ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ
የምስሉ መግለጫ,ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ

ከ 6 ሰአት በፊት

የቬንዙዌላ ባለሥልጣናት የአገሪቱን ሰላም ለማናጋት በማሴር ጠረጠርናቸው ያሏቸውን ሦስት የአሜሪካ፣ ሁለት የስፔን እና አንድ የቼክ ዜጎችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን አስታወቁ።

የቬንዙዌላ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ግለሰቦቹ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ እና ሌሎች ባለሥልጣናትን ለመግደል ሲያሴሩ እንደነበር እና በመቶዎች የሚቆጠሩ የጦር መሳሪያዎችም አብረው መያዛቸውን ገልጸዋል።

ይህ ዜና የተሰማው በአገሪቱ የተካሄደውን አወዛጋቢ ምርጫ ፕሬዝዳንት ማዱሮ ማሸነፋቸውን ተከትሎ አሜሪካ በ16 የፕሬዝዳንቱ አጋሮች ላይ ማዕቀብ መጣሏን ካሳወቀች ከሁለት ቀናት በኋላ ነው።

የቬንዙዌላ መንግሥት በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል የሚገኙት የስፔን ዜጎች ከአገራቸው የስለላ ተቋም ጋር ግንኙነት አላቸው ቢሉም፣ የስፔን መንግሥት ምንጮች ይህንን ክስ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት አስተያየት አስተባብለዋል።

የቬንዙዌላው የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቅዳሜ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የግለሰቦቹን ተልዕኮ የአሜሪካው የስላለ ድርጅት ሲአይኤ እየመራው ነበር ብለዋል።

አክለውም የተያዙት ሰዎች “ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን፣ ምክትላቸውን ዴልሲ ሮድሪጌዝ፣ እኔን እና ሌሎችም ፓርቲያችንን እና አብዮታችንን እየመሩ ያሉ ጓዶችን ለመግደል ግልጽ ዓላማ ይዘው ቅጥረኞችን ወደ አገሪቱ ለማስገባት እየሠሩ እንደነበር አምነዋል” ብለዋል።

አሜሪካ የቀረበውን ክስ በተመለከተ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ በሰጠው ምላሽ “ማዱሮን በማስወገድ ሴራ ውስጥ አሜሪካ ተሳትፋለች መባሉ ፍጹም ሐሰት ነው” በማለት ውድቅ አድርጋ በቬንዙዌላ ያለው ፖለቲካዊ ቀውስ ዴሞክራሲያዊ መፍትሄ እዲያገኝ መደገፏን እንደምትቀጥል ገልጿል።

ይህ ክስ እና እስር የተሰማው የቬንዙዌላ መንግሥት ከአሜሪካ እና ከስፔን መንግሥታት ጋር ውዝግብ ውስጥ ባለበት ወቅት ነው።

የቬንዙዌላ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ለመገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት ግለሰቦቹ “አገራችን ላይ ጥቃት ለመፈጸም በፈረንሳይ እና በምሥራቅ አውሮፓ ከሚገኙ ቅጥረኞች ጋር ሲገናኙ ነበር” በማለት 400 የጦር መሳሪያዎችም እንደተያዘባቸው አመልክተዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል ለቀናት ከዘለቀ ፍጥጫ በኋላ ባለፈው አርብ የቬንዙዌላው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዋና ከተማቸው ካራካስ የሚገኙትን የስፔን አምባሳደርን በመጥራት በስፔን በኩል የቬንዙዌላን መንግሥት አምባገነን በሚል የተገለጸበትን መንገድ በተመለከተ ያላቸውን ተቃውሞ ገልጸዋል።

ሐሙስ ዕለት ደግሞ የአሜሪካ ግምጃ ቤት (ገንዘብ ሚኒስቴር) “ኒኮላስ ማዱሮ አሸናፊ ሆነውበታል በተባለው የተጭበረበረ እና ሕገወጥ በሆነው ምርጫ እንዲሁም ምርጫውን ተከትሎ ሃሳብን በመግለጽ ነጻነት ላይ በተወሰደ እርምጃ ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው” ባለሥልጣናትን ዒላማ ያደረገ ማዕቀብ ጥሏል።

ኒኮላስ ማዱሮ ባለፈው ሐምሌ የተካሄደውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸውን ለአገሪቱ መንግሥት ቅርበት ያለው የቬንዙዌላ ብሔራዊ የምርጫ ምክር ቤት ማወጁ ይታወሳል።

ነገር ግን ምክር ቤቱ የኒኮላስ ማዱሮን አሸናፊነት የሚደግፉ የድምጽ አሰጣጥ እና አሃዞችን የሚመለከቱ ዝርዝር መረጃዎችን ይፋ አላደረገም። በምርጫው ተፎካካሪ የነበረው ተቃዋሚው ፓርቲ ያወጣው መረጃ ዕጩው ኤድሙንዶ ጎንዛሌዝ አወዛጋቢውን ምርጫ እንዳሸነፉ አመልክቷል።