA) ድንጋጌ ነው፡፡ ከአጎዋ ጋር የተያያዘው የማዕቀቡ ይዘት የሚያጠነጥነው ኢትዮጵያን ከአሜሪካ ገበያ የቀረጥ ነፃ ንግድ ተጠቃሚነት ማገድ ላይ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አሜሪካ የጣለችው ማዕቀብ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ላይ የጉዞ ዕገዳ ማድረግ፣ ወዘተ. አካቷል፡፡

አጎዋ በኢኮኖሚ ዓውድ ውስጥ የሚካተት ድንጋጌ ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ ልንጠቀምበት የሚገባ የመፈብረክና የንግድ ዕድል ነው፣ ከዚህ ድንጋጌ ተጠቃሚነት ከሰብ ሳህራ አፍሪካ ካሉ አገሮች ውስጥ አለመካተታችን በግብርና፣ ኢንዱስትሪውና ንግድ ዘርፉ ውስጥ ጉዳት ያስከትልብናል፣ የሚሉ አንዳንድ አገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን፣ በርካታ የዳያስፖራው ኢትዮጵያዊ አካል የሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአሜሪካ ዜጎችና መሰሎቻቸው እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ለእነዚህ መሰሎች በእኔ በኩል፣ ጊዜአዊ መጎርበጥ ቢያስከትልም፣ የሚከተለውን አቋሜን በድጋሚ ማሳወቅ እሻለሁ፡፡ 

ለዘላቂ የኢኮኖሚ ልማትና ዕድገት ትልማችን፣ በዜጎች የሚመራና የሚጎለብት ኢኮኖሚ ይኖረን ዘንድ፣ ኢትዮጵያ በአጎዋ ውስጥ አለመታቀፏ ከጉዳቱ ይልቅ ጠቀሜታው ይበልጣል የሚል አቋም አለኝ፡፡ ይህን አቋሜን ማሳወቅ ከጀመርኩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በአንድ ወቅት አሜሪካኖቹ የአጎዋን አሉታዊ ይዘት ከእነ ግብስባሴው፣ እንዲሁም ይህን የሚያራምዱ የሁለትዮሽ መንግሥታዊ ሆነ  የግል ተቋማቶቻቸውና ኤክስፐርቶቻቸው ጋር ተጠራርገው ከአገራችን ቢወጡልን፣ እኛ ኢትጵያውያን  ዘለቄታ ባለው የግብርና፣ ኢንዱስትሪና ንግድ ሥራ አወቃቀርና አካሄድ ላይ ውጤታማ የመሆን ዕድላችን ሰፊ ነው በማለት ያለኝን ሙያዊ ምልከታ አሳውቄ ማብራሪያ ሰጥቻለሁ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ከነበረኝ ቃለ መጠይቅ ተወስዶ እሑድ ጥቅምት 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ‹‹አሜሪካኖች አጎዋን የሚገለገሉበት እንደ ንግድ ዕድል ሳይሆን እንደ ፖለቲካ መሣሪያ ነው›› በሚል ርዕስ በቆይታ ዓምድ የወጣውን ጽሑፍ አንባቢያን ደግመው ቢያነቡት ስል እመክራለሁ፡፡ በዚያን ወቅት ተሰንደው ከሚገኙ መረጃ ምንጮች ላይ ተመሥርቼ፣ አጎዋ እንኳ ለኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካ በአጠቃላይ፣ የድፍድፍ ነዳጅ ዘይት መበዝበዣነት የዋለ የአሜሪካኖች ሥልታዊ መሣሪያ ነው ብዬ ገልጬአለሁ፡፡ በአጎዋ ድንጋጌ መሠረት በወቅቱ ከአፍሪካ አገሮች ከቀረጥ ነፃ ወደ 6,000 (ስድስት ሺሕ) ጥሬ ዕቃዎችና ሸቀጦች ወደ አሜሪካ ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ተፈቀደ ቢባልም፣ በ2014 ዓ.ም. ቃለ መጠይቁን ሳደርግ በነበረኝ መረጃ አሜሪካኖቹ ወደ አገራቸው ካስገቡት ጠቅላላ ጥሬ ዕቃና ሸቀጥ መሀል ከዘጠና በመቶ (90) በላይ ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ነው፡፡

