ኢራናዊ ሴት

ከ 7 ሰአት በፊት

“ለሥራ ቃለ መጠይቅ እያደረግኩ በነበረበት ወቅት ባለቤቴ መሥራቴን እንደሚፈቅድ የሚገልጽ የጽሁፍ ማስረጃ እንዳቀርብ ተጠይቅኩ” ይህንን ያለችው በነዳጅ እና በጋዝ ኢንጂነሪንግ የማስተርስ ዲግሪ ያላት ኢራናዊቷ ኔዳ ናት።

በትምህርቷ የላቀ ደረጃ ላይ የደረሰችው ኔዳ ሥራ ለመቀጠር ባለቤቷ መፍቀዱን የሚያሳይ የጹሁፍ ማስረጃ አምጪ ስትባል መዋረድ ተሰማኝ ትላለች።

“ትልቅ ሰው ነኝ። የራሴን ውሳኔ መወሰን የምችል ሰው ነኝ አልኳቸው” ስትል ኔዳ ለቢቢሲ ተናግራለች።

በኢራን ያገቡ ሴቶች ሥራ ለመሥራት ከፈለጉ የባሎቻቸውን ፍቃድ እንዲያገኙ ሕጉ ያዛል።

ይህም ወደ ሥራው ዓለም ለመግባት የሚፈልጉ ሴቶች ከሚገጥሟቸው በርካታ የሕግ እንቅፋቶች መካከል አንዱ አድርጎታል።

ዘንድሮ የወጣው የዓለም ባንክ ሪፖርት ኢራን ከሥራ ጋር በተያያዘ ለሴቶች እንቅፋቶች የሚሆኑ ሕጎችን በማውጣት ከከፉ አገራት ተርታ አስቀምጧታል።

የዓለም የምጣኔ ሀብት ጉባኤ (ወርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም) በዓለም አቀፍ የሥርዓተ ፆታ ክፍተት ላይ ባጠናቀረው የዚህ ዓመት ሪፖርቱ ከሸፈናቸው 146 አገራት መካከል ኢራን ሴቶችን በመቅጠር በዝቅተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል።

ምንም እንኳን በዩኒቨርስቲ ከተመረቁ ዜጎች ውስጥ ሴቶች 50 ከመቶ በላይ ቢሆኑም በሥራው ዘርፍ ላይ የተሰማሩት 12 በመቶ መሆናቸውን የባለፈው ዓመት መረጃ ያሳያል።

በሥርዓተ ፆታ ላይ የተመሠረቱ አድሏዊ ሕጎች፣ ወሲባዊ ትንኮሳዎች እንዲሁም በተቀጠሩ ሴቶች ላይ ያለው የፆተኝነት አመለካከት የሥራ ከባቢን ለሴቶች ጤናማ ያልሆነ አድርጎታል።

ቢቢሲ ለዚህ ጽሁፍ ያነጋገራቸው ሴቶች በሥራ ቦታቸው ላይ በቁም ነገር እንደማይወሰዱ እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።

“የተለያዩ ሕጋዊ እና ባህላዊ እንቅፋቶች ኢራናዊ ሴቶችን ከሥራ ውጪ እያደረጋቸው ነው” ሲሉ የዓለም ባንክ የቀድሞ ከፍተኛ አማካሪ ናዴሬህ ቻምሉ ገልጸዋል።

በአገሪቱ ያሉ የሕግ ገደቦች፣ በፆታዎች መካከል ያለው የክፍያ ልዩነት ሴቶች በኢራን ውስጥ ባለው የሥራ ኃይል የመሠማራታቸውን ተሳትፎ ውስን እንዳደረገው አማካሪዋ ያስረዳሉ።

