September 16, 2024 – Getachew Shiferaw 

የፋኖ አመራሮች የሰሞኑን ወጥመድ በጥንቃቄ እለፉት!

የሶማሊያ ባለስልጣናት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ቡድኖች አግዛለሁ የሚል ፕሮፖጋንዳ አሰራጭቶ ብልፅግና ደንበኛ ወጥመድ አድርጎታል። ሰሞኑን በርካታ ሚዲያዎች ወደ ፋኖ አመራሮች እንዲደውሉ ይደረጋሉ። የፋኖ አመራሮች ይህን ወጥመድ በጣም በጥንቃቄ ማለፍ አለባቸው።

1) በጣም ጠቃሚው አማራጭ ፋኖ በጉዳዩ ምንም መልስ ባይሰጥ ነው። አስፈላጊ አይደለም። የፋኖ ትኩረት ህዝቤን ነፃ ማውጣት ላይ ነው የሚል መሆን አለበት። የአማራ ህዝብ በርካታ ችግሮች ውስጥ በመሆኑ መፍታት ያለብን የራሳችን ጉዳይ አለ። ጊዜም ትኩረታችንም ለራሳችን አላማ ነው ማለት ያስፈልጋል።

2) ፋኖ እርዳታም፣ ድጋፍ ወዘተ የሚያገኘው ከህዝብ ነው። ስንቄና መጠለያዬ ህዝቤ፣ ትጥቅ የማገኘው ሰተት ብሎ ከመጣ ጠላት ነው ማለት በቂ ነው። ለድጋፍ ህዝብ፣ ለትጥቅ ጠላት በቂ ነው። አራት ነጥብ!

ማንም ተነስቶ አግዛለሁ ሊል ይችላል። ከእነ ሽመልስ አብዲሳ ጋር የተኮራረፈ የብልፅግና ቡድን “ፋኖን አግዛለሁ” ቢል “አዎ ያግዘኝ” አይባልም። ማንም አግዛለሁ፣ አላግዝም ስላለ፣ መግለጫ ስለሰጠ ብቻ ፋኖ መልስ መስጠት የለበትም። ጫካ ያሉ አመራሮች ስለ ጉዳዩ ላይሰሙ ስለሚችሉም “አልሰማሁም” ማለት ጤነኛ መልስ ነች። ጫካ ውስጥ ያለ ኃይል የሶማሊያን ጉዳይ የግድ መስማት የለበትም። “አልሰማሁም” ምክንያታዊ መልስ ነው!

3) የግድ ከሆነ በገደምዳሜው ማለፍን መልመድ ያስፈልጋል። የሉአላዊነትም ሆነ ሌላ ጉዳይ ስልጣን ሲያዝ የሚፈታ ጉዳይ ነው። ከውጭ ኃይሎች ጋር ያለ ግንኙነት ስልጣን ስንይዝ የምንፈታው እንጅ አሁን ባለንበት ሁኔታ የሚቻል አይደለም የሚል መልስ በቂ ነው። ለዚህ ሲባል የኢትዮጵያ ህዝብ ተባብሮ አገዛዙን እንዲያስወግድ ከዛ በኋላ የአገር ጥቅምና ሉአላዊነት ለማስከበር መስራት እንደሚቻል መግለፅ ይቻላል።

4) አገዛዙ ለህዝብም ለአገርም ለአገርና ህዝብ ጥቅም የማይቆም፣ የአገርንም የውጭ ፖለቲካን ያበላሸ መሆኑን ቆጠብ ብሎ መግለፅ ይቻላል።

እንዲህ ያሉ ወጥመዶች ጦሳቸው ብዙ ነው። ፋኖ በርካታ ስብጥር ያለው ህዝብ ድጋፍ ይሰጠዋል። መሰል የችኮላ አስተያየቶች ድጋፍ ይከፋፍላሉ። ለአገዛዙ የጎንዮሽ ፕሮፖጋንዳ ያመቻሉ፣ ስህተት ከተሰራ ለአመታት እየተከተሉ አይለቁም። ተመሳሳይ አጋጣሚዎች በኢህአፓ ዘመንም ተፈጥረዋል።

“የጠላቴ ጠላት ወዳጄ” የሚባል ድፍን አባባል አለ። ይህኛው ውስብስብ ነው። ፋኖ ሰሞኑን ለምርኮኞች እያደረገ ባለው ብስለት ልክ ለወጥመዱም ስክነት ያስፈልገዋል። የፋኖ አመራሮች ከስሜታዊ የቲክቶክ ደጋፊዎቻቸው መለየት አለባቸው። መሰል አጀንዳዎች የማናውቀውና ጥሻ የሆነ የዓለም ፖለቲካ ውስጥ ወሰዶ ይወሽቀናል። እጅግ አደገኛ ነው።

ለብሽሽቅ ከሆነ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያለው ኃይል በቂ ነው። የፋኖ አመራሮች ከዚህ ዘመናትን ሊከተላቸው ከሚችል ጉዳይ ራሳቸውን ማራቅ፣ ወጥመዱን በብስለት ማክሸፍ አለባቸው!

ፋኖ የአማራ ህዝብን ህልውና ማስጠበቂያ እንጅ የሌላ ኃይል ወዳጅነት መፍጠሪያ፣ ማስፈራሪያ፣ መደራደሪያ መሳሪያ አይደለም። ማንም ሳያማክረው “እረዳለሁ” ስላለ “አዎ ያግዘኝ” የሚል ኃይል አይሆንም።

ከበርካታ ሚዲያዎች ይደወላል። ጥንቃቄ አድርጉ። ቅርበት ያላችሁ ለፋኖ አመራሮች አድርሱ።