ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ
የምስሉ መግለጫ,ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ

ከ 3 ሰአት በፊት

የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሊቀ መንበር አንጋፋው ምሁር እና ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

የፕሮፌሰሩን ማለፍ ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ “[ፕ/ር በየነ] ረዘም ላለ ጊዜ በህክምና ሲረዱ ቆይተው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውንን ስሰማ ከልብ አዝኛለሁ” ብለዋል።

ፕሮፌሰር በየነ ከታኅሣሥ 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በመንግሥታዊው የፖሊሲ ጥናት ኢንስትዩት አምስተኛው ዳይሬክተር ጄነራል ሆነው ሲያገለግሉ ነበር። ፕሮፌሰሩ ይህን ሹመት ያገኙት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ረፋድ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በኢትዮጵያ ገንቢ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ምልክት ነበሩ” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የተወለዱት መጋቢት 2/1942 ዓ.ም. በአሁኑ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን ነው።

ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ በተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኝነት ስማቸው በጉልህ ከሚነሳ ፖለቲከኞች መካከል ናቸው። በሽግግር ወቅት የደቡብ ፓርቲዎችን ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን አስተባብረው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲ ኅብረት የተባለ የፖለቲካ ድርጅት በመመሥረት 17 መቀመጫ ይዘው ነበር።

የደርግ መንግሥት ወድቆ በኢህአዴግ አስተባባሪነት በተቋቋመው የሽግግር መንግሥት ወቅት ምክትል የትምህርት ሚኒስትር ሆነው ተሹመው ለሁለት ዓመት አገልግለዋል። በ1992 ዓ.ም. በሁለተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተወዳድው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልም ሆነው ነበር።

በምክር ቤት ቆይታቸው ወቅትም በሕዝቡ ውስጥ ያሉ አሳሳቢ ጉዳዮችን በማንሳት በመሞገት በአንድ ፓርቲ የበላይነት በተያዘው ምክር ቤት የተለየ ድምጽ ሆነው ቆይተዋል።

ፕሮፌሰ በየነ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በነበራቸው ተሳትፎ ቁጥራቸው የበዛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት ፈጥረው ተጽእኖ እንዲኖራቸው የበኩላቸውን እንዳደረጉ ይነገርላቸዋል።

በዚህም በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ከቅንጅት ጋር ዋነኛ ተፎካካሪ የነበረውን ኅብረት እንዲሁም ከዚያ በኋላ መድረክ የተባሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረትን ካቀወቋሙ ቁልፍ ፖለቲከኞች መካከል ተጠቃሹ ናቸው።

ፕሮፌሰር በየነ በፖለቲከኛነታቸው ይታወቁ እንጂ አንቱ የተባሉ ሥነ ሕይወት (ባዮሎጂ) ሊቅም ናቸው።

በ1965 ዓ.ም. የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ሕይወት አግኝተዋል ከዚያም ወደ አሜሪካ አቅንተው የከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።

የማስተርስ ዲግሪያቸውን ከአሜሪካው ዊስኮንሲን ዩኒቨርሲቲ የተቀበሉት ፕሮፌሰር በየነ፤ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ ከቱሊን ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል።

ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በርካታ የድኅረ ምረቃ እና የዶክትሬት ተማሪዎችን አስተምረዋል፣ አማክረዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍል ሊቀ መንበር በመሆን የአካዳሚክ እና የምርምራ ሥራቸውን የጀመሩት ፕሮፌሰር በየነ የኢትዮጵያ ባዮሎጂካል ሶሳይቲ መሥራች እና ፕሬዝዳንት ነበሩ።

ፕሮፌሰር በየነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በወባ እና በሌሎች ጥገኛ ተውሳኮች ላይ ያተኮሩ የምርምር ፕሮጀክቶችን መርተዋል።

በተጨማሪም በበርካታ ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና አገር አቀፍ የሙያ ማኅበራት ውስጥ አማካሪ ቦርድ እና የኮንፈረንስ አዘጋጅ ኮሚቴዎችን በመምራት አገልግለዋል።

ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በሕዝብ ተሳትፎ፣ በአካዳሚክ ውጤታቸው እና በምርምር መሪነት ብዙ ዓለም አቀፍ እና አገር አቀፍ ሽልማቶችን እና የወርቅ ሜዳሊያዎችን አሸንፈዋል።

ምሁሩ በየነ ጴጥሮስ በሙያቸው ወደ 120 የሚጠጉ በአቻ የተገመገሙ ሳይንሳዊ የጥናት ጽሁፎችን በጥናታዊ መጽሔቶች ላይ አሳትመዋል።