ፖሊስ

ከ 2 ሰአት በፊት

እሑድ ዕለት ኤፍቢአይ ዌስት ፓልም ቢች በሚገኘው የትራምፕ የጎልፍ መጫወቻ ስፍራ የግድያ ሙከራ መኖሩን በመግለጹ፤ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለደኅንነታቸው ሲባል አስተማማኝ ጥበቃ ወደሚያገኙበት ቦታ እንዲዘዋወሩ ተደርገዋል።

የአሁኑ ክስተት የተፈጠረው ከሁለት ወር በፊት በትለር ፔንሲልቬንያ ውስጥ በትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ስብሰባ ወቅት በተተኮሰ ጥይት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቆስለው የአንድ ደጋፊያቸው ሕይወት ካለፈ በኋላ ነው።

የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ራያን ሩዝ ስለተባለው ተጠርጣሪ ዝርዝር መረጃ እያወጡ ነው። ስለጥቃቱ እና ስለተጠርጣሪው እስካሁን ምን ይታወቃል?

ተጠርጣሪው እንዴት ሊታይ ቻለ?

ክስተቱ የተፈጠረው ፍሎሪዳ ከሚገኘው የትራምፕ መኖሪያ ቤት ከሆነው ማር-አ-ላጎ 15 ደቂቃ ያህል ብቻ ርቆ በሚገኘው በዌስት ፓልም ቢች የትራምፕ ኢንተርናሽናል ጎልፍ ክለብ ነው።

ታጣቂው ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው ሴክሬት ሰርቪስ በሚባሉት የፕሬዝዳንታዊ ጥበቃ ባልደረቦች ነበር። የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጎልፍ ከመጫወታቸው በፊት የሴክሬት ሰርቪስ ባልደረቦች አካባቢውን ሲቃኙ ነው ተጠርጣሪውን የተመለከቱት።

የአካባቢው ፖሊስ ኃላፊ ሪክ ብራድሻው መጀመሪያ ኤኬ 47 መሰል ጠመንጃ የጎልፍ ሜዳውን በከለለው ቁጥቋጦ ውስጥ ተደብቆ መገኙቱን ገልፀዋል። በወቅቱ ትራምፕ ከታጣቂው ከ272 እስከ 557 ሜትር ርቀት ላይ ነበሩ ሲሉ ኃላፊው ተናግረዋል።

የሴክሬት ሰርቪስ ባልደረቦች ጠመንጃውን ከያዘው ሰው ጋር “በፍጥነት የተኩስ ልውውጥ ቢያደርጉም” ተጠርጣሪው አምልጧል ብለዋል።

“የሴክሬት ሰርቪስ መደረግ ያለበትን በትክክል አድርጓል።”

የፖሊስ መኪና

ተጠርጣሪው እንዴት ተያዘ?

የሰክሬት ሰርቪስ ባልደረቦች ታጣቂውን ሲያዩ ተኩስ ከፍተውበታል።

ተጠርጣሪው ጠመንጃውን ጥሎ በተሽከርካሪ ሸሸ። ከመሳሪያው በተጨማሪ ሁለት አነስተኛ ቦርሳዎች፤ የዒላማ ማነጣጠሪያ እና የጎፕሮ ካሜራ ጥሎ መሸሹን ብራድሻው ተናግረዋል።

አንድ የዓይን እማኝ ግለሰቡ ከቁጥቋጦው ወደ ጥቁር ኒሳን መኪና ሲሸሽ አይቷል ሲሉ ፖሊሱ ተናግረዋል። የዓይን እማኙ መኪናውን ፎቶ በማንሳት ለሕግ አስከባሪ አካላት ሰጥቷል።

ተጠርጣሪው ከትራምፕ የጎልፍ መጫወቻ ሜዳ 61 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ሚገኘው ማርቲን አውራጃ ከተሻገረ በኋላ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ባለው አውራ ጎዳና ሲያሽከረክር በፖሊስ ተይዟል።

የተጠርጣሪው ስም ራያን ዌስሊ ሩዝ እንደሚባል በርካታ የሕግ አስከባሪ ምንጮች ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።

ተጠርጣሪው ራያን ዌስሊ ሩዝ
የምስሉ መግለጫ,ተጠርጣሪው ራያን ዌስሊ ሩዝ

ራያን ሩት ማን ነው?