እዚህ ጋ ለአንባብያን ሁለት ነገሮችን  ላሳውቅ

አንደኛ አሜሪካኖቹ ማዕቀብ መጣላቸውም ሆነ ማዕቀቡን ማስቀጠላቸው፣ ይህን የሚያደርጉትም የአሜሪካን ብሔራዊ ፍላጎትና ጥቅም ለማስከበር ሲሉ እንደሆነ መግለጻቸው፣ የሚያስወቅሳቸውና በእነሱም ላይ ጥላቻ የሚጭር መሆን የለበትም፡፡ እንዲያውም የሚያደርጉትን በማወቃቸውና የአገራቸውን ብሔራዊ ፍላጎትና ጥቅም ለማስከበር ቆርጠው በመሥራታቸው እኛ እንደ ትምህርት ወስደን፣ በማናቸውም ነገር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ፍላጎትና ጥቅም ከማናቸውም አገር በላይ አስቀድመን፣ ሉዓላዊነታችንን አስከብረን ለመገኘት መሥራት አለብን፡፡ ለዚህም በሁሉም አቅጣጫ አገር ሰላም ሆና፣ ዜጎች በማናቸውም ሥፍራ በነፃነት ተንቀሳቅሰው፣ በዓላቸው ዕውቀት፣ ጥሪትና የሥራ ፈጠራ ችሎታ የአገሪቱን የተፈጥሮ ሀብትና ፀጋ ሁሉ በቅድሚያ ለኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያ ልማትና ዕድገት እንዲያውሉ ማድረግ ይገባል፡፡

ሁለተኛ፣ እንደ አሜሪካ ከመሳሰሉት አገሮች ጋር በብሔራዊ ፍላጎትና ጥቅም መጋጨትና መገፋፋት ሳይሆን በመደጋገፍ፣ አንዱ ሌላውን ለመበዝበዝ ወይም ተገቢነት የሌለው ተጠቃሚ ለመሆን ሳይሆን፣ አንዱ የሌላውን ክፍተት ለመሙላት በሚል መርህ ላይ የተመሠረተ የኢኮኖሚ፣ በተለይም የንግድ ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲያራምድ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ተገቢ ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን አጎዋ መሰል ድንጋጌ ከኢኮኖሚ ይልቅ የፖለቲካ መሣሪያ ሲሆን፣ ነገሮች ሁሉ በተገቢው አቅጣጫ እንዲጓዙ ለማድረግ፣ ጥንቃቄ ያለበት ዕርምጃ አይወሰድ ማለት አይደለም፡፡

የአጎዋን መሰል ድንጋጌዎችን አሉታዊ ይዘት በፅኑ መታገል ተገቢ ነው፡፡ ድንጋጌዎች ይመጣሉ ይሄዳሉ፡፡ አጎዋ እ.ኤ.አ. በ2000 አካባቢ ተጀመረ፣ በ2015 ሊያበቃ ሲባል በአሜሪካ ውስጥም ሆነ ከአሜሪካ ውጭ ባሉ ባለድርሻ አካለት በተደረጉ መጯጯሆች እሰከ 2025 እንዲራዘም ተደረገ፡፡ አጎዋ በሌላ ይዘት ይመጣ እንደሆን እንጂ፣ አሁን ባለው ቅርፅና ይዘት እ.ኤ.አ. በ2025 ጉዞው ያበቃለታል፡፡ በእኔ ምልከታና ታዝቦት፣ እሰከ ዛሬ ባለው ጉዞው የእኛን አገር የመፈብረክ ኢንዱስትሪና የንግድ እንቅስቃሴ፣ ላለፉት ሃያ ዓመታት ዘለቄታዊነት ያለው በአገር ባለሀብቶች የሚመራ የልማትና ዕድገት አቅጣጫ እንዳይዝ አድርጓል የሚል መላምታዊ የጥናት መነሻ ድምዳሜ አለኝ፡፡ 

ኢትዮጵያ ከዘለቄታዊ የኢኮኖሚ ልማትና ዕድገቷ የምትደናቀፈውና ሁሌም ወደ ኋላ የምትጎተተው አጎዋን በመሳሰሉ የምዕራቡ የአደጉ አገሮች ኢምፔሪያል መንግሥታት የመጎተቻና የማደናቀፊያ ድንጋጌዎች ላይ በተቀረፁ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች፣ በእነዚህም መሠረት በተቀረፁ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ስትጠመድ ነው፡፡ በዚህ መሰሉ ወጥመድ ውስጥ ወድቃ የአደጉ በተለይ የምዕረቡ ኢምፔሪያሊስት አገሮች ፍላጎትና ጥቅም አስከባሪ በሆኑት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ በተለይ የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ፣ በመሳሰሉት መሾር ስትጅምርና ስትሾርም ነው፡፡