ኢራናዊ ሴቶች

ሕጋዊ እና ባህላዊ ማነቆዎች

ወንዶች ሚስቶቻቸውን ሥራ ከመሥራት በሕጋዊ መንገድ ማስቆም እንደሚችሉ ያውቃሉ እናም አንዳንዶች ይህንን ሆን ብለው ይጠቀሙበታል።

ኢራናዊው የሥራ ፈጣሪ ሰኢድ በአንድ ወቅት “አንድ የተበሳጨ ባል ወደ ቢሯችን በኃይል ገብቶ የብረት ዘንግ በአየር ላይ እያወዛወዘ እና እየጮኸ ‘ሚስቴን እንድትቀጥር ማን ፈቀደልህ?” እንዳለው ለቢቢሲ ተናግሯል።

በዚህም የተነሳ ሰኢድ ያገቡ ሴቶችን በሚቀጥርበት ወቅት ከባሎቻቸው የጽሁፍ ፍቃድ እንዲያመጡ ይጠይቃል።

በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ የሚሠራው ራዚህ አንድ የተናደደ ግለሰብ ቢሯቸውን በኃይል ጥሶ በመግባት ተመሳሳይ ነገር ማድረጉን ያስታውሳል።

የተናደደው ግለሰብ “ባለቤቴ እዚህ እንድትሠራ አልፈልግም” ሲል ለዋና ሥራ አስኪያጁ በኃይለ ቃል መናገሩን ራዜህ ያስረዳል።

ሥራ አስኪያጁ በኩባንያው ውስጥ ከፍተኛ የሂሳብ ሹም ለሆነችው ሴትም “ወደ ቤቷ ሄዳ ከባሏ ጋር ነገሮችን እንድታስተካክል እና አለዚያ ግን ሥራ መልቀቅ እንዳለባት ነገራት” ይላል ራዜህ።

ግለሰቧም በመጨረሻ ከሥራዋ ለቀቀች።

ይህ ሕግ ያገቡ ሴቶችን ብቻ ሳይሆን በርካታ ኩባንያዎች ሴቶችን እንዳይቀጥሩ ምክንያት እንደሆናቸው ከፍተኛ አማካሪዋ ያሰረዳሉ።

አሠሪዎች “ወጣቶቹን ሴቶች አሠልጥነው ከቀጠሩ በኋላ ባሎቻቸው ከሥራ እንደሚያስወጧቸው በማሰብ ጉልበታቸውን ማባከን አይፈልጉም” ይላሉ።

ሴቶች ከቤተሰቦቻቸው እና ከትዳር አጋሮቻቸው ጋር ታግለው የሥራ ፈቃድ አግኝተው መቀጠር ቢችሉም በሥራ ላይ ያለው መድልዎ አንዳንዱም በሕግ የተደገፈ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሥራ ዓለምን ለኢራናውያን ሴቶች ፈታኝ አድርጎታል።

ከእነዚህ አንዱ የፍትሃ ብሔር ሕግ አንቀጽ 1105 ሲሆን፣ ይህም ባል የቤተሰብ አስተዳዳሪ እንደሆነ የኑሯቸውን ወጪ መሸፈን እንዳለበት ይጠቅሳል።

ይህም ወንዶች ከሴቶች ይልቅ ለሥራ ቅድሚያ የሚሰጥ ነው። ሴቶች የሥራ ዕድል ካገኙም ከባለቤቶቻቸው ጋር ሲነጻጸር ባነሰ ደመወዝ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

በ20ዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኘው ራዝ ሥራዎችን ቀያይራለች። በሠራችበት መሥሪያ ቤቶች ሁሉ መጀመሪያ የሚቀነሱት ሴቶች እንደሆኑ ትናገራለች።

“በመጨረሻ የተቀጠርኩበት ድርጅት መዋቅሩ በአዲስ መልክ ሲሠራ ሁሉም ማለት በሚቻል ሁኔታ ከሠራ የተባረሩት ሴቶች ናቸው” ትላለች።

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀች ሌላ ኢራናዊት ከአስር ዓመት በላይ በሥራ ላይ ከቆየች በኋላ ቤት ውስጥ ለመቆየት የወሰነችበትን ምክንያት ትናገራለች። “በሥራዬ በፍጹም ዕድገት እንደማላገኝ ገባኝ” ትላለች።

