በጎንደር ከተማ የሚገኘው የአጼ ቴዎድሮስ አደባባይ

ከ 34 ደቂቃዎች በፊት

በታሪካዊቷ በጎንደር ከተማ እና በዙሪያዋ በሚገኙ ሌሎች አካባቢዎች ሰሞኑን በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከፍተኛ ውጊያ መደረጉን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

የሰሜን ጎንደር ዞን መቀመጫ በሆነችው በደባርቅ እንዲሁም በዳባት እና በአምባ ጊዮርጊስ ከተሞች ውጊያው ሲደረግ የሰነበተ ሲሆን፣ ዛሬ ደግሞ በማዕከላዊ ጎንደር ዋና ከተማ በሆነችው ጎንደር የተለያዩ አካባቢዎች የተኩስ ልውውጥ መኖሩን ነዋሪዎቹ አረጋግጠዋል።

ሰኞ መስከረም 6/2017 ዓ.ም. ደባርቅ ከተማ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ሲካሄድ እንደነበር የተናገሩት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የከተማዋ ነዋሪ፣ “በነበረው ውጊያ ብዙ ሰላማዊ ሰዎች ተጎድተዋል” ብለዋል።

በደባርቅ ሆስፒታል የሕክምና ባለሙያ እንደሆኑ የነገሩን ሌላኛው ነዋሪ ደግሞ ከተማዋ ሙሉ ቀን በተኩስ ስትናጥ መዋሏን ተናግረዋል። በነበረው ከፍተኛ ውጊያ ምክንያት ሰኞ ዕለት፣ መስከረም 6 2017 ዓ.ም. ብቻ ከ20 በላይ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ዛሬ [ማክሰኞ መስከረም 7] በተመሳሳይ ቁስለኞች ወደ ሆስፒታል እየሄዱ መሆናቸውን ተናግረው፤ ሆስፒታል ውስጥ ሕክምና ሲከታተሉ ከነበሩት ሰዎች መካከል ሁለቱ ወዲያውኑ ሕይወታቸው አልፏል ብለዋል።

ነገር ግን በነበረው ግጭት ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ወደ ሆስፒታል ሳይሄዱ ሕይወታቸው ያለፈ በርካቶች መሆናቸውን የህክምና ባለሙያው አመልክተዋል።

ሰኞ ዕለት በነበረው የተኩስ ልውውጥ የሞቱ ሰዎችም ዛሬ [ማክሰኞ] በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ቀብራቸው ነዋሪዎች ለቢቢሲ የገለጹ ሲሆን፣ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ነዋሪ ደግሞ እርሳቸው በተገኙበት በደባርቅ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ብቻ “ዛሬ [07/01/17 ዓ.ም] 15 ያህል ሰዎች ተቀብረዋል” ብለዋል።

ዛሬ [ማክሰኞ] ረፋድ ላይም በደባርቅ ከተማ የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበር ነዋሪዎች ተናግረዋል። ከእኩለ ቀን በኋላ የተኩስ ድምጹ የቀነሰ ቢሆንም ወደ ገጠር የወረዳው አካባቢዎች የሚካሄደው የተኩስ ልውውጥ እና የከባድ መሣሪያ ተኩስ ግን እንደቀጠለ ነው ብለዋል።

በአካባቢው የሚገኙ አብዛኞቹ የንግድ እና ሌሎች እንቅስቃሴዎች በግጭቱ ምክንያት ዝግ ሲሆኑ፣ የሰዎች እንቅስቃሴም አልፎ አልፎ ብቻ እንደሚስተዋል ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ዳባት እና አምባ ጊዮርጊስ ከተሞችም በተመሳሳይ ከትናንት ሰኞ [መስከረም 6] ጅምሮ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ እየተካሄደባቸው መሆናቸውን ሁለት ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በዚህ የተኩስ ልውውጥ ምክንያት ዳባት ላይ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ብዙ ነዋሪ ለደኅንነታቸው በመስጋት ከከተማው በመውጣት ወደ ገጠር አካባቢዎች እየሸሹ መሆናቸውን ቢቢሲ ከነዋሪዎች ሰምቷል።

ሰኞ በታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል በተካሄደው ግጭት ቢያንስ ሦስት ሰላማዊ ሰዎች ተገድዋል ያሉ አንድ ነዋሪ፣ ይህም በነዋሪዎች ላይ ፍርሃትን ፈጥሯል ብለዋል። ነዋሪው አክለውም ሕይወታቸው የጠፋው ሰላማዊ ሰዎች በየትኛው ወገን እንደተገደሉ ግን መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል።

