ፕሬዝዳንት ኢሳያስ እና የግብፅ ባለሥልጣናት

ከ 7 ሰአት በፊት

የግብፅ የስለላ አገልግሎት ኃላፊ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአሥመራ ተገኝተው የፕሬዝዳንት አል ሲሲን መልዕክት ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ በማድረስ ውይይት ማድረጋቸው ተዘገበ።

የግብፅ ጠቅላላ የስለላ አገልግሎት ኃላፊ አባስ ካሜል እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ባድር አብደልላቲ በቀጣናው ያለውን ወቅታዊ የደኅንነት እና የፖለቲካ ሁኔታ፣ እንዲሁም የአገራቱን ግንኙነት ማጠናከረን የሚመለከት መልዕክትን ለኤርትራው ፕሬዝዳንት ማድረሳቸው ተገልጿል።

የከፍተኛ ባለሥልጣናቱን የአሥመራ ጉብኝት በተመለከተ ከግብፅ የወጣው መግለጫ እንዳለው መልዕክተኞቹ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ጋር ባደረጉት ውይይት በቀይ ባሕር ላይ ስለሚካሄደው የባሕር ላይ እንቅስቃሴ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ደኅንነት እና መረጋጋት ዙሪያ ተወያይተዋል።

የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል በኤክስ ገጻቸው ላይ የግብፅ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ቅዳሜ መስከረም 4/2017 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር በመገናኘት በሁለትዮሽ እና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ሁለቱ ወገኖች “በጋራ በሚመለከቷቸው ቀጣናዊ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ በተለይም በሱዳን፣ በሶማሊያ እና በቀይ ባሕር አካባቢ እየተዩ ባሉ ወቅታዊ ክስተቶች ላይ በጥልቀት” መወያየታቸውን የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር አመልክተዋል።

ከግብፅ በኩል በወጣው መግለጫ ላይም የኤርትራው ፕሬዝዳንት ለልዑካን ቡድኑ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ እየተከሰተ ያለውን ሁኔታ እና ቀጣናው አጋጥሞታል ያሉትን ተግዳሮቶች እንዲሁም የአካባቢውን ደኅንነት እና መረጋጋት ለማጠናከር ስለሚቻልባቸው መንገዶች ማብራሪያ ሰጥተዋል ብሏል።

ሁለቱም ወገኖች በሱዳን መረጋጋት እንዲመጣ እንዲሁም የሶማሊያ አጠቃላይ የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት እንዲጠበቅ ድጋፋቸውን ማጠናከር እንደሚያስፈለግ መስማማታቸው ተገልጿል።

የግብፅ የስለላ እና የውጭ ጉዳይ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በኤርትራ ጉብኝት ያካሄዱት በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ ግብፅ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ጦሯን ወደ ሶማሊያ ለማስገባት የመጀመሪያ እንቅስቃሴ ማድረጓን ተከትሎ ተቃውሞ ከገጠማት በኋላ ነው።

ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ወር ላይ ከሶማሊያ የተለየች ነጻ አገር መሆኗን ያወጀችው ሶማሊላንድ የአገርነት እውቅናን የሚያስገኝ እና ኢትዮጵያ የባሕር መተላላፊያ ለማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሰነድ ከተፈረመ በኋላ በአፍሪካ ቀንድ ውዝግብ መከሰቱ ይታወቃል።

ይህንንም ተከትሎ ከሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ለዓመታት እየተወዛገበች ያለቻውን ኢትዮጵያን በመቀወም ግብፅ ሶማሊያን በይፋ ደግፋ የቆመች ሲሆን፣ ኤርትራም የሶማሊያውን ፕሬዝዳንት በተደጋጋሚ በማስተናገድ ከሶማሊያ ጎን ቆማለች።

ግብፅ እና ሶማሊያ ከአንድ ወር በፊት የወታደራዊ ትብብር ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን፣ ከሳምንታት በፊት የጦር መኮንኖችን እና ወታደራዊ አቅርቦቶች የጫኑ ሁለት አውሮፕላኖች ሞቃዲሾ መግባታቸው እንዲሁም ግብጽ ወታደሮቿን በሶማሊያ ለማሰማራት መዘጋጀቷ ኢትዮጵያን አስቆጥቷል።

ይህ የግብፅ እርምጃ በቀጣናው ያሉውን የፀጥታ ሁኔታ የሚያበላሽ ጣልቃ ገብነት ነው በማለት ኢትዮጵያ የተቃወመች ሲሆን፣ የሶማሊያ ፌደራላዊ ግዛቶች እና የአገሪቱ ምክር ቤት አባላትም ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

የግብፅ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የፕሬዝዳንት አል ሲሲሰን መልዕክት አሥመራ ተገኝተው ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ ባቀረቡበት እና በተወያዩበት ጊዜ ለሶማሊያ ያላቸውን ድጋፍ የገለጹ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ አንጻር ግን ስላነሱት ጉዳይ የተባለ ነገር የለም።

የግብፅ ልዑካን ጉብኝትን በተመለከተ በኤክስ ገጻቸው ላይ መልዕክት ያሰፈሩት የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል “ግብፅ በአፍሪካ ቀንድ አለመረጋጋት የመፍጠር እና የጣልቃ ገብነት አጀንዳ ታራምዳለች” የሚለው ክስ አንዳንድ ወገኖች “ለስህተታቸው ማሳበቢያ ባዶ ክስ ነው” መሆኑን በውይይቱ ወቅት መነሳቱን ጠቅሰዋል።

ይህም በዋናነት ግብፅ በሶማሊያ ውስጥ እያደረገችው ያለው እንቅስቃሴ በይፋ የተቸችውን ኢትዮጵያን የሚመለከት እንደሆነ ይታመናል።

ወትሮውንም በውዝግብ ውስጥ ለዓመታት የቆየው የግብፅ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ከሳምንታት በፊት ሁለቱም አገራት ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት በጻፉት ደብዳቤ መካሰሳቸው ይታወሳል።