ለመሆኑ የአሜሪካው መንግሥት ማዕቀቡ እንዲቀጥል የምንሻው በኢትዮጵያና በቀጣናው ያለው ብሔራዊ ፍላጎታችንና ጥቅማችን ሥጋት ላይ ስለወደቀብን ነው ሲል ምን ማለቱ ነው? ይህን በዕውንና በዝርዝር ለመረዳት የአሜሪካውን የስለላ ድርጅት ካቢኔት ሰብሮ መግባትን ይሻል፡፡ ይህን ማድረግ ደግሞ ግመልን በመርፌ ቀዳዳ ለማሾለክ የሚደረግ ጥረት ስለሚሆን፣ ከዚህ መለስ በአጭሩ ስለጉዳዩ ጭብጥ ይዘት መንደርደሪያ ይሆናል ብዬ ከምገምተው ከአንድ ጥቅል ነገር ልነሳና በጽሑፌ ልዝለቅበት፡፡ ይህም አሜሪካኖች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያደርጉት ነገር ሁሉ፣ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ፍለጎትና ጥቅም መሟላት ታስቦ ሳይሆን፣ ለእነሱ ዜጎች፣ ለኢምፔሪያሊስቶቹ ድንበር ዘለል ኩባንያዎቻቸውና መንግሥታዊ ተቋማት ፍለጎትና ጥቅም መሟላት ሲሉ እንደሆነ ነው የሚል ዕሳቤዬ ነው፡፡ በአሜሪካኖች ዴሞክራሲ፣ ሰበዓዊ መብት፣ ፍትሐዊነት፣ ወዘተ የሚባሉትና አብረዋቸው የሚናፈሱት ጉዳዮች ሁሉ የሚደሰኮሩት በዋነኛነት የእነሱን መንግሥት፣ ሕዝብና ኩባንያዎች ፍላጎትና ጥቅም ለማስጠበቅ ነው፡፡

የአሜሪካኖች ብሔራዊ ፍላጎትና ጥቅም የትኛው ዓውድ ላይ ያተኮረ ነው? ብዬ ስጠይቅ ለእኔ ቀድሞና ጎልቶ የሚታየኝ የኢኮኖሚ ዓውድና እነሱም በዚህ ዓውድ ውስጥ አለን የሚሉት ፍለጎትና ጥቅም ነው፡፡ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ዓውዶች ያላቸው ሥፍራ በጣም አናሳ ሲሆን፣ በጥቂቱም ቢሆን ግን ከአካባቢው ጂኦ ፖለቲካ ጋር የተያያዘ ፖለቲካዊ ፍለጎትና ጥቅም ይኖራቸዋል የሚል ግምት ሊኖር ይችላል፡፡ የጂኦ ፖለቲካ ፍላጎትና ጥቅማቸውም ቢሆን  ሥረ መሠረቱ ሲታይ አኅጉራዊ ከሆነው የኢምፔሪሊስቶቻቸውና መንግሥታቸው የኢኮኖሚ ፍላጎትና ጥቅም ጋር የተቆራኘ ሆኖ ይገኛል፡፡

በአፍሪካ አኅጉር ውስጥ የአሜሪካኖች ብሔራዊ ፍላጎትና ጥቅም አፍሪካን የርካሽ ጥሬ ዕቃ ምንጫቸውና የርካሽ ሸቀጦቻቸው ማራገፊያ ከማድረግ  የተያያዘ ፍለጎትና ተጠቃሚነት ጋር የተቆራኘ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ስለእነዚህ ጉዳዮች ከዚህ ቀደም በጻፍኳቸው መጽሐፍትና ሌሎች የኅትመት ውጤቶች ውስጥ በስፋት፣ በመረጃዎችና ማስረጃዎች አስደግፌ፣ ማብራሪያ አቅርቤያለሁ፡፡ በተለይ እነዚህን መሰል የኢምፔሪያል ኃይሎች የፍለጎትና ጥቅም የማስከበር እንቅስቃሴ ጋር በማዛመድ የሌሎችን አገሮች ቀደምት ታሪካዊ ዳራ አስቃኝቼ፣ የማስጠንቀቂያና  የማስገንዘቢያ ጽሑፍ በ2012 ዓ.ም. ባሳተምኩት፣ ‹‹ኢኮኖሚው ሦስቱ ፖለቲከኞችና ፖሊሲ›› በሚል ርዕስ በታተመው መጽሐፌ በምዕራፍ አምስት ውስጥ አቅርቤአለሁ፡፡ በአንድ ንዑስ ክፍልም የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን እንደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሊያደርጓት ሌት ተቀን ተግተው ሳያሰልሱ እየሠሩ ናቸው የሚል ማስገንዘቢያ አቅርቤአለሁ፡፡

