በልውውጡ ከተለቀቁት ምርኮኞች መካከል አንዱ የሆነው የዩክሬን ወታደር
የምስሉ መግለጫ,በልውውጡ ከተለቀቁት ምርኮኞች መካከል አንዱ የሆነው የዩክሬን ወታደር

ከ 5 ሰአት በፊት

ከሁለት ዓመት በላይ በከባድ ጦርነት ውስጥ የሚገኙት ሩሲያ እና ዩክሬን በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አቀራራቢነት ከሁለት መቶ በላይ ምርኮኞችን ተለዋወጡ።

በሁለቱ ተፈላሚ አገራት መካከል የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር እንዳሳወቀው፣ ዩክሬን በቅርቡ በሩሲያ ኩርስክ ግዛት ላይ ባካሄደችው ወረራ የተማረኩ ወታደሮችን ጨምሮ 103 ዩክሬናውያንን ለቃለች።

በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል እየተደረገ ባለው ጦርነት የዓለም አገራት ጎራ ለይተው ከአንደኛው አገር ጎን የቆሙ ሲሆን፣ የምርኮኞች ልውውጥ እንዲደረግ ያመቻቸችው የባሕረ ሰላጤ አገር የሆነችው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ናት።

በሁለቱ አገራት መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት በሁለቱም ዘንድ የገለልተኝነት ዕምነትን ያገኘችው ኤምሬትስ፣ ከዚህ በፊትም የምርኮኞች ልውውጥ እንዲደረግ አመቻችታለች።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ቅዳሜ ዕለት ከምርኮ የተመለሱትን ወታደሮች ፎቶዎችን አያይዘው “ወታደሮቻቻን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል” የሚል መልዕክት አጋርተዋል።

ባለፈው ነሐሴ ወር የዩክሬን ኃይሎች ድንገተኛ ጥቃት ፈጽመው የሩሲያን ድንበር ጥሰው በመግባት ኩርስክ በተባለችው ግዛት ውስጥ 30 ኪሎሜትሮችን ዘልቀው ገብተዋል።

ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ እንዳስታወቁት ምርኮኞች ልውውጡ ከተለቀቁት ዩክሬናውያን ወታደሮች መካከል 82 ተራ ወታደሮች እና 21 መኮንኖች የሚገኙበት ሲሆን፣ በተለያዩ የአገሪቱ የጦር ክፍሎች አባላት የነበሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ዜሌንስኪ ጨምረውም ወታደሮቹ ዋና ከተማዋን ኪየቭን፣ ዶኔትስክን፣ ማሪዩፖልን፣ አዞቭስታልን፣ ዛፖሪዢያ እና ኻርኪቭን ከሩሲያ ወረራ ለመከላከል በተደረጉት ውጊያዎች ላይ መማረካቸውን ገልጸዋል።

ሩሲያ በበኩሏ የተማረኩባት ወታደሮቿ መለቀቃቸውን አረጋግጣ በጎረቤት ቤላሩስ ውስጥ እንደሚገኙ አሳውቃለች። ወታደሮቹ “አስፈላጊው ሥነ ልቦናዊ እና የህክምና ድጋፍ” ከተደረገላቸው በኋላ ወደ ሩሲያ ከመመለሳቸው በፊት ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ እንደሚያደረግ ተገልጿል።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ዩክሬን በሩሲያ ግዛት ከፈጸመችው ድንገተኛ ወረራ በኋላ በተካሄደው የምርኮኞች ልውውጥ እስካሁን በአጠቃላይ የ230 ምርኮኞች ርክክብ ተካሂዷል።

ዩክሬን በሩሲያ ኩርክስ ግዛት የፈጸመችው ወረራ ዓላማ ያደረገው የሩሲያ ኃይሎች በምሥራቃዊ ዩክሬን የሚያካሂዱትን ዘመቻ በመግታት ትኩረታቸውን ለመከፋፈል ነበር።

የአሁኑ የምርኮኞች ልውውጥ የተካሄደው ዩክሬን በሩሲያ ግዛት ውስጥ ዘልቃ በመግባት በርካታ ቦታዎችን የያዘችበት ጥቃትን በመቀልበስ ይዞታዋን ማስመለሷን ሩሲያ ካሳወቀች በኋላ ነው።

የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር ቅዳሜ ዕለት እንዳሳወቀው በዩክሬን ኃይሎች ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን መልሶ መቆጣጠሩን እና ለወታደራዊ እንቅስቃሴ ወሳኝ የተባሉ መንደሮችን እና ተቋማትን ከሳምንታት በኋላ በእጁ ማስገባቱን አሳውቋል።