ሪክ ዳላዌይ

ከ 7 ሰአት በፊት

ሪክ ዳላዌይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለገሰ ዐይነ ምድር ላይ የሚደረገውን ክሊኒካዊ ሙከራ እንዲቀላቀሉ በተጋበዙበት ወቅት “ዐይነ ምድርን ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው የማስገባት አጠቃላይ ሐሳብ በእርግጥ እንግዳ ነገር ነው” የሚል ስሜት ነበር የተሰማቸው።

የ50 ዓመቱ አዛውንት በዩናይትደ ኪንግደም (ዩኬ) በርሚንግሃም ዩኒቨርስቲ በሚካሄደው ሳምንታዊ የዐይነ ምድር የማዘዋወር የሁለት ወራት መርሃ ግብራቸውን ጨርሰዋል። ስክሌሮሲንግ ቾላንጊትስ (ፒኤስሲ) ተብሎ የሚጠራና ያልተለመደ ሥር የሰደደ የጉበት በሽታ ምልክቶችን ለመቆጣጠር ተስፋ ያደረገ ምርምር ነው።

ሂደቱን ሲያብራሩም “ይህ ትንሽ ዐይነ ምድር አይደለም የሚሰጠው። በቤተ ሙከራ ውስጥ የታከመ ነው” ሲሉ እየሳቁ ያስረዳሉ።

በአሁኑ ጊዜ የሪክ ያልተለመደ በሽታ ከጉበት ንቅለ ተከላ በስተቀር ምንም ዓይነት መድኃኒት የለውም። በዩኬ ውስጥ ከ100 ሺህ ሰዎች ውስጥ ከስድስት እስከ ሰባት የሚደርሱትን የሚያጠቃ ሲሆን፣ በሕይወት የመኖር ዕድሜን ከ17 እስከ 20 ዓመታት ያሳጥራል።

ሪክ በ42 ዓመታቸው ማለትም ከስምንት ዓመታት በፊት ነበር የጤና ችግሩ እንዳለባቸው ያወቁት።

“በጣም ተጨንቄ ነበር። ስለ ወደፊቱ ጊዜ በጣም ተጨነቅኩ። ከገደል እንደ መውደቅ ነው ስሜቱ” በማለት የነበራቸውን ሁኔታ ያስታውሳሉ።

ዓይነ ምድር ሕክምና ምንድን ነው?

ፊክል ማይክሮባዮታ ትራንስፕላንት

ፊክል ማይክሮባዮታ ትራንስፕላንት (ኤፍኤምቲ) ወይንም የዐይነ ምድር ንቅለ ተከላ በመባል ይታወቃል። ይህ ዘዴ በብዙ አገራት ውስጥ የአንጀት በሽታ ላለባቸው ሰዎች በክሊኒካዊ ምርምር ደረጃ ቢሆንም በጥቅም ላይ ይውላል።

ጤናማ ዐይነ ምድር ለጋሾች ይጣሩ እና የአንጀት ባክቴሪያ ከናሙናዎቻቸው ተወስደው ወደ ታካሚ አንጀት እንዲገቡ ይደረጋል። ብዙውን ጊዜ በኮሎንኮስኮፒ፣ ኤንማ ወይም ናሶጋስትሪክ ቱቦ በኩል ይሰጣል።

ሪክ የፒኤስሲ ህክምናውን የወሰደው በሙከራ ደረጃ ነው። ይህ ሙከራ ዩኬ ውስጥ ለአንድ ዓይነት በሽታ ብቻ የሚመከር ነው ሲል የአገሪቱ ብሔራዊ የጤና እና እንክብካቤ ልቀት (ኤንአይሲሲ) አስታውቋል።

ከባድ ክሎስትሪዲየም ዲፊሲል ችግር ያለባቸው ታካሚዎች በዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት (ኤንኤችኤስ) በኩል ህክምናውን ማግኘት ይችላሉ። ክሎስትሪዲየም ዲፊሲል (ሲ.ዲፍ) ተቅማጥ ሊያስከትል የሚችል ጎጂ ባክቴሪያ ሲሆን፣ ብዙ ጊዜ አንቲባዮቲኮችን ለረጅም ጊዜ የተጠቀሙ ሰዎችን የሚያጠቃ እንደሆነ ይነገራል።

የ50 ሚሊ ሊትር ፈሳሽ የኤፍኤምቲ ናሙና የጤና አገልግሎቱን 684 ዶላር ያስወጣዋል። ይህ ዋጋ በተደጋጋሚ ለአንቲባዮቲክ እና ለሆስፒታል ህክምና ከሚወጣ ዋጋ አንጻር ያነሰ ነው ይላሉ ባለሙያዎች። አንዳንዴም ኤፍኤምቲ የሚሰጠው አንድ ጊዜ ብቻ ይሆናል።

