September 16, 2024 

በህወሃት ነባር አመራሮችና በጊዚያዊ አስተዳደሩ ሃላፊዎች መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች መሰጠታቸው እንደቀጠለ ነው፡፡

የባይቶና አባይ ትግራይ ፓርቲ ምክትል ሊመንበር የሆኑት አቶ ዮሴፍ በርሄ በትግራይ እየተከሰቱ ላሉ ፖለቲካዊ ቀውሶች የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ነባሩና በዶክተር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ቡድን ነው ብሎ ፓርቲያቸው እንደሚያምን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዳይኖር፣ስርአት አልበኝነት እንዲበራከትና መሰል ችግሮች እንዲፈጠሩ በታችኛው መዋቅር ያሉና ነባሩን የህወሃት መዋቅር የሚደግፉ አመራሮች ፈተና ሆነዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አንጻር ጊዚያዊ አስተዳደሩ የተሻለ የፖለቲካ አመለካከት አለው ለማለት ያስደፍራል ያሉት ምክትል ሊቀመንበሩ ያም ቢሆን ግን ችግሮችን ከመፍታትና የህዝብን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ ሁለቱ ቡድኖች ስልጣንን የመጀመሪያ ጉዳይ አድርገው መሻኮታቸው ግባቸው ምን እንደሆነ ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው ብለዋል፡፡

ላለፉት 50 ዓመታት ትግራይን ወጥሮ የያዘው የአንድ ፓርቲ አስተሳሰብ መወገድ እንዳለበት እናምናለን ያለው  ፓርቲው ይህንን ለማድረግም የሚጠበቅብኝን የቤት ስራ እየሰራሁ ነው ሲል እወቁልኝ ብሏል።