የተጠርጣሪው ዝርዝር ታሪኮች ቀስ በቀስ ብቅ እያሉ ነው።

የሩዝ ልጅ ኦራን ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደተናገረው ከሆነ “አፍቃሪ እና አሳቢ አባት” ነው ሲል ገልጾታል።

“በፍሎሪዳ ምን እንደተፈጠረ አላውቅም። ነገሮች ልክ እንደሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ምክንያቱም ከሰማሁት አነስተኛ ነገር በመነሳት የማውቀው ሰው አልመስልህ ብሎኛል” ሲል ኦራን ለሲኤንኤን በሰጠው መግለጫ ተናግሯል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ ከስሙ ጋር የሚዛመዱ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾችን አግኝቷል። ሩዝ የውጭ ተዋጊዎች ለዩክሬን ተሰልፈው ከሩሲያ ጦር ጋር እንዲዋጉ ጥሪ ማቅረቡን ያመለክታሉ።

ስለ ቻይና “ባዮሎጂካዊ ጦርነት” እና የኮቪድ -19 ቫይረስን እንደ “ጥቃት” በማቅረብ ፀረ ቻይና መልዕክቶችን ከማስተላለፍ ባለፈ ለፍልስጤም እና ለታይዋን ድጋፉን የገለጠበት መልዕክትም ተገኝቷል።

ምንም ዓይነት የውትድርና ልምድ ያልነበረው ሩዝ እአአ በ2023 ለኒውዮርክ ታይምስ፤ ከሩሲያ ወረራ በኋላ ታሊባንን ሸሽተው ከወጡ የአፍጋኒስታን ወታደሮች መካከል ወታደሮችን ለመመልመል ወደ ዩክሬን ተጉዞ እንደነበር ተናግሯል።

እስከቅርብ ጊዜ ድረስም በምልመላ ሥራው መሳተፉን የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ። በሐምሌ ወር በፌስቡክ ገጹ ላይ “ወታደሮች እባካችሁ አትደውሉልኝ። ዩክሬን የአፍጋኒስታን ወታደሮችን እንድትቀበል እና በመጪው ጊዜ አንዳንድ መልሶች እንዲኖረን ለማድረግ አሁንም እየሞከርን ነው። በቀጣይ ወራት ምላሽ እናገኛለን … እባካችሁ ትዕግስት ይኑራችሁ” ሲል አስፍሯል።

ቀደም ብሎ የወጡ ሪፖርቶች ሩዝ የወንጀል ሪከርድ እንደነበረው ይጠቁማሉ። እንደ ሲቢኤስ ምንጮች ከሆነ ግለሰቡ በሰሜን ካሮላይና ግዛት በጊልፎርድ አውራጃ ከ2002 እስከ 2010 ድረስ በበርካታ ወንጀሎች ተከሶ ተፈርዶበታል።

ከቀረቡበት ወንጀሎች መካከል የተደበቀ መሳሪያ መያዝ፣ በፖሊስ አባል በቁጥጥር ስር መዋልን መቃወም፣ ባልታደሰ መንጃ ፈቃድ ማሽከርከር፣ የተሰረቀ ንብረት መያዝ እና ገጭቶ ማምለጥ ይገኙበታል።

ግለሰቡ ይዟቸው የነበሩ ቁሳቁሶችን ፖሊስ አሳይቷል
የምስሉ መግለጫ,ግለሰቡ ይዟቸው የነበሩ ቁሳቁሶችን ፖሊስ አሳይቷል

ትራምፕ ምን ገጠማቸው?

