የጥቃቱ ሰለባዎች
የምስሉ መግለጫ,በማኅበራዊ ሚዲያ የተጋራ ቪዲዮ በዋድ አል ኑራህ የበርካታ ሰዎች አስክሬን ተደርድሮ ያሳያል።

ከ 6 ሰአት በፊት

ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ጽሑፍ አንዳንድ አንባቢዎችን ሊረብሹ የሚችሉ ይዘቶች አሉት።

ለ40 ዓመቱ አርሶ አደር አሊ ኢብራሂም ቅዠት የሚመስለው ክስተት የጀመረው ሰኔ 5 ቀን ከሰዓት በኋላ ነበር።በዕለቱ የከባድ የጦር መሳሪያዎች ድምፅ ከየአቅጣጫው ይሰማ ጀመር።

“ከልጅነታችን ጀምሮ እንዲህ ዓይነት ድምጽ ሰምተን አናውቅም።” የሚለው አሊ የቦምብ ጥቃቱ ለአራት ሰዓታት ያህል እንደቆየ፣ ቤቶች እንደወደሙ፣ ለማምለጥ ምንም አቅም የሌላቸው ሕፃናት፣ ሴቶችና አረጋውያን ሲጮሁ እንደነበር ተናግሯል።

በዋድ አል ኑራህ መንደር በተፈጸመው በዚህ ጥቃት ቢያንስ 100 ንፁሃን ዜጎች መገደላቸውን በአካባቢው በበጎ ፈቃደኞች የሚንቀሳቀሰው ተቃዋሚ ኮሚቴ ግምቱን አስቀምጧል።

አሊ እንደሚለው የመንደሩ ነዋሪዎች ያልታጠቁ ነበሩ።“እኛ ገበሬዎች ነን።መሳሪያ ይዘን አናውቅም።ጠላቶች የሉንም።እኛ ሕይወታችንን ለማሸነፍ የምንጥር ዜጎች ነን።” ብሏል።

ጥቃቱን የሚያሳይ ከማኅበራዊ ሚዲያ የተገኘ ምሥል
የምስሉ መግለጫ,በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋራ ቪዲዮ አስክሬኖች ለጅምላ ቀብር ሲዘጋጁ አሳይቷል።

ቢቢሲ ከጥቃቱ የተረፉ የበርካታ ሰዎችን ምስክርነት ሰምቷል።ከሱዳን ጦር ጋር የሚዋጋው የአርኤስኤፍ ተዋጊዎች ቡድን መንደሩን ወርሮ ተኩስ ከፍቶ በፈጸማቸው ሁለት ተከታታይ የከባድ መሳሪያ ጥቃቶች በርካታ ነዋሪዎችን ተገድለዋል፤በርካቶችም ቆስለዋል።

በአገሪቱ ጦር ሠራዊት እና በአርኤስኤፍ መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከጀመረ ወዲህም በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር የተመዘገበበት ክስተት ሆኗል።

ሆስፒታል የሚገኙ እና ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች
የምስሉ መግለጫ,ከዋድ አል ኑራህ ጥቃቱ የተረፉ ሰዎች በአል ማናጊል የመንግሥት ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው ነው።

ቢቢሲ ከዋድ አል ኑራህ ጥቃት የተረፉትን እና ለህክምና ወደ አል ማናጊል የመንግሥት ሆስፒታል የተወሰዱትን በርካታ ሰዎችን ማነጋገር ችሏል።

ዘጋቢዎችም በማኅበራዊ ሚዲያ የተጋሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ተንትነዋል።

ሆስፒታሉ የሚገኘው ከመንደሩ በ80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሲሆን ከጥቃቱ ከሰዓታት በኋላ በሕይወት የተረፉ ብዙ ሰዎች ሆስፒታል ደርሰዋል።የዓይን እማኞቹ የአርኤስኤፍ ኃይሎች መንደሩን ለቀው እንዳይወጡ ለማድረግ ከመሞከር ባለፈ በርካታ ተሽከርካሪዎች መዝረፋቸውን ተናግረዋል።