በ2012 ዓ.ም. መጽሐፌ ውስጥና ቀደም ሲል እ.ኤ.አ. በ2017 በእንግሊዝኛ በጻፍኩት ‹‹ለውጥን ፍለጋ…›› በሚለው መጽሐፌ ውስጥ  የውጭ ኃይሎች፣ በተለይም አድገናል፣ ጠንካራ የኢኮኖሚ፣ የጦርና መከላከያ ተቋማት ገንብተናል የሚሉት የምዕራቡ ኢምፔሪያል አገሮች መንግሥታት ከ1990ዎቹ መባቻ ጀምሮ ለኢኮኖሚ ፍለጎትና ጥቅማቸው ሲሉ እያራመዱት መጥተዋል ያልኩትን የርቀት ሥውር/ህቡዕ ቅኝ  አገዛዝ ሥርዓት (Colonialism-in-Absentia) ላይ ማብራሪያዎች አቅርቤያለሁ፡፡ ይህ ሥርዓት የጀርመን መሪ በነበረው በቢስማርክ እ.ኤ.አ. በ1880ዎቹ አፍሪካን በመቀራመት በቅኝ ግዛት ለመግዛት ከተደረገው ስምምነትና ዕቅድ በኋላ ከነበረው ቅኝ አገዛዝ (Colonialism)፣ በ1930 እና 40ዎቹ ጀምሮ አፍሪካውያን ከዚህ ዓይነቱ ቅኝ አገዛዝ ሥርዓት ራሳቸውን ነፃ ለማውጣት ባደረጉት ትግልና መስዋዕትነት ካገኙት የይስሙላ የፖለቲካና የሕዝብ አስተዳደር ነፃነት ጀርባ፣ ቅኝ ገዥዎቹ ተጣብቀው ከፈጠሩት፣ እነ ኑኩሩማና ፊደል ካስትሮ የኒኦ ኮሎኒሊዝም (Neo-Colonialism) ቅኝ አገዛዝ ሥርዓት ብለው ከስተዋወቁት፣ ዓይነት ለየት ያለ ነው፡፡

የርቀት ሥውር/ህቡዕ ቅኝ አገዛዝ ሥርዓት ከቀድሞዎቹ ሁለት የቅኝ አገዛዝ ሥርዓቶች የሚለየው አንድም በአመራር ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ ለቅኝ ተገዥነት በሚታጩትና በሚያዙት አገሮች መረጣም ላይ ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የዚህ መሰሉ ሥርዓት ትኩረቱ ፖለቲካ ሳይሆን የኢኮኖሚ ዓውዱ መሆኑና ከዓለም ገንዘብ ድርጅትና ዓለም ባንክ ከመሳሰሉ ተቋማዊ መሣሪያዎቹ በተጨማሪ የታዳጊ አገሮቹን የተለያዩ ዘርፎች ሊሒቃን በጣምራ ባንዳነት (የኢኮኖሚና ፖለቲካ) መልምሎ፣ አሠልጥኖና ተገቢውን የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ፣ አስፈላጊም ከሆነ የጦር መሣሪያ አስታጥቆ፣ ማሰማራቱ ነው፡፡

ከ1990ዎቹ በፊት የነበሩት የቀድሞዎቹ ሥርዓቶች በዋነኛነት በአውሮፓውያን አገሮች መንግሥታት የሚመሩ ሲሆን የርቀት ሥውር/ህቡዕ ቅኝ አገዛዝ ሥርዓት ደግሞ በአብዛኛው በአሜሪካኖቹ  የሚመራና በዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ ደባ ዛሬ ላይ በተለያዩ የኢኮኖሚ ማሻሻያና የመዋቅር ለውጥ ፕረሮግራምና ፕሮጀክቶች አማካይነት የአፍሪካ አገሮችን የተፈጥሮ ሀብት ለመበዝበዝና ሕዝቡን በድህነት አረንቋ ውስጥ አፍኖ፣ ታዳጊ አገሮቹ የአደጉ አገሮች ልግስናና ምፅዋት ጠባቂ እንዲሆኑ ተዘርግቶ እየተስፋፋ ያለ ሥርዓት ነው፡፡

ከአገሮች ምርጫ አንፃር የቀድሞዎቹ ሁለት ዓይነቶች፣ ኮሎኒያሊዝምና ኒኦ ኮሎኒሊዝም፣ እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉትን አገሮች የማያካትቱ ሲሆን፣ የርቀት ሥውር/ህቡዕ ቅኝ  አገዛዝ ሥርዓት ግን ኢትዮጵያን ያካትታል፣ ዛሬ ላይ ደግሞ አካቶም እየሰረሰራት ነው፡፡

