September 15, 2024 – Konjit Sitotaw 

ልማት የሰውን ልጅ ሲያፈርስ በዓይኔ አየሁት!

የልማት ተነሺ ተብሎ ሰዎች ድንገት ቤታቸው ሲፈርስ ስለገጠማቸው ጉዳት ብዙ የሚያሳዝኑ ታሪኮች ሲነገሩ ሰምቻለሁ። ነገሩ ቢያሳዝነኝም፣ የስሚ ስሚ አይቼ ሳልመረምር አስተያየት ብሰጥ ሚዛናዊ አልሆን ይሆናል፣ እሳሳት ይሆናል በሚል ከማዘን በስተቀር ምንም አላልኩም ነበር፣ አሁን ግን ለልማት ድንገት መፍረስ የሰውን ልጅ ሲያፈርስ በዓይኔ አየሁት።

የማወራው ስለአንድ ሰው ታሪክ ነው፣ ተቆጥሮ ህዝብ ስለሚባለው፣ ሀገር በማቅናት ውስጥ ማህበረሰብ በመስራት ውስጥ አስተዋጽኦ ስላለው አንድ ሰው ነው።

የህይወት ታሪኩ እንዲህ ነው …

ገና ጎረምሳ እያለ ከተወለደበት ገጠር ወጥቶ 250 ኪሎሜትር በእግሩ ተጉዞ አዲስ አበባ ገባ። አዲስ አበባ የግለሰቦች ንግድ ቤት ተቀጥሮ ከጽዳት አንስቶ የተለያዩ ስራዎችን ሰርቶ ከራሱ አልፎ ወላጆቹን ቤተሰቡን ረድቶ፣ ትዳር መስርቶ፣ ልጆች አፍርቶ፣ የግል ንግድ ከፍቶ ሲኖር ቆይቶ የዛሬ 60 ዓመት አካባቢ ከፈረንሳይ ኢምባሲ ወረድ ብሎ ከሃይዌዩ ድልድይ ስር የግንብ ግድግዳ ላይ “ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ” የሚለው ጽሁፍ በደማቁ በቀይ ቀለም ከተጻፈበት ፊትለፊት ወደ ቤላ በሚወስደው ቀኝ መታጠፊያ መንገድ ላይ መሬት ገዝቶ ቆንጆ ቤት ሰርቶ ኑሮውን መሰረተ።

12 ልጆችን አሳድጎ፣ አስተምሮ ለወግ ለመዓረግ አበቃ፣ የልጅ ልጅ አየ። አሁን የ 94 ዓመት አዛውንት ነው። ጠንካራ፣ ደግ፣ ሰራተኛ፣ ተጫዋች፣ ቀልድ አዋቂ፣ ሰው ሁሉ የሚወደው፣ ሰውን ሁሉ የሚወድ፣ ሃይማኖቱን አክባሪ እምነቱን አጥባቂ ነው። የግቢ አትክልት ይወዳል፣ ግቢው በወይን፣ በአቩካዶ፣ በኮክ፣ በአፕል፣ በቡና ዛፍ የተሞላ የሚያምር ግቢ ነው። የአትክልት ፍቅሩ ለራሱ ቤት ብቻም አይደለም፤ ሰፈር ውስጥ እየዞረ በሰው ቤት በዘመድ ቤትም ችግኝ ከቤቱ እየወሰደ ይተክላል።

ይህ ጠንካራ ሰው በቅርቡ በህመም አልጋ ላይ ዋለ ፥ “በቂ ኖሬያለሁ ሆስፒታል እንዳትወስዱኝ በኖርኩበት ባረጀሁበት ቤት አስከሬኔ ይውጣ” አለ። ልጆቹ ቃሉን አከበሩለት ቤቱ ውስጥ እንዳለ ሀኪም እያየው በልጆቹ፣ በልጅ ልጆቹ በቤተዘመድ በጎረቤት ተከቦ እንዲያስታመሙት አደረጉ። ጳጉሜ 5 ቀን 2016 ዓ.ም የ አዲስ ዓመት ዋዜማ በሰፈሩ አንድ ዜና ተሰማ፣ ከወረዳ የመጡ ሰዎች እየዞሩ ለልማት እየመዘገቡ ነው የሚል።

የአዲስ ዓመት በዓል ማግስት መስከረም 2 መጥተው በ20 ቀን ውስጥ ቤታችሁ ለልማት ሊፈርስ ስለሆነ ለመስከረም 3 ጠዋት ለስበሰባ ኑ የሚል መልእክት በቃል ብቻ ተነገረ። እንዲህ ያለ ዱብ እዳ ሲሰማ ለህግ ጉዳይ መዋሉ ቢቀር እንኳን ህልም ይሆን እንዴ ብሎ ድጋሚ አይቶ ለማረጋገጥ የሚያስችል ብጣቂ ወረቀት አልተሰጠም፣ ልክ እንደ ክፉ መርዶ ነጋሪ በር አንኳኩተው በቃል ትዕዛዝ ሰጥተው ሄዱ።

መስከረም 3 በስብሰባው ላይ ስልክም ሆነ ማንኛውም ድምጽ እና ምስል መቅጃ ይዞ መግባት ባልተፈቀደበት ስብሰባ ላይ ለተሰብሳቢዎቹ ቤታችሁ ለልማት ይፈርሳል የሚለው መርዶ ተነገራቸው።

ለምን?

