ቡና የምትጠጣ ሴት

ከ 5 ሰአት በፊት

በመላው ዓለም ተወዳጅ የሆነው የቡና ዋጋ ባለፉት ወራት ጭማሪ ታይቶበታል። በዋነኛ የቡና አምራች አገራት ውስጥ እያጋጠመ ያለው ምጣኔ ሀብታዊ እና የተፈጥሮ ሁኔታ መለዋወጥ ምክንያት በቀጣይ ዓመታትም የቡና ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር እንደሚችል እየተነገረ ነው።

በቅርቡ በተካሄደ የባለልዩ ጣዕም ቡና ውድድር ዓለም አቀፍ ጨረታ የኢትዮጵያ አንድ ኪሎ ቡና ከ102 ሺህ ብር በላይ በመሸጥ አዲስ ክብረ ወሰን መመዝገቡ ይታወሳል።

የቡና ግብይት ተንታኝ የሆነችው ጁዲ ጌብስ እንደምትለው በአሁኑ ወቅት በዓለም ገበያ ያለው ያልተቆላ የቡና ምርት ዋጋ “በታሪክ ከፍተኛ ከሚባል ደረጃ” ላይ ደርሷል።

የቡና ባለሙያዎች እንዳሉት ለተወዳጁ ፍሬ ዋጋ መናር የምርት መቀነስ፣ የግብይት ሂደት፣ የክምችት መቀነስ እና ሌሎችንም ጉዳዮች በምክንያትነት ይጠቅሳሉ።

ከሦስት ዓመታት በፊት በስፋት የሚጠጣውን አረቢካ የተባለውን የቡና ዓይነት በከፍተኛ መጠን ለዓለም በማቀረብ ቀዳሚ የሆነችው ብራዚል ምርቷ በውርጭ በመመታቱ በገበያው ላይ የምርት እጥረትን ተከስቶ ነበር።

አረቢካ ቡና ኢትዮጵያን ጨምሮ በተወሰኑ አገራት ውስጥ የሚመረት ሲሆን፣ በመዓዛው እና በጣዕሙ በአብዛኞቹ ቡና ጠጪዎች በእጅጉ ተፈላጊው የቡና ዓይነት ነው።

ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የተባለውን የቡና ምርት ወደ ውጭ መላኳ ተገልጾ ነበር። በዚህም 300 ሺህ ቶን የሚጠጋ ቡና ወደ ተለያዩ አገራት ተልኮ 1.43 ቢሊየን ዶላር ኢትዮጵያ ያገኘች ሲሆን፣ በአገሪቱ የቡና ንግድ ታሪክ ከፍተኛው መሆኑን ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ገልጿል።

በአየር ጠባይ ለውጥ ምክንያት የተፈጠረውን የአረቢካ ቡና እጥረት ለማሟላት ቡና ገዢዎች ፊታቸውን ሮቡስታ የተባለውን ቡና በከፍተኛ መጠን ወደምታመርተው ቬትናም አዙረው ነበር።

ነገር ግን ይህ የቡና ዓይነት በቡና ማፍያ ማሽን ለሚዘጋጀው በስፋት ተወዳጅ ለሆነው ቡና ብዙም የሚፈለግ ሳይሆን በፈላ ውሃ ተበጥብጦ የሚጠጣ ዱቄት ቡና ለማዘጋጀት የሚውል ነው።

በቬትናም እና በአካባቢዋ በአስር ዓመት ውስጥ አጋጥሞ የማያውቅ ድርቅ በመከሰቱ አምራቾች ከቡና ይልቅ ፊታቸውን ዱሪያን ወደተባለው መዓዛማ ፍሬ ምርት ለማዞር ተገደዋል።

በቬትናሟ ሆ ቺ ሚኒ ሲቲ ውስጥ ተቀማጭ የሆነው የቡና ምርት አማካሪ ዊል ፊርዝ እንዳለው የአየር ጠባይ ለውጥ የቡና ተክል እድገትን በመጉዳቱ በውጤቱ ምርት እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል።