በሦስተኛነት የርቀት ሥውር/ህቡዕ ቅኝ አገዛዝ ሥርዓት ትኩረቱ የታዳጊ አገሮች የኢኮኖሚ ፀጋዎችና የተፈጥሮ ሀብት ላይ ነው፡፡ በተለይም የማዕድንና የደን ሀብቶችና ውጤቶችን በላቀ ቴክኖሎጂና በርካሽ ጉልበት ለመበዝበዝ  በታዳጊ አገሮች ውስጥ ያለን የፖለቲካና የሕዝብ አስተዳደር ሥርዓትን፣ በተለይም የመንግሥት ተቋማትንና ኃላፊዎችን፣ በአገሬው ሰዎች/ዜጎች፣ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገሮች በዳያስፖራ ስም ከሚንቀሳቀሱት መሀል ለዚህ ሥራ በጥምር ባንዳነት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ እንዲሠለጥኑና እንዲሰማሩ በማድረግ ነው፡፡ አብዛኞቹ የአገር ታሪክና ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ መስተጋብሮች ለአገር አንድነት ያላቸውን ሚና በሚገባ ያልተረዱና በምዕራቡ የኒኦ ሊብራል የነፃ ኢኮኖሚ ትርክት የደነዘዙ ናቸው፡፡ ፖለቲከኞች የሚባሉትን (በሥልጣን ላይ ያሉትም ይህኑ በተፎካካሪ ወይም በተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲካ ቡድኖች ውስጥ የተቧደኑትን) ምናልባትም 99 በመቶ የሚሆኑትን፣ ቅኝ ገዥው አገር በርቀት በሥውር ህቡዕ አደረጃጀቱ ባሉ ተቋማቱና የውጭ ኤክስፐርቶች ቁጥጥር  ውስጥ በማዋል ይገለገልባቸዋል፡፡ ቀጥተኛ ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ባንዳ ፖለቲከኞቹን ለቅኝ ገዥው አገርና ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ፍላጎትና ጥቅም አስፈጻሚዎችና አስከባሪዎች አድርጎ ይመራቸዋል፣ ለዚህ ሥራቸውም የተንደላቀቀ ኑሮ ለመኖር የሚያስችላቸውን የዶላር ተከፋይነትና ጥቀማ ጥቅሞች ይሰጣቸዋል፡፡

በሦስተኛነት ካቀረብኩት ሐሳብ ጋር ተያይዞ የሚገኘው የሚዲያው መሣሪያነት  ነው፡፡ ከባንዳዎችና የዓለም ሁለትዮሽ ሆነ ብዝኃ ድርጅቶች መሣሪያነት ጋር አቀናጅቶ የዓለም አቀፍ ሆነ የአገር ውስጥ ሚዲያዎችን፣ ቅኝ ገዥው አገር፣ ለርቀት ሥውር/ህቡዕ ቅኝ  አገዛዝ ሥርዓቱ ግቦቹ መዳረሻ ያደርጋቸዋል፡፡ ለኢኮኖሚ ፍላጎቱና ጥቅሙ ማሟያነት ያግዙኛል ለሚላቸው ሚዲያዎች የፋይናንስ፣ ቴክኖሎጂና ቴክኒካል ድጋፍ በማድረግ፣ እንደ ሰሞንኛው የአሜሪካኖች ማዕቀብ ማስቀጠልን ዓይነቱን ልፈፋ ለማዕቀብ ጣዮቹ የትክክለኛነት  ገጽታ ለማሰጠት በማመቻቸት፣ ማዕቀብ መጣልን፣ የኢኮኖሚ አሻጥር መጠንሰስንና ማፍላትን ብሎም ማዕቀብን እነደ ሥልት ይዞ መንቀሳቀስ በአገሬው ሕዝብ ዘንድ በቅቡልነት ይሰርፅ ዘንድ ሚዲያውን ይጠቀምበታል፡፡ በተጨማሪም ቅኝ ግዥ አሳቢዎቹ የማይፈልጉትን የአገር መሪ፣ ወይም የመንግሥት ባለሥልጣንና ተቋም ለማስጠላትና ለማስወገድ፣ ቅኝ ገዥውን ደግሞ በዴሞክራሲ ማስፈን፣ በፍትሐዊነት፣ ሰበዓዊነት ቅቡልነት ያገኝ ዘንድ ሚዲያውን የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ አድረጎ ይጠቀምበታል፡፡

በእኔ ምልከታና የመረጃ ማቀናጀት አቅም፣ ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ፣ ከመቶ ሃምሳ በላይ እንደሚሆኑ ከሚነገርላቸው የዋና ዘርፍ (Mainstream) ሚዲያ ተቋማት (የመንግሥት፣ የሕዝብና የግል የኅትመትም ሆነ የኤሌክትሮኒክስ)፣ እንዲሁም እንደ አሸን ከፈሉት የማኅበራዊ ሚዲያ አካላት ውስጥ ቀጥተኛም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ከዘጠና አምስት በመቶ በላይ የሚሆኑት (95 በመቶ) የውጭ ኃይሎችን ፍላጎትና ጥቅም እንዲያስጠብቁ ሆነው የተቃኙ ናቸው ብዬ እገምታለሁ፡፡ መገመት ለምርምርና ጥናት መነሻ ይሆናልና ከአንባቢያን በኩልም በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ዕውቀቱና ልምዱ ያላቸው ምርምርና ጥናት እንዲያደርጉ እመክራለሁ፡፡