“ወንዶች እስካሉ ድረስ በብቃት ያነሱ ቢሆኑም እንኳን ደመወዝ ጭማሪ ወይም ዕድገት እንደማይሰጠኝ ተረዳሁኝ። ጊዜዬን ማባከን ነው የሆነብኝ” ትላለች።

ኢራናዊት ኬክ እየጋገረች

ሴቶች በሕጉ መሠረት እንደ ቤተሰቡ አስተዳዳሪ አለመታየታቸውን ተከትሎ በሥራ ላይ በሚያገኙዋቸው ጥቅማጥቅሞች እና ቦነስ ላይ ተጽእኖ ያሳድራል።

በሥራ ላይ ላሉ ጥቅማጥቅሞች ብቁ ከሆኑ እንኳን “በሥራ ዘመናቸው የሚያጠራቅሙት ገንዘብ ለምሳሌ እንደ ጡረታ ያሉ ክፍያዎች ለቤተሰቦቻቸው ላይሰጡ ይችላሉ” ይላሉ ከፍተኛ አማካሪዋ።

ከቴህራን ዩኒቨርስቲ በሥነ ጥበብ የማስተርስ ዲግሪ ያላት ሴፒዴህ በዩኒቨርስቲው ታስተምር እንዲሁም የጥበብ ፕሮጀክቶችንም ትሠራ ነበር። ነገር ግን ሥራዋን ካቋረጠች ጥቂት ዓመታት አልፈዋል።

“ከተመረቅሁ በኋላ እንደማውቃቸው ወንዶች ተቀጥሬ ኑሮዬን መግፋት እንደምችል አስቤ ነበር። ነገር ግን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መዋቅሩ ሴቶች በሙያቸው የሥራ ዕድል በማያገኙበት መልኩ ነው የተዋቀረው” ስትል ሴፔዴህ ለቢቢሲ ተናግራለች።

በተጨማሪም አገሪቷ ሴቶችን በአስገዳጅ መልኩ ሂጃብ መከናነብ አለባቸው የሚለው ሕጓ ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞን ያቀጣጠለ እና አሁንም የውዝግብ መንስኤ ሆኖ ቀጥሏል።

በተለይም በመንግሥታዊ እና ሕዝባዊ ተቋማት የሚሠሩ ሴቶች ሂጃብ ካልጠመጠሙ መቀጠር አይችሉም።

የኢራን ምጣኔ ሀብት በማዕቀብ እንዲሁም በአስተዳደር ችግር ምክንያት እየተንገዳገደ ይገኛል። የኢራን ሴቶች በሥራ ላይ ተሰማርተው ከወንዶች ጋር እኩል ደረጃ ላይ ቢደርሱ የአገሪቱ ጥቅል ምርት (ጂዲፒ) 40 በመቶ ሊጨምር እንደሚችል ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) አመልክቷል።

የአገሪቱ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ከሴቶች የሥራ ተሳትፎ ጋር የተቆራኘ መሆኑን ተቋሙ ገልጿል።

በአሁኑ ወቅት ከኢራን አመራሮች በኩል ሴቶችን ወደ ሥራው ዘርፍ የማምጣት ፖለቲካዊ ፍላጎት ባይታያቸውም የኢራን ሴቶች አነስተኛ የተናጠል የንግድ ሥራዎችን በማቋቋም የሥራ መድረኩን እየተቆጣጠሩት እንደሆነ አማካሪዋ ይናገራሉ።

“የምግብ ማብሰያ መተግበሪያዎች፣ የዲጂታል ችርቻሮ መሸጫዎችን የመሳሳሉ አዳዲስ የንግድ ሃሳቦች በሴቶች ተጀምረዋል። በኢራን ውስጥ የግሉ የሥራ ዘርፍ በአብዛኛው ሴቶች ባለቤት የሆኑበትን ንግዶችን የያዘ ነው” ይላሉ።