የአርቲ ሚዲያ አርማ ሞባይል ላይ

ከ 5 ሰአት በፊት

የፌስቡክ ባለቤት የሆነው ሜታ በሚያስተዳድራቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾች አማካኝነት ሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ያልተገባ ተጽእኖ ለመፍጠር እየሞከሩ ነው በሚል በርካታ የሩሲያ መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትን ገጽ ዘጋ።

ሜታ ባወጣውወ መግለጫ “በጥንቃቄ ካደረግነው ምልከት በኋላ በሩሲያ መንግሥት ቁጥጥር ስር ያሉ መገናኛ ብዙኃን ላይ እርምጃ ወስደናል። በዚህም ሮሽያ፣ አርቲ እና ሌሎች ተመሳሳይነት ያላቸውን ተቋማት በጣልቃ ገብነት ምክንያት ከመተግበሪያዎቻችን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ አግደናቸዋል” ብሏል።

ዕገዳው በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ተግባራዊ መሆን ይጀምራል።

ቢቢሲ በዋሽንግተን ለሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ፣ ለ‘ራሽያ ቱደይ’ ወይም አር ቲ እና ለስፑትኒክ የዜና ወኪል እንዲሁም ሮሽያ ስለጉዳዮ አስተያየት እንዲሰጡ ቢጠይቀም ምላሽ አላገኘም።

የሩሲያ መንግሥት መገናኛ ብዘኃን በምዕራባውያን አገራት ፖለቲካ ላይ ተጽእኖ ለመፈጠር እየሞከሩ ነው በሚል ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገባቸው ነው።

አሁን ደግሞ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ዋትስአፕ እና ትሬድስን የሚያስተዳድረው ግዙፉ ሜታ ይህንን እርምጃ ተቀላቅሏል።

ይህ እርምጃ ሜታ በሩሲያ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ላይ እወሰደ ያለውን እርምጃ ያጠናከረበት ነው።

ከሁለት ዓመት በፊት ሜታ የእነዚህን መገናኛ ብዘኃን ተደራሽነት ለመግታት ውስን እርምጃዎችን ወስዷል። ይህም በመገናኛ ብዙኃኑ ገጽ ላይ ማስታወቂያን አለማስተላለፍ እና ተደራሽነቱን መገደብ ይጨምራል።

የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ የአውሮፓ ኅብረት፣ ዩክሬን እና ዩናይትድ ኪንግደም በግዛታቸው የሩሲያ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን መዘጋት ይገባዋል ሲሉ ቆይተዋል።

ከሁለት ሳምንታት በፊት አሜሪካ የሩሲያ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን የሆነወ አርቲ ለአንድ ተቋም 10 ሚሊዮን ዶላር በመክፈል የሩሲያ መንግሥት ደብቅ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ ሞክሯል ስትል ከሳለች።

እንደ ፆታ፣ ስደት እና ኢኮኖሚ ያሉ የቀኝ ዘምም ትርክቶች ላይ በማተኮር በሚታወቀው ተቋም በሁለት የአርቲ ሠራተኞች በድብቅ እየተዘጋጀ እንደሚቀርብ ተነግሯል።

ባለፈው ሳምንት አርቲ የሩሲያ ስለላ አካል ነው ስትል የፈረጀችው አሜሪካ በውጭ ጉዳይ ሥሪያ ቤት ኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን አማካኝነት ማዕቀብ ጥላለች።

ብሊንክን በሩሲያ መንግሥት የሚደገፈው አርቲ የአሜሪካ ዲሞክራሲን ላይ ችግር ለመፍጠር እየጣረ እንደሆነ ገልጸዋል።

ጨምረውም የሩሲያ መንግሥት አርቲ ከሩሲያ የስለላ ተቋም ጋር የተሳሰረ እና የሳይበር ተልዕኮ የተሰጠው ነው ብለዋል።

ይህንን የብሊንክን ንግግር አርቲ በኤክስ ገጹ ላይ በቀጥታ ያስተላለፈው ሲሆን “የአሜሪካ ሰሞነኛው የሴራ ትንታኔ” ሲል ገልጾታል።