ለጫካ ፕሮጀክት ልማት።

መቼ?

እስከ መስከረም 20።

ተሰብሳቢው ደነገጠ “ልጆቻችንን ትምህርት ቤት አስመዝገበናል፣ ዩኒፎርም አሰፍተናል፣ የደከመ ታማሚ ቤታችን ስላለ ጊዜው አይበቃንም፣ የእለት ጉርሴ ከቤት ኪራይ የማገኘው ብቻ ነው፣ ምን ልሁን? የሚሉ አዛውንቶች፣ እናቶች፣ አባቶች፣ ጮኸው አልቅሰው ተናገሩ። ሁለት ሳምንት አላችሁ ተባሉ።

ሁለት ሳምንት ለምን ይበቃል??

በየቤቱ ያለ እቅድ ፥ ያለ ኑሮ… ለቅሶ፣ ጽኑ ታማሚ፣ ሰርግ፣ አራስ፣ የደረሰች ነፍሰጡር….ቤቱ ይቁጠረው ሁለት ሳምንት ለምን ይበቃል? ምንድነው ጥድፍድፉ? ልማት ታስቦ እንደሆነም እኮ በረጅም ጊዜ እቅድ ላይ በመጀመሪያው ረድፍ ላይ ሊቀመጥ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ሰው ነው።

ነዋሪው እንዴት ይነሳ? ወዴት ይሂድ የሚለው እንጂ ትግበራ ከተጀመረ በኋላ በመጨረሻው ሰዓት ለነዋሪው በቀናት ውስጥ ትነሳለህ ብሎ በቃል መንገር እንዴት? ሰው ያነሰ ቅድሚያ ነው የሚሰጠው? ልማቱ ለሰው ነው አይደል??

ይህ ቤተሰብ የመራ፣ ሀገር ያቀና፣ ስንቱን ያስተማረ፣ የዳረ፣ አስታሞ በክብር የቀበረ፣ የተጣላን አስታራቂ የሐገር ሽማግሌ፣ አልጋ የያዘ መንቀሳቀስ፣ መንቃት የማይችል፣ ፈጣሪው ጋ እስኪሄድ ቀኑን የሚጠብቅ አረጋዊ እስከ መስከረም 20 ይነሳ ቤቱ ይፈርሳል ተባለ።

እንዴት ይሄድ? የት ይሂድ? በኖረበት ሰፈር ባቋቋምው እድር፣ በሚወደው አብሮ በኖረው የሰፈር ሰው ላይሸኝ? የሀገር ትርጉም ሲነገር “አባት የሞተ እንደሁ በሀገር ይለቀሳል” አልተባለም ነበር እንዴ? እና ለአባት የሚለቅሰበት፣ ለቅሶ የሚቀመጡበት ሀገር የለም??

ልማት ማንም አይጠላም ፣ ማማር ፣ መታደስ ማንም አይጠላም። የሰው ልጅን ግራ ሲያጋባ ለድንገተኛ ስጋት ሲዳርግ፣ ሰው ሁሉ የኔስ ተራ መቼ ይሆን እያለ በጭንቀት እንዲኖር ሲገደድ፣ ክብርን ሲነካ፣ ሰውነትን ሲያፈርስ ግን አዎን ልማት ይጠላል!!

ይሄን ጽሁፍ የምታዩ የልማት ደጋፊ ነን ባዮች ኮመንት ላይ መጥታችሁ፣ “እና ሃገር አይልማ? ሀገር ሲለማ አይናችሁ የሚቀላ፣ የልማት አደናቃፊዎች” ትሉ ይሆናል። እውነቱ ግን የልማት አደናቃፊ እናንተ ናችሁ።

እንደግፈዋለን የምትሉት ልማት በሰዎች እንዲጠላ፣ ሰው እንዲያለቅስበት፣ የምትታትሩ ዛሬን እና ሆዳችሁን ብቻ የምታዩ፣ ከሆዳችሁ ውጪ ሌላ ነገር የመደገፍ አቅም የሌላችሁ ሰባራ ሸንበቆዎች የልማት ጠላቶቹ ናችሁ።

ድንገት እንደ ሱናሜ አደጋ ቤታችሁ የፈረሰባችሁ ወገኖቼ፡ እስቲ ተናገሩት እንዴት ሆናችሁ? እንዴት አለፋችሁት?

እስቲ እውነተኛ ታሪካችሁን፣ ስሜታችሁን፣ ትኩስ ትዝታችሁን አጋሩን ታሪክ ይጻፍ ለሚመለከተው አካልም ሰውን ሳያፈርስ፣ ቤት አላልኩም ሰውን ሳያፈርስ ሰዉም ተቀብሎት ሊሰራ እንደሚችል ትክክለኛ ጥቆማ እና ድጋፍ ይሁነው።

✍️ Azeb Worku