ተቃዋሚ ኢራናዊት

ከ 6 ሰአት በፊት

*ማሳሰቢያ ይህ ጽሁፍ የአንባብያንን ስሜት ሊረብሹ የሚችሉ ይዘቶችን አካቷል። አንዳንድ ስሞችም ተቀይረዋል።

በኢራን የሚገኙ ሴቶች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያላቸው ተሳትፎ በመንግሥት ሹማምንት ይሰለላል። የስላለው ውጤት ታይቶ አንዳንዶች ወደ እስር ቤት ይላካሉ። ሌሎች ደግሞ ዛቻ ይደርስባቸዋል አልያም ይደበደባሉ። ይህ ኢራን የሚገኙ ሴቶች ለቢቢሲ የገለጹት ነው።

ከሁለት ዓመት በፊት በኢራን ማህሳ አሚኒ የተባለች የ22 ዓመት ሴት ሂጃብ በተገቢው መንገድ አለበሰችም በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለች። ቀጥሎ ማህሳ በፖሊስ ማቆያ ሳለች መሞቷ ተሰማ። ይህም በመላው አገሪቱ በሴቶች የሚመራ ከፍተኛ ቁጣን እና ተቃውሞን ቀሰቀሰ።

ከዚህ ጊዜ ወዲህ የኢራን መንግሥት የስለላ ተግባር ተጠናክሯል።

ከማህሳ ሞት በኋላ በኢራን ቁጥር ስፍራ የሌላቸው ሴቶች ተገደን ሂጃብ አናደርግም በሚል ፀጉራቸውን እያሳዩ አደባባይ ወጥተዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ መሰል ይዘት ያላቸውም መልዕክቶችንም አስተላልፈዋል። ወይም ፀጉራቸው የሚታይበትን ፎቶዎች አጋርተዋል።

አሌፍ ከእነዚህ ሴቶች መካከል አንዷ ነች።

ፎቶዋን በማኅበራዊ ሚዲያ የለጠፈችው ለዚህ ተቃውሞ ያላትን አጋርነት ለመግለጽ ነው።

“ማን እንደሆንኩ ለመደበቅ አስፈላጊ ነው የምለውን ጥንቃቄ ለማድረግ ግድ አልነበረኝም። ወይም ፎቶው የት ነው የተነሳው የሚለውን ለመደበቅ ግድ አልሰጠኝም። መናገር የፈለኩት ‘አለን’ የሚለውን መልዕክት ነበር” ትላለች።

አሌፍ ያ ፎቶ ግድ ባይሰጣም የተመለከተው አካል ግን ነበር።

በኢራን የተቀሰቀውን ተቃውሞ ለማዳፈን ሲሞክሩ የነበሩት የአገሪቱ ሹማምንት በዚህ ፎቶ ምክንያት አሌፍን አስረዋታል።

ዓይኗ ታስሮ እና እጇ ውስጥ ካቴና ገብቶ ወደ ማታውቀው ስፍራ መወሰዷን ትገልጻለች።

በዚህ ቦታ ወደ ሁለት ሳምንት ገደማ ሌሎች እስረኞች አጠገቧ ሳይኖሩ ታስራ ቆይታለች። የምርመራ ጥያቄዎች ሲቀርቡላትም ነበር።

በአንድ የምርመራ ጥያቄ ወቅት መሪማሪዎች ያላደርግችውን እንድታምን ጫና ሲያደርጉባት እንደነበር ትናገራለች።

በዚህ የእስር ወቅት የእጅ ስልኳን እንድትሰጥ የተደረገች ሲሆን፣ መርማሪዎቿ ስልኳ ውስጥ ያሉ ፎቶዎችን ተመልክተዋል።

የማኅበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴዎቿንም አይተዋል።

በእስር ቤት ሳለች የሞተችው ማህሳ በኢራን ከፍተኛ ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆናለች።
የምስሉ መግለጫ,በእስር ቤት ሳለች የሞተችው ማህሳ በኢራን ከፍተኛ ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆናለች

እነዚህ ፎቶዎች አሌፍ ተቃውሞዎች ውስጥ እንደተሳተፈች እና በፖሊስ የፕላስቲክ ጥይት እንደተመታች ያሳያሉ። ለአሜሪካ መንግሥት ትሠሪያላሽ የሚል ውንጀላም ቀርቦባታል።

አሌፍ “በሕዝብ ፊት ያለ ሂጃብ መቅረብ” እና “ሙስናን እና ዝሙትን ማበረታት” የሚሉ ሁለት ክሶችን ጨምሮ ሌሎች ክሶች ቀርበውበታል።

በእነዚህ ክሶች ጥፋተኛ ተብላለች። ወደ እስር ቤት ባትላክም 50 ጊዜ ተገርፋለች።

“ወንድ የፖሊስ መኮንን መጥቶ ኮቴን እንዳወልቅ ነገረኝ” ትላለች አሌፍ። ቀጥላም “ጥቁር የቆዳ አልንጋ ይዞ ነበር። በዚያ ሁሉንም የሰውነቴን ክፍሌን ገረፈኝ። እጅግ በጣም ከፍተኛ የህመም ስሜት ነበረው። ነገር ግን ደካማ መስዬ መታየት ስላልፈለኩኝ ስቃዩን ዋጣ አደርኩት” ስትል አክላለች።

ይህ ታሪክ ቢቢሲ ኢራን ውስጥ ካናገራቸው ሁለት ሴቶች እና አንድ ወንድ ጋር ይመሳሰላል። እያንዳንዳቸው ታሰርው ፍርድ ቤት መቅረባቸውን እንዲሁም “አገራቸውን የሚጻረር ፕሮፖጋንዳ ላይ በመሳተፍ” መከሰሳቸውን ይገልጻሉ። ሁሉም እስር ቢፈረድባቸውም አልታሰሩም።

የእስር ጊዜ

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት ሰዎች ከዚህ ተቃውሞ በኋላ ፍርድ ቤት ከመቅረባቸው እና ብያኔ ከመሰጠቱ አስቀድሞ በኢራን የፓለቲካ እስረኞች ወደሚታሰሩበት ታዋቂ እስር ቤት ተልከዋል።

ሁለቱ ሰዎች በእስር ቤቱ እጅግ የተበላሸ አያያዝ እንዳለ ይገልጻሉ።

እስር ቤቱ እጅግ ጠባብ፣ ንጽህና የሚጎድለው እንዲሁም መታጠቢያ እና መጸዳጃ ቤት ‘ብርቅ’ በሚባል ሁኔታ እንዳለበት ይነገራል። በዚህም ሳቢያ ታሳሪዎች ለበሽታ ይጋለጣሉ።

ቢቢሲ ከአንድ ወር በታች ለሆነ ጊዜ የታሰረ በኢራን ታዋቂ የሆነ አንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪን አነጋግሯል።

ግለሰቡ በዚያ እስር ቤት አንድ ወለል ላይ ያለው አንድ መታጠቢያ እና አንድ መጸዳጃ ቤት እንደሆነ ገልጾ፤ አንድ መጸዳጃ ወይም መታጠቢያ ቤት 100 ለሚጠጉ እስረኞችን እንደሚያገለግል ተናግሯል።

ማራል የተባለች ሌላ ሴት ደግሞ ከሁለት ወር በላይ ባሳለፈችበት የሴቶች እስር ቤት እስረኞች ገላቸውን የሚታጠቡት በሳምንት አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ብቻ እንደሆነ ትናገራለች።

ይህ ሁኔታ በተለይ የወር አበባ ላይ ለሆኑ ሴቶች አጅግ ፈታኝ ነው።

“አንዳንደ ጊዜ ለሰዓታት ወደ መጸዳጃ ቤት እንዳንሄድ ይከለክሉናል” የምትለው ማራል “አልፎ አልፎ ምሬታችንን ስንገለጽ ‘የምትተባበሩን ከሆነ በቅርቡ ትለቀቃላችሁ’ ይሉናል። የንጽህና መጠበቂያ እጃችን ስለሌለ መግዛት ይኖርበናል። ገንዘብ ግን የለንም። ገንዘቡን ከቤተሰቦቻችን ለመውሰድ ደግሞ አሳሪዎቻችን ፍቃደኛ አይሆኑም ” ትላለች።