በሰሜን ጎንደር ወገራ ወረዳ የአምባ ጊዮርጊስ ከተማ ነዋሪ የሆኑ እና ማንነታቸውን እንዲገለጽ ያልፈለጉ ግለሰብ “ትናንት [ሰኞ] ለተወሰኑ ሰዓታት ውጊያ ከተደረገ በኋላ የፋኖ ታጣቂዎች ወደ ከተማዋ ዘልቀው ገብተዋል” ብሏል።

አሁንም [ማክሰኞ ረፋድ] በከተማዋ የፋኖ ታጣቂዎች መኖራቸውን የገለጹት ነዋሪው፣ ከከተማው ወጣ ብሎ ደግሞ የመከላከያ ሠራዊት በካምፕ ውስጥ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በከተማዋ ዳርቻ ላይ ባሉ አካባቢዎች አሁንም የተኩስ ልውውጥ መኖሩን ተናግረዋል።

በአምባ ጊዮርጊስ ከተማ ዛሬ ማክሰኞ አንጻራዊ የሰዎች እንቅስቃሴ ቢኖርም የንግድ እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲሁም የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ግን አሁንም እንደተገደበ ነው።

ከሰሜን ጎንደር ወረዳዎች በተጨማሪ ሌሎች የማዕከላዊ ጎንደር አካባቢዎችም ባለፉት ቀናት ከፍተኛ ውጊያ ሲካሄድባቸው እንደሰነበተ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት ከጎንደር ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኙ አካባቢዎች ሲደረግ የሰነበተ ቢሆንም፣ ባለፉት ቀናት ጎንደር ከተማ አንጻራዊ ሰላም ነበራት።

በዙሪያዋ ሲካሄድ የነበረው የተኩስ ልውውጥም አድማሱን አስፍቶ ዛሬ ማክሰኞ ንጋት ላይ የጎንደር ከተማ ዳርቻዎች ላይ መድረሱን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የጎንደር መሃል ከተማ አካባቢ መደበኛ እንቅስቃሴ እንደቀጠለ ቢሆንም፣ በከተማዋ መግቢያ እና መውጫ አካባቢዎች የተኩስ ልውውጥ እየተካሄደ መሆኑን ሦስት የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በተለይ አዘዞ፣ ቀበሌ 18፣ አዲስ ዓለም፣ አይራ እና ዓለም በር በሚባሉ አካባቢዎች ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ እየተደረገ መሆኑን ነዋሪዎቹ ለቢቢሲ ገልጸው፤ በእነዚሁ አካባቢዎችም መደበኛ እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ተቋርጧል።

በአካባቢዎቹም የመንግሥት ኃይሎች እንቅስቃሴ በስፋት የሚታይ ሲሆን፣ የተኩስ ድምጹም ጎንደር ከተማ ማዕከላዊ ክፍል ድረስ ይሰማ እንደነበር ገልጸው ከዕኩለ ቀን በኋላ ግን መጠኑ መቀነሱን ተናግረዋል።

ቢቢሲ ከአማራ ክልል፣ ከሰሜን ጎንደር ዞን እና ከጎንደር ከተማ የመንግሥት አካላት በአሁኑ ጊዜ በአካባቢዎቹ ስላለው ሁኔታ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ በጎንደር ቀጠና በተለያዩ አካባቢዎች በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መካከል ተደጋጋሚ ግጭቶች ሲደረጉ ቆይተዋል።

በዚህም ሳቢያ በነዋሪዎች ላይ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱን እንዲሁም አንዳንዶች በደኅንነት ስጋት ምክንያት አካባቢያቸውን በመልቀቅ ወደ ገጠር አካባቢዎች መሸሻቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በተጨማሪም በአንዳንድ አካባቢዎች የመንግሥት አገለግሎቶች፣ የንግድ እና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ሙሉ በሙለ ተስተጓጉሎ ሰንብቷል።

ከአንድ ዓመት በላይ የሆነው በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው የመንግሥት ኃይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች ግጭት እየረገበ እና መልሶ እያገረሸ የቆየ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በርካታ በሚባሉ ቦታዎች ላይ ግጭቶች እየተካሄዱ መሆናቸውን ነዋሪዎች እና የሚወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ።