ሎራ ሉመር

ከ 5 ሰአት በፊት

ቀኝ ዘመም፣ ወግ አጥባቂ የሴራ ትንታኔ አራማጅ ናት። ከሰሞኑ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጎን አትጠፋም።

ይህ ጉዳይ አንዳንዶችን ያሳሰበ ሆኗል። የተወሰኑ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላትም በዚህ ደስተኛ አይመስሉም።

ሎራ ሉመር የምትታወቀው ፀረ-ሙስሊም የሆነ አቋሞችን በማንፀባረቅ ነው። ማስረጃ የሌላቸው የሴራ ትንታኔዎችንም ታስፋፋለች። በተለይ ደግሞ የመስረም 11/2001 የሽብር ጥቃት የተፈፀመው “በአሜሪካ መንግሥት” ነው ስትል በልበ-ሙሉነት ትናገራለች።

ባለፈው ሳምንት ትራምፕ ለ9/11 ዝክር በተዘጋጀ አንድ ፕሮግራም ላይ ሲገኙ እሷ ካጠገባቸው ነበረች። ይህ አንዳንዶች በጥርጣሬ እንዲያይዋት ያደረገ ክስተት ነው። የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ደግሞ ይህ እንዴት ይሆናል? ሲሉ ቁጣቸውን ገልፀዋል።

ይህ ብቻም አይደለም የ31 ዓመቷ ሉመር ባለፈው ሳምንት የነበረውን የዕጩ ፕሬዝዳንቶች የቴሌቪዥን ክርክርን ለመታደም በትራምፕ አውሮፕላን ነው ወደ ፊላደልፊያ ያቀናችው።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና የወቅቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሀሪስ በነበራቸው ሙግት ላይ መነጋገሪያ የነበረው ትራምፕ ከሄይቲ የመጡ ሕገ-ወጥ ስደተኞች “ድመት እና ውሻ ሳይቀራቸው የቤት እንስሳትን እየበሉ ነው” ያሉበት ቅፅበት ነበር።

ድመት እና ውሻዎቿ ስጋት ላይ ናቸው የተበላሉት የኦሀዮ ግዛቷ የስፕሪንግፊልድ ከተማ ባለሥልጣናት “ይህን የሚያረጋግጥ ማስረጃ የለም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ትራምፕ ይህን ያልኩት ከቴሌቪዥን መስኮት ባገኘሁት መረጃ ነው ይላሉ። ምክትል ፕሬዝዳንታቸው ሆነው የሚወዳደሩት ጄዲ ቫንስም ይህንን ደግመዋል።

በኤክስ የማኅበራዊ ገጿ 1.2 ሚሊዮን ተከታዮቿ ያላት ሉመር ናት ለመጀመሪያ ጊዜ ይህን ሐሳብ ያሰራጨችው።

ሴትየዋ ከትራምፕ ጋር ያላት ግንኙነት ግልፅ ባይሆንም የቀድሞው ፕሬዝዳንት ይህን ሐሳብ በምርጫ ክርክራቸው ላይ እንዲያነሱ የገፋፋቻቸው እሷ ናት የሚል ቅሬታ እየቀረበባት ይገኛል።

ለትራምፕ ቅርብ የሆኑ ምንጮች እንደሚሉት ሉመር ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ያላት ቅርበት ብዙዎችን እያሳሰበ ነው።

ነባር የሚባሉ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላትም ትራምፕ ግለሰቧን ብዙም ባይቀርቧት መልካም ነው የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ቶም ቲሊስ የተባሉት የኖርዝ ካሮላይና ሴናተር “ሎራ ሉመር የተባለች የሴራ ትንተና አራማጅ በሪፐብሊካን ፓርቲ ውስጥ ክፍፍል ለመፍጠር የተላከች እብድ ሴት ናት” ሲሉ ወቅሰዋል።

አርብ ዕለት ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ትራምፕ ሎራ ማለት “ደጋፊ ናት” ብለው በቅርቡ ካማላ ሀሪስን እና የ9/11 የሽብር ጥቃትን በተመለከተ ስለሰጠችው አስተያየት ምንም እንደማያውቁ ተናግረዋል።

“አኔ ሎራን አልቆጣጠራትም። የፈለግችው የመናገር መብት አላት። ነፃ መንፈስ ያላት ሰው ናት” ብለዋል።

ሎራ ሉመር ከቢቢሲ በተደጋጋሚ ለቀረበላት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠችም።

ነገር ግን በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ገጿ “ራሷን ችላ እንደምትንቀሳቀስ” እና “የአገራችን የመጨረሻው ተስፋ” የምትላቸው ትራምፕን ለማገዝ እንደምትሰራ ፅፋለች።

“በየጊዜው እናናግርሽ እያላችሁ ለምትፅፉልኝ ጋዜጠኞች ምላሼ አይሆንም የሚል ነው። እኔ የራሴን የምርመራ ሥራ በመሥራት ጊዜ ያጠረኝ ሰው ነኝ። ለእናንተ የሴራ ፅንሰ ሐሳብ ጊዜ የለኝም” ብላለች።

ዶናልድ ትራምፕ

በአውሮፓውያኑ 1993 በአሪዞና ግዛት የተወለደችው ሎራ በግሏ የምትንቀሳቀስ የምርመራ ጋዜጠኛ ስትሆን፣ ለተለያዩ ድርጅቶች ‘አክቲቪስት’ እና ሐሳብ ሰጪ በመሆን ሠርታለች።

በ2020 የአሜሪካ ምርጫ የሪፐብሊካን ፓርቲ የፍሎሪዳ ግዛት የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ተወካይ ለመሆን በትራምፕ ድጋፍ ያደረገችው ጥረት ሳይሳካላት ቀርቷል።

በ2022 በድጋሚ በፍሎሪዳ ግዛት በተደረገ ቅድመ ምርጫ ተሳትፋ በቂ ድምፅ ሳታገኝ ቀርታለች።

አሁን በምታስተላልፋቸው ያልተጨበጡ የሴራ ፅንሰ-ሐሳቦች ታዋቂነቷ እየጨመረ መጥቷል። ካማላ ሀሪስ ጥቁር አይደለችም፤ የቢሊየነሩ ጆርጅ ሶሮስ ልጅ ትራምፕ እንዲገደሉ ምሥጢራዊ መልዕክት አስተላልፏል እና ሌሎችም ፅንሰ-ሐሳቦችን ታራምዳለች።

በእነዚህ መልዕክቶች ምክንያት ከፌስቡክ እና ከኢንስታግራም የታገደች ሲሆን፣ ስለሙስሊም አሽከርካሪዎች በሰጠችው አስተያየት ደግሞ ኡበር እና ሊፍት ከተሰኙት የታክሲ መተበግሪያዎች መታገዷን ተናግራለች። ራሷን “ኩሩ እስላም ጠል” በማለት ነው የምትገልፀው።

ሎራ ሉመር የቀድሞው ፕሬዝዳንት በሚያደርጓቸው የተለያዩ የምርጫ ቅስቀሳዎች ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ የትራምፕ መኖሪያ የሆነው ማር-አ-ላጎ የተሰኘው ቅንጡ ግቢ ውስጥም ታይታለች።

ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ባለፈው ዓመት ባወጣው ዘገባው ዶናልድ ትራምፕ ሴትየዋን የምርጫ ቅስቀሳ ኃላፊያቸው አድርገው ለመሾም አቅደው ከረዳቶቻቸው ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር ይላል።

ሎራ የሕንድ ደም ያለባቸው ሀሪስ ዋይት ሐውስ የሚገቡ ከሆነ “የከሪ ጠረን ይኖረዋል” ስትል አስተያየት ሰጥታለች። ከሪ ተወዳጅ የሕንድ ምግብ ሲሆን፣ በዚህ አስተያየቷ ከብዙዎች ትችት ቀርቦባታል።

የትራምፕ ደጋፊ የሆኑት ታዋቂዋ እንደራሴ ማርጆሪ ቴይለር ግሪን፣ የሎራ አስተያየት “ዘረኛ እና የሪፐብሊካን ፓርቲንም ይሁን የትራምፕን ቡድን የማይወክል ነው” ብለዋል።