ከአድማ በታኝ ፖሊስ በተተኮሰባት የፕላስቲክ ጥይት አንደ ዓይኗን ያጣችው ኮሳር
የምስሉ መግለጫ,ከአድማ በታኝ ፖሊስ በተተኮሰባት የፕላስቲክ ጥይት አንደ ዓይኗን ያጣችው ኮሳር

ኮሳር ኤፍቴካር በማኅበራዊ ሚዲያ የነበራት ተሳተፎ ተፈትሾ ለእስር ተዳርጋለች። “አገርን የሚጻረር ፕሮፖጋንዳ መሥራት”፣ “የሚከበሩ የእምነት ድንጋጌዎችን በመስደብ”፣ “የሕዝብን አመለካከት በመረበሽ” እና “ስድብ” የሚሉ ክሶች ቀርበውባታል።

በኢራን ለተቀሰቀሰው ተቃውሞ መነሻ የነበረው ማህሳ አሚኒ ከሞተች እና ተቃውሞ ከተቀሰቀሰ አንድ ወር በኋላ በተቃውሞ የተሳተፈችው ኮሳር በፖሊስ በተተኮሰባት የፕላስቲክ ጥይት መራቢያ አካሏ ላይ ተመትታለች።

ይህ ከሆነ ከቅጽበቶች በኋላ በተመሳሳይ ጥይት ዓይኗ ተመቷል። ይህ ጥይት የአንድ ዓይኗን ዕይታ እንድታጣ ምክንያት ሆኗል።

ይህ ኮሳር ላይ ያጋጠመው ክስተት ተቀርጿል። መቀረጽ ብቻም ሳይሆን በኢንስታግራም ተሠርጭቷል። ይህ ሁኔታ ግን ኮሳርን አላስቆማትም። ከደረሰባት ጉዳት እና ሰቆቃ በላይ በማኅበራዊ ሚዲያ ንቁ ተሳታፊ ሆናለች። በዚህም ምክንያት በደኅንነት ክትትል ውስጥ ወድቃለች።

ፍርድ ቤት ስትቀርብ በእጅ ስልኳ የተገኙ እና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የለቀቀቻቸው ያለሂጃብ ያሉ ፎቶዎች በዐቃቢያነ ሕጎች እንደማስረጃ ቀርበዋል።

ጥፋታኛ ተብላ በእስር ቤት አራት ዓመታት ከሦስት ወር እንድታሳልፍ ተፈርዶበታል። በተጨማሪም ማኅበራዊ ሚዲያ እና ዘመናዊ ስልኮችን ለእምስት ዓመታት እንዳትጠቀም ተወስኖባታል።

ነገር ግን ኮሳር ከእስር ሸሽታ ወደ ጀርመን ተጉዛለች።

አሁን በዚያ ለኢራናውያን ሴቶች ደምጽ ለመሆን እየሠራች ነው። ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ በመንግሥታቱ ድርጅ የኢራን እውነታ አፈላላጊ ተልዕኮ “በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል” ተብሎ የተገለጸው ድርጊትን በተመለከተ ንግግር አደርጋለች። የደረሰባትንም አስረድታለች።

የመንግሥታቱ ደርጀት ተልዕኮ አስተባባሪዎች “ማንም ሰው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በጻፈው ሰላማዊ ይዘት ባለፈው ጽሁፍ ሊታሰር አይገባውም” ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አምስት የተለያዩ ሰዎች ያቀረቡትን ጉዳይ አስመልቶ ቢቢሲ ለኢራን መንግሥት ጥያቄ አቅርቧል። ግን ምላሽ አላገኘም። የኢራን አድማ በታኝ ፖሊስ አዛዥ ከዚህ ቀደም፣ የሚያዙት ሠራዊት ተቃዋሚዎች ላይ ፊት ለፊት ተኩሷል መባሉን አስተባብለዋል።

ኢራናውያን ሴቶች
የምስሉ መግለጫ,ከሁለት ዓመት በፊት በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ኢራናውያን ሴቶች አስገዳጁን የሂጃብ መልበስ ደንብ በመቃወም በአደባባይ በይፋ ታይተዋል