አንባቢያን ሆይ! ከላይ ካቀረብኩት መንደርደሪያ ሐሳብና መነሻ አንፃር ዛሬ ላይ የብሔራዊ ፍለጎትና ጥቅማችንን ለማስከበር ስንል ማዕቀብ ጥለናል የሚሉ የሰሜን አሜሪካና አውሮፓ አገሮችን መሰሪ የኢኮኖሚ ፍላጎትና ጥቅም ማግኛ እንቅስቃሴውን መመርመርና ማጥናት፣ በዕለታዊ እንቅስቃሴአችንም ክትትል ማድረግ ይገባናል፡፡ በቅርቡ በምዕራብ አፍሪካ፣ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ደግሞ በኮንጎና ሞዛምቢክ የመሳሰሉ አገሮች ውስጥ የሚደረጉ የብዝበዛ እንቅስቃሴዎችን ዛሬ ላይ እኛ አገር በተለያዩ አቅጣጫዎች ከተነሱብን ኃይሎች ማንነትና ሥሪት ጋር አቆራኝቶ ማጥናት፣ መመርመርና መከታተል ተገቢ ነው፡፡ ማዕቀብ ለማዕቀቡ አድራጊ አገሮች መንግሥታትና ድንበር ዘለል ኩባንያዎቻቸው የማኑፋክቸሪንግና የጦር ኢንዱስትሪዎቻቸው ጥሬ ዕቃ ፍላጎትና ጥቅም ማስከበሪያ  የመግቢያ በር መፈለጊያነት የሚውል መሣሪያ ነው፡፡ ከዚህ ሚናው አንፃር፣ ማዕቀብ፣ በጦር ትምህርት ከሚገለጸው የካሙፍላጅ ሽፋን ጋር የሚመሳሰል ተልዕኮ ያለው መሣሪያ ነው፡፡

የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን እንደ ኮንጎ የበርካታ መቶዎች የታጠቁ ቡድኖች መናኸሪያ እንድትሆን፣ እነሱ በዚህ ትርምስና ግጭት መሀል የማሰታረቅ ሥራ የሚሠሩ፣ ባህታዊ መስለው የሚቀርቡ፣ በዴሞክራሲና በነፃ የፖለቲካ ቡድኖች ምርጫ ማካሄድ ስም በአገራችን ውስጥ ሲፏልሉ፣ ኢምፔሪያል ኩባንያዎቻቸው ደግሞ መንግሥትና ሕዝብ ሳያውቅ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ተጠቅመው የማዕድንና ተጓዳኝ ሀብትን ለመዝረፍ ይሰማራሉ፡፡ ይህን በማድረግ ረገድ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠሩ  ቢሆኑም በቅርቡ ግን ከመቼውም ጌዜ በበለጠ የተሳካላቸው እየመሰላቸው መጥተዋል፡፡ በዚህ ስትራቴጂ የኮንጎን ሕዝብ ለማይነጥፍ ወይም ለማይቀንስ ግፍና ጭቆና፣  ለዘላለማዊ ድህነት የዳረገው የርቀት ሥውር/ህቡዕ ቅኝ ገዥዎች ሴራና ተግባር፣ ኢትዮጵያ ውስጥም እየተስፋፋ መምጣቱን ደግሞ በቅረቡ አቶ ገብሩ አሥራት የትግራይ ክልልን አስመልክቶ ከሰጠው ቃለ መጠይቅ ምላሽ መገንዘብ ይቻላል፡፡ እሱ በዚህ ክልል፣ በወርቅና ሌሎች ማዕድናት ላይ የሚደረገውን ሕገወጥ ቁፋሮ፣ ዘረፋና የሀብት ማሸሽ አስመልክቶ የሰጠንን መረጃ በቀላሉ ማየት የለብንም፡፡ የአቶ ገብሩ ቃለ መጠይቅ በሪፖርተር ጋዜጣ እሑድ ነሐሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. በቆይታ ዓምዱ ‹‹የሕወሓት መንገድ ሁሉም ወደ ገደል ካልሆነ ወደ በጎ አይወስድም›› በሚል ርዕስ ታትሞ ስለሚገኝ በድጋሚም ቢሆን ያንቡት፡፡