“የሮቡስታ ቡና ፍላጎት መነቃቃት በጀመረበት ጊዜ ነበር፣ ዓለም ለተጨማሪ የቡና አቅርቦት ጥረት ሲያደርግ የነበረው” በማለት ጋንስ ገልጻለች።

ነገር ግን ቬትናማውያን በቻይና ተፈላጊ የሆነውን ዱሪያን የተሰኘውን ፍሬ በስፋት ሲያመርቱ የቡና ምራት አቅርቦታቸው ቀንሷል። ባለፈው ሰኔ የቀረበው የሮቡስታ ቡና ምርት ከቀደመው ዓመት ሰኔ ጋር ሲነጻጸር በ50 በመቶ አሽቆልቁሏል።

በዚህም ሳቢያ በመላው ዓለም የተመረተ ቡና ምርት ክምችት “ተመናምኗል” ሲል የዓለም አቀፉ የቡና ድርጅት መረጃ አመልክቷል።

ተፈላጊውን አረቢካ ቡናን በከፍተኛ ሁኔታ ከሚያመርቱት አገራት መካከል በሆኑት በኮሎምቢያ፣ በኢትዮጵያ፣ በፔሩ እና በኡጋንዳ የሚገኙ ቡና ላኪዎች የሚያቀርቡትን ምርት መጠን ቢያሳድጉም የተፈጠረውን ጉድለት የሚያሟላ ምርት ግን ማግኘት አልተቻለም።

በዚህም ሳቢያ በዓለም ላይ ለየትኛውም ዓይነት የቡና ምርት ያላው ፍላጎት በመጨመሩ፣ በአሁኑ ወቅት ሮቡስታም ሆነ አረቢካ ቡናዎች በሸቀጦች ገበያ ላይ ከፍተኛ ሊባል በሚችል ዋጋ በመሸጥ ላይ ናቸው።

ቡና

በቡና ገበያ ላይ የተፈጠረው ቀውስ

ይህ የምርት እጥረት እና ያስከተለው የዋጋ ጭማሪ ወደ ቡና ጠጪዎች ኪስ መድረሱ አጠያያቂ አይደለም።

የጅምላ ነጋዴ የሆነው ፖል አርምስትሮንግ እንደሚያምነው ቡና ጠጪዎች በየዕለቱ ለሚጎነጩት ቡና በቅርቡ ተጨማሪ ክፍያ የሚጠየቁበት ዕድል ይኖራል።

ከደቡብ አሜሪካ እና ከእስያ አገራት ቡና በማስመጣት በመቁላት በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ለሚገኙ ካፌዎች የሚያቀርበው ‘ካራራ ኮፊ ሮስተርስ’ ባለቤት የሆነው አርምስትሮን በመርቱ ላይ በቅርቡ ዋጋ መጨመሩን ለቢቢሲ ገልጿል።

ጨምሮም ከዚህ በፊት ቡና ለማቅረብ የገባቸው ኮንትራቶች በቀጣይ ወራት የሚያበቁ ሲሆን፣ ቡናውን የሚጠቀሙ ካፌዎች ከፍተኛውን የቡና መግዣ ጭማሪውን ወደ ተጠቃሚዎች ለማሻገር የሚወስኑበት ጊዜ መቃረቡን ጠቅሷል።

በዚህም ሳቢያ ቡናን ቆልተው እና ፈጭተው የሚያዘጋጁ ተቋማት፣ ነጋዴዎች፣ ካፌዎች እና ተጠቃሚዎች በቅርብ ወራት ውስጥ ከፍተኛ የቡና ዋጋ ንረት እንደሚገጥማቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በብራዚል ቡና አምራች የሆነው ኤፍኤኤፍኮፊስ ሥራ አስፈጻሚው ፌሊፔ ባሬቶ ዋጋ በመጨመሩ ቡና ጠጪዎች ከዋጋ አንጻር “ጫናው እየተሰማቸው ነው” በማለት የሚታየው የዋጋ ንረት ተጨባጭ መሆኑን ይስማማበታል።

