ሪያል ማድሪድ 16ኛው የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ለማንሳት ይፎካከራል

ከ 5 ሰአት በፊት

የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዛሬ [ማክሰኞ መስከረም 8] ምሽት ይጀምራል።

36 ክለቦች እንደ አዲስ በተዋቀረው ውድድር ላይ ይሳተፋሉ። ቀደም ሲል ለባለትልቁ ጆሮ ዋንጫ ይፋለሙ የነበሩት 32 ቡድኖች ብቻ ነበሩ።

ፍጻሜውን ሙኒክ ላይ የሚያደርገውን የዘንድሮውን ዋንጫ ማን ሊያነሳ እንደሚችል የቢቢሲ የእግር ኳስ ተንታኞች ግምታቸውን ሰጥተዋል።

የትኛው ቡድን አስገራሚ ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል እና ጎልተው ሊወጡ የሚችሉ ተጫዋቾችንም ገምተዋል።

የሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ማን ይሆናል?

የቢቢሲ አግር ኳስ ፀሐፊ ፊል ማክነልቲ ግምቱን ለሪያል ማድሪድ ሰጥቷል።

ምክንያት ያለው ደግሞ የክሊያን ምባፔ ቡድኑን መቀላቀልን ነው።

ማንቸስተር ሲቲ ሊቀናቀናቸው ቢችልም ማድሪዶች ደካማ በሆኑበት የውድድር ዘመን ጭምር ዋንጫውን የማንሳት ልምድ እንዳላቸው አሳይተዋል ብሏል።

ለቢቢሲ በፈረንሳይ እግር ኳስ ዙሪያ ትንታኔዎችን የሚያቀርበው ጁሊየን ላውረንስም ተመሳሳይ ሃሳብ አለው።

ማድሪድ ዋንጫውን ደጋግሞ ማንሳቱ ውድድሩን አሰልቺ አድርጎታል። ዘንድሮም ተለየ ነገር አይኖርም ብሏል።

የስፔኑ ቡድን ለዚህ የሚሆን ልምድ፣ ታሪክ፣ ገንዘብ፣ ጊዜ፣ ጥንካሬ እና ችሎታ አለው ብሏል።

በስፔን እግር ኳስ ዙሪያ ለቢቢሲ የሚጽፈው ጉለም ባላግ በበኩሉ ከግማሽ ፍጻሜ በኋላ አሸናፊው ቡድን በብዙ ነገሮች ላይ ሊመሠረት ይችላል ብሏል።

ሆኖም ማንቸስተር ሲቲ የፕሪሚር ሊጉንም ሆነ የሻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫ እንደሚያነሳ ግምቱን አስቀምጧል።

ኮንስታንቲን ኤክነር የጀርመን እግር ኳስን በተመለከተ ትንታኔዎችን ለቢቢሲ በመጻፍ ይታወቃል።

ኤክነር ግምቱን ለሪያል ማድሪድ ሰጥቷል።

ከማድሪድ በመቀጠል ደግሞ ማንቸስተር ሲቲ እና ባየር ሙኒክ ዕድል አላቸው ብሏል።

በጣሊያን እግር ኳስ ዙሪያ ለቢቢሲ ትንታኔዎችን የምትጽፈው ሚና ዙኪ ማድሪድ የኮከብ ተጫዋቾች መሰባሰቢያ መሆኑን በድጋሚ ቢያሳይም፤ ዘንድሮ ግን ዋንጫው የማንቸስተር ሲቲ ይሆናል ብላለች።

ኤርሊንግ ሃላንድ ክረምቱን በማረፉ እና ቡድኑ ከያዘው የፈጠራ ክህሎት እና ልምድ አንጻር ዋንጫውን ያነሳል ስትል ግምቷን አስቀምጣለች።

አዳዲስ አሠልጣኝ የቀጠሩት ሙኒክ እና ባርሴሎና ጊዜ ይፈልጋሉ። አርሰናል ደግሞ ትኩረቱ የሊጉ ዋንጫ ላይ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ማንቸስተር ሲቲ በልምድ እየዳበረ በተለያዩ መንገዶች ማሸነፍን እየለመደ ነው ስትል ገልጻለች።

የውድድሩ አስደናቂ ቡድን ማን ሊሆን ይችላል?

