September 15, 2024 – Konjit Sitotaw 

ፐርፐዝ ብላክ ከሲዳማ ክልል አርሶ አደሮች የ ‘ሼር’ ገንዘብ ካለ ደረሰኝ ሰብስቦ እንደነበር ታወቀ

(መሠረት ሚድያ)- ፐርፐዝ ብላክ በሲዳማ ክልል የሚገኙ አርሶ አደሮችን “ምርቶቻችሁን እቀበላለሁ፣ መጀመርያ ግን ሼር ግዙ” በማለት ከበርካታዎቹ ገንዘብ ሲሰበስብ እንደነበር ታውቋል።

በክልሉ የተለያዩ ዞኖች፣ ወረዳዎች፣ ክፍለ ከተማዎች እና ቀበሌዎች እስከታች ድረስ በመወረድ ለአርሶ አደሮች ድጋፍ አደርጋለሁ እና ምርቶቻችሁን እቀበላለሁ በማለት በሁሉም ቦታ የራሱ የሆኑ ሰራተኞችን በኮንትራት ቀጥሮ ያሰራ እንደነበርም ታውቋል።

“እነዚህ ሰራተኞች በተሰጣቸው ተልእኮ መሰረት ወደ አርሶ አደሩ ቀርበው ከእኛ ጋር ለመስራት በመጀመርያ የአክስዮን አባል ሁኑ ብለውን በርካቶቻችን ያለንን ገንዘብ ሰጥተናል” ብለው ቃላቸውን ለመሠረት ሚድያ የሰጡት እነዚህ ዜጎች መንግስት መፍትሄ ይስጠን ብለዋል።

“በሲዳማ ክልል በደቡባዊ ዞን ዳራ ወረዳ ውስጥ ብቻ በተለያዩ ቀበሌዎች አትክልት፣ ቡና፣ ፍራፍሬ፣ እና ስንዴ አምርቱና እንቀበላለን ብለው ስለ አክስዮን ምንነት ለይቶ ከማያውቁ ሰዎች ጭምር የእኛ አክስዮን አባል ከሆኑ አዲስ አበባ እያስገነባን ካለው ግዙፍ ሕንጻ ባለቤት ይሆናሉ ብለውን ነበር” ያሉት አንድ አርሶ አደር ናቸው።

ሌላኛው ጠቋሚ ደግሞ “የአንድ አክስዮን ዋጋ ከነ ምዝገባዉ ጭምር 1,050 ብር ብለውን ነበር። ሕዝቡ እስከ ሶስት እጣ (ሼር) የወሰደ አለ፣ ከዚህ ውስጥ ከወረዳችን ደረሰኝ እጅ በእጅ የተቀበሉት እኔ የማውቃቸው አንድ ግለሰብ ብቻ ናቸው፣ ለሌሎቹ ምንም የተሰጠ ደረሰኝ የለም” ብለው ገንዘብ ያለ ደረሰኝ ጭምር ሲሰበሰብ እንደነበር ተናግረዋል።

የፐርፐዝ ብላክ አካውንት በመግስት ታግዶ አንዳንድ አመራሮቹ ደግሞ በቅርቡ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ይታወሳል።