ነገር ግን ይህ የቡና ዋጋ ጭማሪ የተከሰተው በቡና ምርት መወደድ ሳይሆን፣ በኪራይ እና በሠራተኛ ክፍያ መጨመር ምክንያት እንደሆነ ይነገራል። የቡና ንግድ አማካሪው ተቋም ‘አሌግራ ስትራተጂስ’ እንደሚገምተው በአንድ ሲኒ ቡና ዋጋ ላይ የቡናው ድርሻ ከ10 በመቶ በታች ሲሆን አብዛኛው ገንዘብ የግብይት ሰንሰለቱ ተሳታፊዎች ድርሻ ነው።

ቡና በቤት ውስጥ ሲዘጋጅ ዋጋው ርካሽ ሲሆን፣ በትላልቆቹ የቡና መሸጫ ካፌዎች ውስጥ ሲቀርብ ግን ዋጋው ይንራል።

ባለው የቡና ገበያ ሁኔታ ምክንያት ዝቅተኛ ጥራት ያላቸው የቡና ምርቶች ሳይቀሩ ዋጋቸው ከፍ ማለቱን ፌሊፔ ይናገራል። ይህ ማለት ደግሞ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ቡናዎች የበለጠ ዋጋን ማግኘት ይችላሉ።

“ልዩ የቡና ምርቶችን አዘጋጅተው በሚያቀርቡ ካፌዎች ውስጥ እና በሌሎች ካፌዎች የሚጠየቀው የአንድ ሲኒ ቡና ዋጋ ልዩነቱ በጣም ዝቅ ያለ ነው” ይላል።

ቡና
የምስሉ መግለጫ,በተለያየ መልኩ የሚዘጋጀው ቡና በዓለም ዙሪያ ተወዳጅ መተጥ ነው

የቡና አሳሳቢው መጪ ጊዜ

አንድ ሦስተኛውን የዓለማችንን የቡና ምርት የምታቀርበው ብራዚል በቀጣይ ወራት የምታገኘው የቡና ምርት መጠን በገበያው እና በዋጋ ላይ ከሚኖረው ለውጥ አኳያ ወሳኝ መሆኑን ፌሊፔ ይናገራል።

“ሁሉም ሰው መቼ ዝናቡ እንሚጥል ነው እየተጠባበቀ ያለው። ዝናቡ ቀደም ብሎ የሚጥል ከሆነ የቡና ተክሎቹ ጤናማ በመሆን የሚያብበው ፍሬም ጥሩ ይሆናል” ይላል።

ነገር ግን ዝናቡ ዘግይቶ እስከ ጥቅምት ድረስ የሚቆይ ከሆነ፣ ለቀጣይ ዓመት የሚኖረው የምርት ትንበያ ስለሚቀንስ በገበያው ላይ ያለው እጥረት እና የዋጋ ጭማሪ ይቀጥላል በማለት አክሏል።

የአየር ጠባይ ለውጥ በረጅም ጊዜ ሂደት በዓለም የቡና ኢንዱስትሪ ላይ ከባድ የሆነ ተግዳሮት ይደቅናል።

በአውሮፓውያኑ 2022 የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው የበካይ ጋዝ ልቀትን በከፍተኛ መጠን መቀነስ ቢቻል እንኳን፣ ለቡና ምርት በከፍተኛ ሁኔታ አመቺ በሆኑት አካባቢዎች የሚበቅለው ቡና በ2050 በግማሽ ይቀንሳል።

የቡና ምርት ዘርፍን ወደፊት ጠብቆ ለማቆየት በተለያዩ መንገዶች ለአምራቾች ድጋፍ እና ጥበቃ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ፌሊፔ ይመክራሉ።

በዚህም አርሶ አደሮች የእርሻ መሬታቸው መልሶ እንዲያገግም እና ዘላቂነት እንዲኖራቸው በሚያደርጉ የግብርና ተግባራት ላይ እንዲያተኩሩ የሚያደርጉ ግብር ቅነሳን የመሳሰሉ ማበረታቻዎች አስፈላጊ ናቸው ይላሉ።