አንዳንድ የህክምና ማዕከላትም በሰው ዐይነ ምድር ውስጥ ከሚገኙ ጤናማ ባክቴሪያዎች የተሠሩ በአፍ የሚወሰዱ እንክብሎችን ይሰጣሉ።

በዐይነ ምድሩ ይወስናል

አዲስ ጉበት፣ ኩላሊት ወይም ልብ በንቅለ ተከላ ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ተስማሚ ለጋሽ ለማግኘት ለወራት ወይም ለዓመታት ሊቆዩ ይችላሉ።

ከእነዚህ በጣም ከሚፈልጉ የአካል ክፍሎች በተለየ የሰው ዐይነ ምድር በብዛት ይገኛል። የሌላ ሰው ዐይነ ምድር ሐሳብ ለአንዳንድ ሰዎች ምቾት ላይሰጣቸው ይችላል።

እንግዳ ነገር ቢሆንም ሪክ በሳይንስን ይተማመናል። ሚስቱ እና ጓደኞቹም ጉዞውን ደግፈውታል።

“ምንም ሃፍረት ወይም ድንጋጤ የለውም። የሚሠራበት ዕድል ካለ ለምን አይሆንም? ከጓደኞቼ እና ከቤተሰብ ያገኘሁት ምላሽ ይህ ነው” ብሏል ሪክ።

የዐይነ ምድር ባንኮች

በበርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው ማይክሮባዮም የሕክምና ማዕከ

በበርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው ማይክሮባዮም የሕክምና ማዕከል (ኤምቲሲ) የዩናይትድ ኪንግደም የመጀመሪያው የሦስተኛ ወገን የኤፍኤምቲ አገልግሎት ሰጪ ሲሆን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ በሽተኞችን ለማከም እና የምርምር ሙከራዎችን ለማካሄድ ለክሊኒኮች የዐይነ ምድር ናሙናዎችን ያቀርባል።

በተቋሙ ውስጥ ለጋሾች ጥብቅ የሆነ የማጣሪያ ሂደቶች ውስጥ ያልፋሉ። ይህም ዝርዝር የሕክምና ታሪክን፣ የአኗኗር ዘይቤን እና በደማቸው እና ዐይነ ምድር ውስጥ ያሉ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን ምርመራዎችን ያካትታል።

በደንብ ከተጣራ በኋላ ጤናማ የዐይነ ምድር ናሙናዎች እስከ 12 ወራት ድረስ ከዜሮ በታች -80 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በሆነ ማቀዝቀዣ ውስጥ ይቀመጣሉ። አንድ ታካሚ የዐይነ ምድር ንቅለ ተከላ ሲፈልግ፣ ተጣርቶ የቀዘቀዘው ዐይነ ምድር መርፌ ውስጥ ይገባል።

የማይክሮባዮም ህክምና ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ታሪቅ ኢቅባል “የዐይነ ምድር ባንኮች በሌሉባቸው አገሮች ውስጥ በጣም ከባድ ቢሆንም ግን የቀዘቀዘ ኤፍኤምቲ መጠቀም በትክክል ለማጣራት ጊዜ ይሰጣል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የዐይነ ምድር ለጋሾች በተሳካ ሁኔታ በለገሱ የ10 ቀናት ውስጥ የ200 ፓውንድ የስጦታ ካርድ ያገኛሉ።

ኤፍኤምቲ በፒኤስሲ ውስጥ ያለው ሚና

የሕክምና መሳሪያ

ከሪክ ጋር ተመሳሳይ ሁኔታ ካጋጠማቸው ህመምተኞች መካከል ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆኑት ተጨማሪ የአንጀት በሽታ (አይቢዲ) እንደሚይዛቸው ያስጠነቅቃሉ። ይህም ከባድ የሆድ ድርቀት፣ ህመም እና ተቅማጥ ያስከትላል።

የሪክ ሙከራን የሚመሩት ዶክተር ፓላክ ትራይቬዲ ሳይንቲስቶች ለምን ፒኤስሲ እንደሚያዳብሩ ወይም ለምን ከአይቢዲ ጋር እንደተገናኘ አያውቁም ብለዋል።

“እኛ የምናደርገው ጤናማ የአንጀት ማይክሮባዮታ ወደ ፒኤስሲ ታማሚዎች አንጀት በማስተላለፍ የጉበት በሽታቸው ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ ማየት ነው” ሲሉ ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ያስረዳሉ።