ትራምፕ ጉዳት አልደረሰባቸውም።

ክስተቱ በምርጫ ዘመቻ ቡድናቸው ከተረጋገጠ በኋላ “በአካባቢዬ የተኩስ ድምጽ ነበር። ነገር ግን ወሬው ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ መምጣት ከመጀመሩ በፊት ጉዳዩን ቀድማችሁ እንድትሰሙ እፈልግ ነበር። እኔ ደህና ነኝ” ሲሉ መግለጫ አውጥተዋል።

ትራምፕ ሃሳባቸውን ለፎክስ ኒውስ ዜና አቅራቢ ሾን ሃኒቲ የሰጡ ሲሆን፣ ጋዜጠኛውም እሑድ የነበረውን ትዕይንት በድጋሚ ተናግሯል።

“[በጎልፍ ጨዋታው] ከአምስተኛው ጉድጓድ ወደ ሚቀጥለው ሊሄዱ ነበር” ሲል ሃኒቲ ገልጿል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት የትኩስ ድምጽ ሰምተዋል ብሏል ። “በሰኮንዶች ውስጥ የሴክሬት ሰርቪስ ባልደረቦች ፕሬዝዳንቱን ከበው ሸፈነዋቸዋል።”

በማስከተልም ተጨማሪ የሴክሬት ሰርቪስ አባላት በብረት ለበስ ተሽከርካሪ በፍጥነት ደርሰው ትራምፕን ለደኅንነታቸው ሲሉ ወስደዋቸዋል በማለት አክሏል።

የጎልፍ መጫወቻ ቦታው
የምስሉ መግለጫ,የጎልፍ መጫወቻ ቦታው

ቀጥሎ ምን ይፈጠራል?

ከፖሊስ ጋር በተመሳሳይ ወቅት መግለጫ የሰጡት የኤፍቢአይ ማያሚ ጽህፈት ቤት ባልደረባው ጄፍሪ ቬልትሪ ቢሮው ከሌሎች የሕግ አስከባሪ አካላት ጋር በመሆን ምርመራዎችን እየመራ መሆኑን ተናግረዋል።

“የመርማሪ ቡድኖችን፣ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ሰጪ ቡድን አባላትን፣ የቦምብ ቴክኒሻኖችን እና የማስረጃ መሰብሰብ ቡድን አባላትን ጨምሮ በርካታ አካላትን አሰማርተናል” ሲሉ ቬልትሪ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የዴሞክራቲክ ፓርቲ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ የሆኑት ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ ስለ ክስተቱ ገለጻ እንደተደረገላቸው እና ትራምፕ ደህና መሆናቸውን በማወቃቸው እፎይታ እንደተሰማቸው ዋይት ሐውስ አስታውቋል።

“በቀድሞው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ላይ ሊሆን ይችል የነበረው የግድያ ሙከራ ጥቃት በጣም አሳስቦኛል” ሲሉ ሃሪስ በመግለጫቸው ተናግረዋል።

በፔንስልቬንያ የተፈጸመውን የግድያ ሙከራ ለመመርመር የተቋቋመው እና ከሁለቱ ፓርቲዎች የተወጣጣው ግብረ ኃይል የቀድሞው ፕሬዝዳንት ምንም ዓይነት ጉዳት ስላልደረሰባቸው እፎይታ ተሰምቶናል፤ “ፖለቲካዊ ጥቃት የሚያሳስበን ከመሆኑም በላይ በሁሉም መልኩ የሚወገዝ ነው” ብለዋል።

የሪፐብሊካን ኮንግረስ አባል ማይክ ኬሊ እና የዴሞክራቱ ጄሰን ክራው ግብረ ኃይሉ “ምን እንደተፈጠረ እና ደኅንነቱ ምን ዓይነት ምላሽ እንደሰጠ” ለመረዳት ከሴክሬት ሰርቪስ አጭር ማብራሪያ ጠይቀዋል።

የሴክሬት ሰርቪሱ ራፋኤል ባሮስ እሁድ ዕለት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ከሆነ ካለፈው የግድያ ሙከራ በኋላ እርምጃዎች ተወስደዋል፤ “የአደጋው ደረጃ ከፍተኛ ነው” ብለዋል።

በትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ ሊፈጽም ነበር ተብሎ የተጠረጠረው ግለሰብ ዛሬ ሰኞ ለመጀመርያ ጊዜ የፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።