ፊል ማክነልቲ፡ ሊቨርፑል

የርገን ክሎፕ ከቡድኑ ጋር ባይሆኑም ቡድኑ ወደ ጥሎ ማለፈ ከተሸጋገረ ለተፎካካሪዎች ከባድ ይሆናል።

በአሠልጣኝ አርን ስሎት የሚመራው ቡድን አሁንም ድንቅ ተጫዋቾችን ይዟል።

አሠልጣኙ በአውሮፓ መድረክ ያለውን ታክቲካዊ ፉክክር ለመጋፈጥ ዝግጁ ናቸው።

ጁሊየን ላውረንስ፡ ባየር ሊቨርኩሰን

አዲሱ የሻምፒዮንስ ሊግ መዋቅር ከታላላቅ ቡድኖች ውጪ ላሉ ቡድኖች ዕድል የሚሰጥ ነው።

ሊቨርኩሰን ደግሞ የውድድር ዓመቱ አስገራሚ ቡድን ሊሆን ይችላል።

ዣቪ አሎንሶ እና ቡድናቸው ባለፈው የውድድር ዓመት የሊጉን ዋንጫ ያነሱበትን ጉዞ በትልቁ መድረክ ለማሳየት ይሞክራሉ።

ጉለም ባላግ፡ ኢንተር ሚላን

ስኩዴቶው የጁቬንቱስን የበላይነት ከማስቆም በተጨማሪ በአውሮፓ መድረክ በተደጋጋሚ እየተሳተፉ ነው።

እንደ ላውታሮ ማርቲኔዝ ያሉ ኮከቦቻቸውን ከማቆየታቸውም በላይ አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርመዋል።

ኮንስታንቲን ኤክነር፡ አትሌቲኮ ማድሪድ

ቡድኑ እንድ ዩሊያን አልቫሬዝ እና ኮኖር ካላገር ያሉ ተጫዋቾችን በማስፈረም ተጠናክሯል።

ቡድኑ በአሰልጣኝ ዲዬጎ ሲሞኔ ስር ለሁለት ጊዜ ለፍጻሜ መድረሱም መዘንጋት የለበትም ብሏል።

ሚና ዙኪ፡ ኢንተር ሚላን

ቡድኑ እንደማድሪድ እና ማንቸስተር ሲቲ ሁሉ ወጥ አቋም የሚያሳይ ቡድን ገንብቷል።

ባለፈው ዓመት ትኩረታቸው በድል ባጠናቀቁበት የስኩዴቶ ዋንጫ ላይ ቢሆንም ዘንድሮ ግን ለአውሮፓ መድረክ ትኩረት ያደርጋሉ።

ዘንድሮ የሚጠበቀው ተጫዋች የትኛው ነው?

ፊል ማክነልቲ፡ ላሚን ያማል

አውሮፓ ዋንጫን ላነሳው ላሚን ያማል ቅድሚያ ሰጥቷል። ትልልቅ መድረኮች እንደሚመጥኑት በአውሮፓ ዋንጫው አስመስክሯል ብሏል።

ሁለተኛ ዕድል ከተሰጠው የማድሪዱን የ18 ዓመት ወጣት ኤድሪክን እንደሚጠብቅ አስታውቋል።

ጁሊየን ላውረንስ፡ ላሚን ያማል

ብዙ ተፎካካሪዎች ቢኖሩም አሁን ያለው ድንቁ ተጫዋች የባርሴሎናው ላሚን ያማል ነው።

17 ዓመቱ ቢሆንም መወሰን ብቃቱ አስደናቂ ነው ሲል ገልጾታል።

ጉለም ባላግ፡ ላሚን ያማል

በሊጉ የመጀመሪያዎቹ አምስት ጨዋታዎች 3 ጎሎችን አስቆጥሮ 4 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አቀብሏል።

ያማል ቡድኑን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ተጫዋች ነው ብሏል።

ኮንስታንቲን ኤክነር፡ ቪክተር ጋይኮረስ

ቪክተር ጋይኮረስ እና የስፖርቲንግ ሊዝበን የአጥቂ መስመር በሻምፒዮን ሊጉ የሚኖረውን ጉዞ ለማየት መጓጓቱን ገልጿል።

ጋይኮረስ የሚታወቅ ተጫዋች ቢሆንም በሊጉ ደካማነት ምክንያት ሊዝበን ብዙም ትኩረት አይሰጠውም ብሏል።

ሚና ዙኪ፡ ፋቢያን ሩይዝ

ፒኤስጂ እና ፋቢያን ሩይዝ ዘንድሮ የሚኖራቸውን ጉዞ ለማየት ጉጉት እንዳላት ተናግራለች።

ቡድኑ የአማካይ ስፍራው ላይ ላለው ጥያቄ ተጫዋቹ ጥሩ ምላሽ ይሆናል ብላለች።