ዛሬ ላይ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶች፣ ጦርነቶችና ብዝኃ አቅጣጫ ያላቸው የሰላም ዕጦት ኩነቶችና ውጥንቅጦች፣ በእኔ አረዳድና መረጃ ዳሰሳ፣ በሰሜን ምዕራብ አሜሪካና አውሮፓ አገሮች የማይነጥፍ የኢኮኖሚ፣ በተለይም የማዕድን ሀብት ፍላጎትና ጥቅም ማስከበር ሴራ ጋር  የተያያዙ ናቸው፡፡ ከእነዚህ አካባቢ ካሉ አገሮች የሚንቀሳቀሱ፣ የኢትዮጵያን ምድር ምንጊዜም በጦርም ሆነ ዛሬ ላይ በሚከተሉት ሥውር አካሄድ ለመያዝ ከቅዠት ወጥተው በማያውቁ አገሮች ኢትዮጵያ ተደጋጋሚ የግጭትና የጦርነት ሰለባ እንድትሆን እየተደረገች ነው፡፡ በቅርቡ ደግሞ አነዚህ አገሮች፣ የጎረቤት አገር የሆነችውን የሶማሌን መንግሥት ባለሥልጣናት ለተለመደው የሴራ ፖለቲካ ሥራቸውና እኩይ የኢኮኖሚ ሀብት ተጠቃሚነታቸው እየጋለቧቸው ነው፡፡ ደጋግመው የሞከሩንና ደጋግመን ያሸነፍናቸው ቅኝ ገዥ አገሮች ጭምር ለአሁነኛው የሶማሌ መንግሥት የጦረ ሄሊኮፕተሮች ሰጥተዋል፣ ሌሎች ድጋፎችንም እንደሚያደርጉ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ የግብፆቹ ጉዳይ ለዘመናት አብሮን የቆየ ነገር ነውና እዚህ ጋ በሰፊው ስለነሱ እኩይ ተግባርና ተልዕኮ መጻፍ ጊዜና ብዕርን አላግባብ ማባከን ይሆናል፡፡

ለማጠቃለል እዚህ ጋ የሚከተሉትን ሦስት ምክረ ሐሳቦች አቅርቤ ይህን የማስገንዘቢያ ጽሑፌን እደመድማለሁ፡፡ 

  1. ኢትዮጵያውያን ዛሬ ላይ፣ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ፣ የውጭ ኃይሎችን ሴራና ደባ ነቅተን በመከታተል፣ ራሳችንን ከውድቀት፣ አገራችንን ከውድመት መጠበቅ አለብን፡፡ በፖለቲካ፣ በተለይም የዴሞክራሲ ማስፈን ስም፣ አብረውም በሰብዓዊ መብት መከበር፣ ብሎም በሰብዓዊ ዕርዳታ ስም የርቀት ሥውር/ህቡዕ ቅኝ አገዛዛ ሥርዓት መሣሪያዎችና ሥልቶችን ተጠቅመው ኢትዮጵያውያንን ከዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት መሪነት፣ የነፃ ሕዝቦች ተምሳሌነት አውርደው፣ ጥለው፣ ሕዝባችን በዘመናዊ ባርነት ውስጥ ለመዝፈቅና አገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ሀብትና ፀጋ ለራሳቸው የኢኮኖሚ ፍላጎትና ጥቅም ለማዋል የሚያደርጉትን ብዝኃ አቅጣጫ እንቅስቃሴ ለማክሸፍ፣ ጦር ሰብቀው፣ ወይም አሰብቀው የሚመጡ የውጭ ኃይሎችን ድባቅ ውስጥ ለመክተትና አገራችንን ከፀጉረ ልውጦች ለመጠበቅ ሌት ተቀን በተጠንቀቅ ላይ መሆን ይኖርብናል፡፡
  2. ዛሬ እርስ በርስ አጋጭተው፣ አበጣብጠው፣ ጠመንጃ አማዘው በአገራችን ውስጥ ለተከታታይ የአሥር ዓመት የኢኮኖሚ ልማትና ዕድገት ጊዜ እንዳናገኝ ማድረጋቸው አዲስ ነገር አይደለም፡፡ አገራችን በእርስ በርስ ግጭት ለተከታታይ ከሰላሳ በላይ ዓመታት በጦርነት ታምሳ (በ16ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ) እንደ አገር የቀጠለች፣ የመሳፍንትና የቅኝ ገዥዎችን ዓውዳሚ የጦርነት ጊዜያት ያሳለፈች፣ ባለብዙ ተሞክሮ የሆነች የፅናት ተምሳሌት አገር ናት፡፡ ይህም ይቀጥላል፡፡ በእርግጥ በ16ኛው ክፍለ ዘመን አፄ ፋሲል አደረጉት እንደተባለው የውጭ ዜጎችን ከአገር ጠራርገው እንደአስወጡት፣ ዛሬ ላይ ደግሞ የወቅቱ መንግሥት በስምምነት ሆነ በመግፋት እነዚህን ኃይሎች አገራችንን ጥለው እንዲወጡ ባያደርግም፣ ቢያንስ የእነሱ ስንዴ ተሰፋሪ፣ የገንዘብ ተመፅዋች ያልሆነች፣ ዛሬ ካለንበት የኑሮ ደረጃ በተሻለ ዜጎቿ የሚኖሩባት ኢትዮጵያ እንድትኖር፣ የማዕቀብ ጋጋታና የድንጋጌዎች ምናብ ሳያዘናጋው፣ ነቅቶና ተግቶ መሥራት አለበት፡፡
  3. ኢትዮጵያ በውስጥ የእርስ በርስ ግጭቶችና ጦርነቶች፣ ከውጭ በሚነሱ ወረራዎችና የጥፋት ኃይሎች ተፈትና ያለፈችው ዛሬ ላይ ከየአቅጣጫው ማዕቀብ አድርገናል የሚሉ አገሮች መካከል ዋነኞቹ እንደ አገር ከመፈጠራቸው በፊት ነው፡፡ ማዕቀብ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ተጀምሮ፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ተጠናክሮ፣ የሚተገበር የምዕራቡ ኢምፔሪያሊስት አገሮች የኢኮኖሚ ፍላጎትና ጥቅማቸው ማስከበሪያ መሣሪያ ነው፡፡ ማዕቀብ ለእነሱ የኢኮኖሚ ፍላጎትና ጥቅም ሲባል በራችንን በርግደን አንተውም ባሉ አገሮች ላይ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ፣ የሚተገበር እኩይ የፖሊሲ መሣሪያ ነው፡፡ በተለይ አገራዊ የኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲንና ስትራቴጂን በሚከተሉ መንግሥታት ላይ የሚያነጣጥር የማዳከሚያና ያልተረጋጋ ኢኮኖሚ ማስፈኛ ስትራቴጂ አንዱ መሣሪያ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ግን ይህ የከረመ ስትራቴጂና መሣሪያ፣ ከዘመነና ከመጠቀ የመረጃና ተግባቦት ቴክኖሎጂ ጋር አቆላልፈው፣ በምዕራቡ አደጉ በሚባሉት ኢምፔሪያሊስት አገሮች ውስጥ ያሉትን ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵውያንን በመጠቀም፣ ለዘመናት በጦርነት ሊያንበረክኳት ያልቻሏትን አገር፣ በሐሰትና በአድሏዊነት በተቃኘ የፕሮፓጋነዳ ስትራቴጂ ኢትዮጵያን በዘር፣ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በቀለም፣ ወረድ ብለውም በጎሳ፣ በጎጥ ከፋፈለው፣ በወሬና በዲስኩር ሊያንበረክኳት የተቃረቡ መስሏቸዋል፡፡ ይህ ግን እውነተኛ በሆኑት፣ በሁሉም የአገሪቷ ክፍል ባሉ፣ ኢትዮጵያውያን ልጆቿ ትግልና መስዋዕትነት ዕውን አይሆንም፡፡ ዕውን እንዳይሆንም ሁላችንም በአንድነት ልንታገላቸው ይገባል፡፡