ከጥቃቱ ተርፈው ህክምና በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ሰዎች
የምስሉ መግለጫ,ከጥቃቱ የተረፉት እንዲህ ዓይነት የቦምብ ጥቃት አይተው እንደማያውቁ ተናግረዋል።

በቦምብ ጥቃቱ ወቅት “ለሰዓታት የቆየውን ሽብር” ተቋቁመው ከቆዩ በኋላ፣ የቆሰሉትን ለማጓጓዝ እና በጥቃቱ የተገደሉትን ለመቅበር ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውንና በቀጣዩ ቀን ጠዋት ላይ በመንደራቸው በደረሰው ሁለተኛ የአርኤስኤፍ መጠነ ሰፊ ጥቃት ነዋሪዎቹ መደናገጣቸውን ከጥቃቱ ተርፈው ሆስፒታል በህክምና ላይ የሚገኙ ግለሰብ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“እኛ ቤት ገብተው እኔን እና ወንድሞቼን ደበደቡን። ‘ወርቁ የት አለ?’ ብለው ጠየቁኝ።ታናሽ እህቴ ፈርታ እናቴ ወርቁን እንድትሰጣቸው ነገረቻት።በቢሊዮን የሚቆጠር የሱዳን ፓውንድ የሚያወጣ ወርቅ ነው።”

1 ዶላር በ2600 የሱዳን ፓውንድ ይመነዘራል።

ሌሎች ከጥቃቱ የተረፉ የዓይን እማኞችም ተመሳሳይ ምስክርነት ነው የሰጡት።“ሁሉም የአርኤስኤፍ ኃይሎች መንደሩን በሦስት አቅጣጫ መውረራቸውን፣ ቤት ገብተው ሲቪሎችን እንደገደሉ፣ወርቅ፣ መኪና እና የግብርና ምርቶችን ጨምሮ ውድ ንብረቶችን መዝረፋቸውን” አረጋግጠዋል።

‘ወንድሜን ገደሉት’

የ42 ዓመቱ ሃማድ ሱሌይማን በንግድ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ነው ሕይወቱን የሚመራው።ሃማድ የአርኤስኤፍ ተዋጊዎች ወንድሙ ቤት ገብተው ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ መተኮስ እንደጀመሩ ተናግሯል።

“ወደ ወንድሜ ቤት ሄጄ እዚያ አገኘኋቸው. . . ወንድሜን እና የወንድሜን ልጅ በጥይት ተኩሰው ገድለዋቸዋል። ሌላኛው የወንድሜ ልጅ ቆስሎ እዚህ ሆስፒታል ከእኔ ጋር አለ።” ሲል ስለተፈጠረው አስረድቷል።

ከአርኤስኤፍ ተዋጊዎች ቤተሰቦቹ የተገደሉበትን ምክንያት ለማወቅ እንደሞከረ ተናግሯል።

“ላናግራቸው ሞከርኩኝ። ሻሃዳ (ሰው ለሞት ሲቃረብ የሚነበበው እስላማዊ ጸሎት) እንዳነብ ነገሩኝ።ከዚያ እጄ ላይ ተኩሰው ሸሹ . . . መኪናዎቼን ሁሉ ዘረፉ።በመቁሰሌ ምክንያት ለሰዓታት መውጫ መንገድ ማግኘት አልቻልኩም ነበር።” ብሏል።

ከከተማዋ የሚሸሹ ሰዎች
የምስሉ መግለጫ,ጥቃቱን ተከትሎ በርካታ ነዋሪዎች ዋድ አል ኑራህ ከተማን ለቀው ወጥተዋል።

ቢቢሲ ከአደጋው የተረፉ ሰዎችን ምስክርነት በማንሳት ስለጥቃቱ፣ ግድያው፣ ዘረፋው እና ማስፈራሪያው ክስ አርኤስኤፍን አነጋግሯል።ሆኖም ከቡድኑ ወዲያውኑ ያገኘው ምንም ዓይነት ምላሽ የለም።

ድርጊቱ ከተፈጸመ ከአንድ ቀን በኋላ ግን የአርኤስኤፍ ቃል አቀባይ አል ፈትህ ቁራሺ በኤክስ ገጻቸው ላይ የቪድዮ መግለጫ ያወጡ ሲሆን ቡድኑ ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ አድርጓል መባሉን አስተባብለዋል።

