September 16, 2024 – Konjit Sitotaw 

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኀበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) በአዳማ ከተማ እየተካሄዳ ላለው የብልፅግና ፓርቲ አባላት ሥልጠና ከመንግሥት ካዝና ገንዘብ ወጥቶ መከፈሉ የህዝብ ሃብት እየተመዘበረ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ሲል በመግለጫው ተችቷል፡፡

የፌደራል ዋና ኦዲተር እና የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ይሄንን ጉዳይ ተከታትለው ከሕግ አግባብ ውጪ የሕዝብ ሀብትን የዘረፈውን የመንግሥት አካል ተጠያቂ እንዲያደርጉ እና ጉዳዩን በይፋ ለሕዝብ እንዲያሳውቁ ጠይቃለው የሚለው ፓርቲው ይሁን እንጂ አጥጋቢ ምላሽ አለማግኘቱን አስታውቋል፡፡

ብልፅግና ፓርቲ መንግሥት እና ፓርቲን ላለመለየት ዕያሳየ ያለው ዳተኝነት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት እንቅፋት ነው!

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኀበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ጥቅምት 07/2016 ዓ.ም. ለብልፅግና ፓርቲ አባላት ሥልጠና ከመንግሥት ካዝና ገንዘብ ወጥቶ መከፈል ስህተት መሆኑን እና ሊታረም እንደሚገባ ገልፀን መግለጫ ማውጣታችን እንዲሁም በመግለጫችን ‹‹ የፌደራል ዋና ኦዲተር እና የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ይሄንን ጉዳይ ተከታትለው ከሕግ አግባብ ውጪ የሕዝብ ሀብትን የዘረፈውን የመንግሥት አካል ተጠያቂ እንዲያደርጉ እና ጉዳዩን በይፋ ለሕዝብ እንዲያሳውቁ በጥብቅ እንጠይቃለን።›› ማለታችንም የሚታወስ ነው፡፡ በተጨማሪም ጥቅምት 12/2016 ዓ.ም. ለፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የመንግሥት ንብረት እና ሀብት ለፓርቲ ስራ መዋሉን ጠቅሰን በኦዲት እንዲጣራልን በደብዳቤ የጠየቅን ቢሆንም እስከ አሁን አጥጋቢ ምላሽ አላገኘንም፡፡

እንደ ባለፈው ዓመት ሁሉ ዘንድሮም ፖርቲው በተመሳሳይ መንገድ ያንኑ ስህተት በዐደባባይ ሲደግመው የሕዝብ መገናኛ ብዙኃኑም እንደ ትልቅ ስኬታማ ሥራ ዜና አድርገው ሲዘግቡት ተመልክተናል፤ በመሠረቱ ብልፅግና ፓርቲ የመንግሥት እና የፓርቲ ሥራ መለያየት አለበት የሚለውን የፖለቲካ ሀ ሁ ካለመረዳት የሚሠራው ስህተት ሳይሆን የማናለብኝነት መንገድን መርጦ መሆኑን በግልፅ ያሳያል፡፡

ኢዜማ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሒደት በመግለጫ እና በንግግር ብቻ እውን ይሆናል የሚል ቅዠት የለውም፡፡ በተግባር መሠራት ያለባቸው ሥራዎችን ለመሥራት ቁርጠኛ ሆኖ የሚሠራ መንግሥትና በሥልጣን ላይ ያለ ፓርቲ እስካልተፈጠረ ድረስ ሀቀኛ ምርጫ ማድረግ፣ ነፃ መገናኛ ብዙኃን መፍጠር እንዲሁም ገለልተኛ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን መገንባት ሊታሰብ የሚችል አይደለም፡፡ ብልፅግና ፓርቲ የመንግሥት ሥልጣንን እንደያዘ ፓርቲ ዕያሳየ ያለው ዳተኝነትም በሀገራችን እውን ሆኖ ማየት ለምንፈልገው የመድብለ ፓርቲ እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንቅፋት መሆኑን በተደጋጋሚ በሚፈፅማቸው ስህተቶች እየተመለከትን ነው፡፡

የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት፣ ነፃና ገለልተኛ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ እና መሰል መንግሥትና ፓርቲን የመለየት ተግባሮች በአንድ ጀንበር ተሳክተው ተጠናቀቁ የምንላቸው ተግባራት ሳይሆኑ ዕለት በዕለት በእያንዳንዱ ተግባራችን እየተገለጹ እየዳበሩ እና እየጠነከሩ መሔድ ያለባቸው ልምምዶች ናቸው፡፡ ኢዜማ እነዚህ ተቋማት በገለልተኝነት ሥራቸውን እንዲሠሩ እየተከታተለ ልምዶቹም እንዲጎለብቱ ብሎም በሀገራችን እውነተኛ ዴሞከራሲ ሥርዓት ግንባታ እንዲኖር የበኩሉን አስተዋፅዖ እያደረገ ይገኛል፡፡

ነገር ግን ብልፅግና ፓርቲ ከዚህ በተቃራኒው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ አደጋ እና ስጋት የሚደቅን ተግባር ደጋግሞ በመሥራት ለተጠያቂነት ዝግጁ አለመሆኑን ዕያሳየ ይገኛል፤ ይህ ደግሞ ዛሬ ላይ ስህተት መሆኑ ታውቆ በአስቸኳይ የእርምት እርምጃ ካልተወሰደ ለሀገር ዴሞከራሲ ግንባታ ወደሚበጅ ትክክለኛ አሠራር እና ልምምድ ካልተመለሰ በስተቀር የሚያመጣው ቀውስ እና ይዞ የሚመጣው መዘዝ ቀላል አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

በመሆኑም አሁንም ብልፅና ፓርቲ እየሄደበት ካለው የተሳሳተ መንገድ ተመልሶ ስህተቱን በማረም የመንግሥትን ሀብት እና ንብረት እንዳይባክን እና አላስፈላጊ ቦታ እንዳይውል የመገናኛ ብዙኃን ገለልተኝነታቸው በማረጋገጥ ይህን መሰል ተግባር እንዲያወግዙ እየጠየቅን የሚመለከታቸው ዴሞክራሲያዊ ተቋማትም ሰሞኑን ብልፅግና ፓርቲ ለሥልጠና የተጠቀመበትን ሀብትና ንብረቱ በትክክል ወደ መንግሥት ካዝና መመለሱን እንዲያረጋግጡ ከወዲሁ ጥሪያችንን እናቀርባለን፤ መንግሥትንና የሥራ ኃላፊዎቹን ተጠያቂ ለማድረግ የተቋቋሙ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትም በሀገር እና በሕዝብ የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ መንግሥትን ተጠያቂ እንዲያደርጉ እንዲሁም የሀገርን ሀብት ከሙስና እና ከምዝበራ እንዲታደጉ እናሳስባለን ።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኀበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)

ኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባ

መስከረም 06/2017 ዓ.ም.