‘ዙሪያ ገባን በደኅንነት ክትትል ሥር ማስገባት’

የኢራን መንግሥት ሹማምንት መንግሥትን የሚቃወሙ ዜጎች ላይ የደኅንነት ክትትል ለዓመታት ሲያደርግ ቆይቷል። በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ ንቁ ተሳትፎ ያላቸው ኢራናውያን ላይ መንግሥት የሚያደርገውን ቁጥጥር አጠናክሯል።

ሹማምንቱ በተደጋጋሚ ኢንተርኔት አቋርጠዋል። አንዳንዴም የተለያዩ ስልቶችን በጠቀም ዒላማ የሆኑ ሰዎችን የእጅ ስልክ በመጥለፍ መረጃዎቻቸውን ለመበርበር ጥረት እንዳደረጉ ይነገራል።

እንደ ኢንስታግራም፣ ኤክስ እና ቴሌግራም ያሉ የምዕራባውያን የማኅበራዊ የትስስር ገጾች በኢራን ተዘግተዋል። ሆኖም በርካታ ኢራናውያን እንደ ‘ቨርችዋል ፕራይቬት ኔትወርክ’ ወይም ‘ቪፒኤን’ ያሉ ስልቶችን በጠቀም የኢራን መንግሥት ዕገዳን ጥሰው እነዚህን ማኅበራዊ ገጾች ይጠቀማሉ።

በቅርቡ በተቀሰቀሰ ሌላ ተቃውሞ በእነዚህ ማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት የተለያዩ የተቃውሞ ሰነዶች ሲዘዋወሩ ተስተውሏል። ነገር ግን መንግሥት በዘረጋው የክትትል መረብ ታቀውሞው በተቀሰቀሰ ጥቂት ወራት ውስጥ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ታስረዋል።

‘አርቲክል 19’ በተባለ የሰብዓዊ መበት ተሟጋች ድርጅት ውስጥ የምትሠራው ማሻ አሊማርዳኒ በዚህ ተቃውሞ የሚሳተፈው አብዛኛው አዲሱ ትውልድ ነው ትላለች።

ይህም በመሆኑ መጠነ ሰፊ የዲጂታል እንቅስቃሴ ስላላቸው መንግሥት በቀላሉ ተከታትሎ ሊይዛቸው በሚያስችሉት የማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀሚያ መሳሪያዎች በኩል ‘አሻራ’ ትተው ያልፋሉ።

በተጨማሪም የመንግሥት ሹማምንት ‘ናዜር’ የተባለ መተግበሪያ እንዲበለጽ አደርገዋል። መተግበሪያው በፖሊሶች እና በመንግሥት በተመለመሉ በጎ ፍቃደኞች ሂጃብ ያልለበሱ ሴቶችን ለመጠቆም የሚውል ነው።

በሌላ በኩል መንግሥት የተወሰነውን የኢንተርኔት መረብ ወደራሱ በመጠቅለል አገልግሎቱን ለተጠቃሚዎች በርካሽ ያቀርባል። ይህንን መረብ መጠቀም ማለት መረጃን ለመንግሥት አሳልፎ መስጠት ማለት ነው።

በኢራን ከፍተኛ ቁጣን የቀሰቀሳው የማህሳ አሚኒ ሞት ከተሰማ ሁለት ዓመታት ተቆጥሯል። ነገር ግን በአገሪቱ የሴቶች ነጻነት መብት ይከበር የሚለው ተቃውሞ የመቀዛቀዝ ምልክት አላሳየም።

አሌፍ “አሁን በቤተሰብ እና ጓደኞቻችን ሰብስብ ብለን እናወራለን። በዚህ ስብስብ ስለሴቶች የመብት ነጻነት የተጀመረው እንቅስቃሴ ላይ እንነጋገራለን። አሁን የዘራነው እያፈራ ይመስላል። ያ ዘር የማያፈራ ቢመሰልም እንኳ የሆነ ቦታ ማበቡ፣ ማፈራቱ አይቀርም” ብላለች።