እኔ የምለዉ የቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም (ፎካክ) ለአፍሪካ መዘመን ያለው ሚና

አንባቢ

ቀን: September 15, 2024

በመላኩ ሙሉዓለም

ዘመናዊነት (Modernization) የአንድ ማኅበረሰብ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሒደት ነው። ለአንድ አገር ልማትና ዘመናዊነት ለማምጣት የተለያዩ ሞዴሎች አሉ፡፡ ዘመናዊነት እንዲስፋፋ በአገሮች መካከል ትብብር፣ አጋርነትና የልምድ ልውውጥ አስፈላጊ ናቸው። የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ነሐሴ 29 እስከ ጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በተካሄደው የቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም (ፎካክ) የቤጂንግ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ነው። በዚህ ጉባዔ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ሌሎች 52 የአፍሪካ መሪዎችና የተለያዩ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የመሪዎች ጉባዔው የተከፈተው በፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ንግግር ነው። እንደ እርሳቸው ንግግር ከሆነ የዘመናዊነት የመጨረሻ ግብ የሰው ልጅን ሁለንተናዊ ዕድገት ማሳካት ነው፡፡ የመሪዎች ጉባዔው በቻይናና በአፍሪካ አገሮች መካከል የጋራና ጠቃሚ ትብብር እንዲኖር በማድረግ ዘመናዊነት (Modernization) ላይ ያተኩራል። ዘመናዊነት ማስፈን የቻይናና የአፍሪካ የጋራ ፍላጎት ነው።

እ.ኤ.አ በ2013 ጀምሮ ፕሬዚዳንት ዢ የአንድ ቀበቶ የአንድ መንገድ (One Belt One Road Initiative)፣ የዓለም አቀፍ ልማት (Global Development Initiative)፣ የዓለም አቀፍ ደኅንነት (Global Security Initiative) እና የዓለም አቀፍ ሥልጣኔዎች (Global Civilization Initiative) ሐሳብን ወይም ተነሳሽነትን ወስደዋል፡፡ እነዚህ ተነሳሽነቶች ከዘመናዊነት ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ተነሳሽነት ለቀጣይ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ ዕድገቶችና ለውጦች መሠረት ናቸው።

የጋራ ጥቅምና መተማመን በአጋርነት ለመሥራት መሠረት ናቸው። አፍሪካና ቻይና ብዙ ተመሳሳይ ተግዳሮቶች አሉባቸው፡፡ እነዚህም የአየር ንብረት ለውጥ፣ ሥራ አጥነት፣ በዓለም ላይ የሚታይ ኢፍትሐዊነት፣ የኃያላን አገሮች የተናጠል ማዕቀብ፣ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብነትና የመሳሰሉት ናቸው። እነዚህንና መሰል ተግዳሮቶችን በትብብርና በአጋርነት መቋቋም ይቻላል።

ብዙ የአፍሪካ አገሮች ሰላምና ደኅንነት፣ የአካባቢ መራቆት፣ ማይምነት፣ ድህነት፣ ሕገወጥ የገንዘብ ፍሰት፣ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር፣ ስደት፣ ሙስና፣ ኢፍትሐዊነት፣ ሥራ አጥነት፣ መሠረተ ልማቶች፣ የኃይል ምንጭ፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሽብርተኝነት፣ የባህር ላይ ዝርፊያና የመሳሰሉት ችግሮች አሉባቸው፡፡ አንዳንዶቹ ድንበር ተሻጋሪ ችግሮች ናቸው። እንዲህ ዓይነት ሁለንተናዊ ችግሮች የሚፈቱት በአንድ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ከሌሎች አጋሮችና ተባባሪዎች ጋር በመተባበር መሥራት ነው፡፡

የቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም ለቻይናም ሆነ ለአፍሪካ የጋራና የተለዩ ችግሮችን የመፍትሔ ሐሳቦችን የሚያቀርቡበት መድረክ ነው። ሰላምና ፀጥታ፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ ትምህርት፣ ጤናና ፈጠራ ለዘመናዊነት ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው። የፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ተነሳሽነቶችን ተግባራዊ ማድረግ በአፍሪካ ውስጥ ያሉ በርካታ ችግሮችን መፍታትና ወደ ዘመናዊነት ማምጣት ያግዛል።

በመሆኑም አፍሪካውያን ሁለት ፈተናዎችን ማለፍ አለባቸው። የመጀመሪያው ከሰላም፣ ኢኮኖሚ፣ ፍትሕ፣ እኩልነት፣ ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች ጋር የተያያዙ ችግሮችን መፍታት ነው። ቀጣዩ ፈተና ወደ ዘመናዊነት መሄድ ነው። በቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም የመሪዎች ጉባዔ ላይ ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ በቻይናና በአፍሪካ መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከርና ለጋራ ጥቅም ለመሥራት በርካታ ቃሎች ገብተዋል። በቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም የመሪዎች ጉባዔ ላይ በቻይና የቀረቡትን ልምድና ተሞክሮ፣ የፋይናንስ፣ ሥልጠና፣ የዕድገት ሞዴል፣ ደኅንነትን ማሻሻልና ሌሎች በርካታ የተገቡ ቃሎችን አፍሪካ አገሮች የሚያገኙበት ጥሩ አጋጣሚ ነው።