ሆኖም ጦሩ በጥቃቱ ወቅት በመንደሩ ውስጥ ከነበሩት ከሱዳን ጦር ኃይሎች (ኤስኤኤፍ) እና ከስለላ ባልደረቦቻቸው በተጨማሪም ‘አል ሙስተንፋሮን’ ተብሎ ከሚጠራው ትናንሽ መሳሪያዎችን ከያዙ እና ከኤስኤኤፍ ጋር ከተሰለፉ አካላት ጋር መፋለሙን ገልጸዋል።

ከመንደሩ ውጭስ?

የቢቢሲ መረጃ አጣሪ ቡድን በዋድ አል ኑራህ ውስጥ አል ሙስታንፋሮን የተጠቀመባቸውን ቦታዎች እና ምሽጎችን የሚያሳዩ ምስሎች ናቸው በሚል በአርኤስኤፍ የቀረቡ ቪዲዮዎችን ተንትኗል።ትንታኔው እነዚህ ቦታዎች ከመንደሩ ውጭ እንጂ በመንደሩ ውስጡ እንዳልሆኑ አረጋግጧል።

የአርኤስኤፍ አባላት ከአንድ ማይል ርቀት ላይ ከባድ መሳሪያዎችን ተጠቅመው ወደ መንደሩ ተኩስ እንደከፈቱ ትንታኔው ያሳያል።

ዋድ አል ኑራህ በገዚራ ግዛት ከሚገኙ በመቶዎች ከሚቆጠሩ መንደሮች ጋር ተመሳሳይ ነው።አብዛኛው ነዋሪ በእርሻ እና በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራ ሲሆን ከአጎራባች መንደር ነጋዴዎች ከብቶችን እና ሰብሎችን ለመግዛት እና ለመሸጥ የሚመጡበት አነስተኛ ሳምንታዊ ገበያ አለው።

አርኤስኤፍ በታኅሳስ ወር 2023 ከዋና ከተማዋ ካርቱም በስተደቡብ የሚገኘውን የገዚራ ግዛትን የተቆጣጠረ ሲሆን በዚያም በሰላማዊ ሰዎች ላይ ብዙ በደል ፈጽሟል ተብሎ ተከሷል። ቡድኑ ግን ይህንን ውንጀላ ደጋግሞ አስተባብሏል።

ገዚራ በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ክልሎች አንዱ ነው።ከካርቱም እና ከዳርፉር ለሚሰደዱ በሺዎች ለሚቆጠሩ ተፈናቃዮችም መሸሸጊያ ሆኗል።

አርኤስኤፍ ባለፈው ዓመት መጨረሻ አካባቢውን ከተቆጣጠረበት ጊዜ አንስቶ እያንዳንዱ መንደር በየተራ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።

አርኤስኤፍ እንደ ግድያ፣ ዘረፋ፣ አስገድዶ መድፈር እና መንደሮችን ማቃጠል ያሉ የጦር ወንጀሎችን መፈጸሙን በመካድ በምትኩ ጣቱን “የማይታዘዙ” በሚላቸው ሰዎች ላይ መቀሰሩን ቀጥሏል።

በጥቃቱ ከቀያቸው ተፈናቀሉ ሰዎች

ምርመራ እንዲካሄድ የሚደረጉ ጥሪዎች

እንደ የተባበሩት መንግሥታት ዘገባ ከሆነ በሱዳን ያለው ጦርነት ለ14 ሺህ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል።ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉም አድርጓል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሱዳን የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ክሌመንት ንክዌታ ሳላሚ የዋድ አል ኑራህ ጥቃትን ለመረዳት አጠቃላይ እና ግልጽ የሆነ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

በርካታ ዘመዶቻቸውን ያጡ የመንደሩ ነዋሪዎችም፣ ከዚህ ቀደም በሱዳን እንዳጋጠመው ሁሉ ወንጀለኞች ከሚጣልባቸው ቅጣት እንዳያመልጡና በሕግ እንዲጠየቁ አጣሪ ኮሚቴ ይቋቋማል የሚል ተስፋ አላቸው።