በአጭሩ ውድ ኢትዮጵያውያን ሆይ!!

ለውጭ ኃይሎች ብሔራዊ ፍላጎትና ጥቅም ስንል ሳይሆን፣ ለኢትዮጵያ ፍላጎትና ጥቅም ብለን፣ በአንድነት የውጭ ኃይሎችን መሰሪ ሥራና ተልዕኮ ለማክሸፍ መነሳት ያለብን ወቅት ላይ የደረስን ስለሆነ፣ ሁላችንም ባለንበት አካባቢ፣ ሥራ፣ ሙያ ባለን አቅምና ችሎታ በንቃትና በብቃት ይህን ተልዕኳቸውን ለማክሸፍ እንነሳ፡፡ ጉዳዩ የፖለቲካ ሳይሆን፣ የኢኮኖሚ በተለይም የምድራችን፣ በላይዋ ሆነ በውስጧ ከያዘቻቸው ሀብትና ፀጋዎች ጋር የተያያዘና እኛንም በርቀት ሥውር/ህቡዕ ቅኝ አገዛዝ ሥርዓትና ዘመናዊ ባርነት ውስጥ ቀፍድዶ ከመቆጣጠርና ከመበዝበዝ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ነው፡፡  የውጭ ኃይሎች የኢኮኖሚ ማዕቀብና አሻጥር ለዚህ እንዳይዳርገን ነቅተን እንከታተለው፣ ያቀዱት ዕቅድም እንዲከሽፍ እናድርግ፡፡ በተለይም ከእርስ በርስ ግጭትና ጦር መማዘዝ ወጥተን፣ በችግሮቻችን ዙሪያ በመነጋገርና በመወያየት መፍትሔ በመሻት፣ አንድ ሆነን የአገራችንን ሉዓላዊነት እናስጠብቅ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የግብርና ኢኮኖሚ ተመራማሪና ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው demesec2006@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