የመሪዎች ስብሰባ ተከትሎ የወጣው የቤጂንግ መግለጫና የድርጊት መርሐ ግብር (እ.ኤ.አ. 2025-2027) በአፍሪካ ኅብረትና በቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም ዓላማዎች መካከል ያለውን አንድነት አሳይቷል። በተጨማሪም የመሪዎች ፎረሙ የሰው ልጅን አኗኗር ማዘመን፣ የዘመናዊነትን ልምድ መለዋወጥ፣ የሚሠሩ ልማቶች ሕዝብን ማዕከል ማድረግ፣ በአዲስ ኢንዱስትሪያል አብዮት ውስጥ ያለውን አጋርነት ማጠናከር፣ በመከባበርና በመተሳሰብ መርህ ላይ መሥራት፣ ዘመናዊ አገልግሎቶችን ማስፋፋት፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ማካፈልና ማዘመን አስፈላጊ መሆኑን አስምሮበታል።

የአፍሪካ ኢንዱስትሪዎችና ግብርናዎች፣ የድህነት ቅነሳ ፕሮጀክቶችን ማካሄድ፣ የኢኮኖሚ ዞኖችና የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት፣ የቻይናን ኢንቨስትመንቶች በአፍሪካ ማሳደግ፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታና ቀጣናዊ ውህደትን መደገፍ፣ ለየኃያላን ብዝኃነት ዓለም ላይ (Multipolar) መሥራት፣ የፀጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ የፀጥታና የዓለም አስተዳደርን ማሻሻል፣ በቻይና-አፍሪካ ኅብረት የኃይል (Energy) አጋርነት፣ የኑክሌር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ ተግባራት መጠቀም፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል የገቢና የወጪ ንግድ ማሻሻል፣ የዲጂታል ኢኮኖሚን ማስፋት፣ ልማት ዘላቂነት እንዲኖረው ማድረግ፣ በፋይናንስ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በመገናኛ ብዙኃን፣ በፆታና በመሳሰሉት መተባበር አስፈላጊነት ላይ አፅንኦት ሰጥቷል፡፡

ኢትዮጵያ የአንድ ቀበቶ የአንድ መንገድ አባል አገር እንደ መሆኗ በቻይና ከተከናወኑ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ብዙ ጥቅሞችን አግኝታለች። ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን መድረኮች እየሠራች ነው። ቻይና አዲስ አበባንና ጂቡቲን የሚያገናኝ የባቡር መስመር ገንብታለች፣ በዋና ከተማዋ በርካታ የኢንዱስትሪ ፓርኮችንና የቀላል ባቡር መንገዶችን ሠርታለች፡፡ በብዙ የኢትዮጵያ ከተሞች የቀለበት መንገዶችና አውራ ጎዳናዎች ሠርታለች። እነዚህም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ተጠቃሚ የሆኑበት ለቀጣይ ዘመናዊነት ጉዞ መሠረት ናቸው።

እ.ኤ.አ. በ2003 ኢትዮጵያ የቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም የሚኒስትሮች ስብሰባ በአዲስ አበባ ከቻይና ጋር በጋራ አዘጋጅታለች። ይህ የሚያሳየው ኢትዮጵያ ቻይናንና አፍሪካን በጥብቅ የሚያስተሳስር ሁለንተናዊ የባለብዙ ወገን ፎረም ላይ ያላትን ድጋፍና ቁርጠኝነት ነው። ቻይናም ሀብቷንና ልምዷን ለኢትዮጵያ እያካፈለች ነው። ቻይና በምታደርገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳተላይቷን ወደ ህዋ ልታመጥቅ ችላለች። ይህ በኢትዮጵያና በቻይና መካከል አርዓያነት ያለው ግንኙነት መኖሩን ያሳያል።

የቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም መግለጫና የድርጊት መርሐ ግብር በቻይና፣ በኢትዮጵያና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (UNIDO) መካከል በተደረጉ የሦስትዮሽ ስምምነቶች የልህቀት ማዕከል መመሥረትም ትልቅ ጥቅም አስገኝቷል። ዓላማው ቀጣይነት ያለው ኢንዱስትሪ መስፋፋት፣ ግብርና ማዘመን፣ አረንጓዴ ልማትና በአፍሪካ የክህሎት ልማትን ማሳደግ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ማዕከሉ ለአፍሪካ አገሮች የፖሊሲ ምክክርና የልማት ዕቅድ ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል። የቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም የድርጊት መርሐ ግብር ኢትዮጵያ በብሪክስ (BRICS) ኅብረት አባል መሆኗን በመልካም ጎኑ አንስቶታል፡፡ በዚህም ሁለቱም አገሮች በጋራ ዓላማዎች ላይ የሚወያዩበት ተጨማሪ የባለብዙ ወገን መድረክ ሆኖ ያገለግላል። ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች በብሪክስ ትብብር በአባልነት ቢሳተፉ መልካም መሆኑን ቻይና ገልጻለች።

ለማጠቃለል ያህል በ2016 ዓ.ም. መጨረሻ የተከናወነው የቻይና-አፍሪካ ትብብር የመሪዎች ጉባዔ ቻይናንና አፍሪካን ወደ ዘመናዊነት ለመቀየር በማለም የተከናወነ ነበር። ጉባዔውን ተከትሎ የወጣው መግለጫና የድርጊት መርሐ ግብሩ በቻይናና በአፍሪካ መካከል ያለ ጣልቃ ገብነት፣ ሕዝብን ያማከለ ልማት፣ እኩልነት፣ መከባበርና ከፍተኛ ጥራት ባለው ልማት ላይ የተመሠረተ የጋራ ዕድገት ሊኖር እንደሚገባ አስምሮበታል። እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካት ሁለቱም ወገኖች በመተማመንና በመተባበር ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው melakumulu@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