የዐይነ ምድር ንቅለ ተከላ መመሪያዎች

በአሁኑ ጊዜ ይህ የመጀመሪያው የህክምና አማራጭ አይደለም ብለዋል የለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅ ባልደረባው ዶ/ር ሆራስ ዊልያምስ።

ዶ/ር ዊልያምስ እንደሚሉት ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ለከባድ ሲ.ዲፍ ታካሚዎች ብቻ ኤፍኤምቲ ይሰጣል እንጂ ለሁሉም አይደለም። በሌሎች ምክንያቶች ህክምናውን የሚሹ ታካሚዎች ሪክ እንዳደረገው ሁሉ ክሊኒካዊ ሙከራዎችን እንዲቀላቀሉ ጠቁመዋል።

በኢምፔሪያል ኮሌጅ የለንደን ጋስትሮኢንተሮሎጂስት እና የብሪቲሽ ጋስትሮኢንተሮሎጂ ሶሳይቲ የኤፍኤምቲ መመሪያዎች ዋና ፀሐፊ የሆኑት ዶ/ር ቤንጃሚን ሙሊሽ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ብዙ ሰዎች ዲአይዋይ ኤፍኤምቲ ሙከራ ለመሳተፍ መሞከራቸው አደገኛ ነው።

በደቡብ አፍሪካ በዊትዋተርስራንድ (ዊትስ) ዩኒቨርሲቲ የስቲቭ ቢኮ የባዮኤቲክስ ሴንተር ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ሃሪየት ኢቴሬጅ በበኩላቸው ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች እና ግልጽ መመሪያዎች በሌሉበት ኤፍኤምቲ ጎጂ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል። “የጤና ማዕከላት በስፋት በሌሉባቸው የድሃ አገሮች ውስጥ የከፋ ነው” ብለዋል።

ሕክምናው አልፎ አልፎም ሞት ሊያስከትል ይችላል።

ዐይነ ምድሩ የቤተሰብ ነው ወይስ የማያውቋቸው ሰዎች?

ታካሚ

ከአሜሪካ እና አውሮፓ በተጨማሪ ኤፍኤምቲ እንደብራዚል፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሕንድ ባሉ አገራት በሙከራ ደረጃ ተካሂዷል።

አንዳንድ ታማሚዎች በዐይነ ምድር ጥላቻ እንዲሁም በተለያዩ ባህላዊ፣ ማኅበራዊ እና ሃይማኖታዊ ምክንያቶች ህክምናውን ለመቀበል ፍቃደኛ አልነበሩም።

የሕንዱ የሰር ጋንጋ ራም ሆስፒታል ባልደረባው ዶ/ር ፒዩሽ ራንጃን “ሰዎች ለዚህ ሕክምና አንዳንድ ጊዜ በጣም መጥፎ ምላሽ ይሰጣሉ” ብለዋል።

ዶክተር ራንጃን ከራሳቸው ልምድ በመነሳትም አንዳንድ ታካሚዎች ምንም እንኳን ምርመራ ተደርጎ የሚሰጥ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ከማያውቁት ሰው ይልቅ የዘመዶቻቸው ዐይነ ምድርን መቀበል ይመርጣሉ።

በተቃራኒው ደግሞ የኮርን እና የኮሊቲስ ዩኬ ከ200 የሚበልጡ ሰዎች ላይ ባደረገው የሕዝብ አስተያየት ከሚያውቁት ሰው ይልቅ ከማይታወቅ ሰው የተገኘን ዐይነ ምድር መርጠዋል።

መጀመሪያ ላይ 37 በመቶዎቹ ሰዎች የዐይነ ምድር ንቅለ ተከላውን እንደማይቀበሉ ቢገልጹም ስለ ሂደቱ የበለጠ ከተማሩ በኋላ ይህ አሃዝ ወደ 54 በመቶ ከፍ ብሏል።

ጥናቱን ያካሄዱት ዶክተር ብሬት ፓልመር “ትምህርት ሁሌም ብዙ መሰናክሎችን ያፈርሳል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሪክ ምርምሩ ለህመሙ ፈውስ እንደሚያስገኝለት ተስፋ አድርገዋል።

“ከ10 ዓመት በፊት የሰዉ ዐይነ ምድር የጤና በሽታ እንደሚያክም ቢነገረኝ በፍጹም አላምንም ነበር” ብለዋል። አሁን ግን ዕውን ሆኖ እያዩት ነው።