ደብረጽዮን (ዶ/ር) እና አቶ ጌታቸው
የምስሉ መግለጫ,ደብረጽዮን (ዶ/ር) እና አቶ ጌታቸው

ከ 5 ሰአት በፊት

በደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው አዲሱ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 16 ከፍተኛ አመራሮቹን ከፓርቲው ፖለቲካዊ ሥራዎች ማገዱን አስታወቀ።

ይህንንም ተከትሎ የታገዱት አመራሮች፣ በህወሓት ውክልና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ያላቸው ኃላፊነት ላይ ማስተካከያ እንዲደረግ እንደሚፈልግ ገልጿል።

ህወሓት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ እና በከፍተኛ አመራሮቹ ተቀባይነት ሳያገኝ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ባደረገው 14ኛ ጠቅላላ ጉባዔው ላይ ያልተሳተፉ ከፍተኛ አመራሮቹን በፓርቲው ውስጥ ካላቸው ኃላፊነት ማንሳቱን አሳውቆ ነበር።

አሁን ደግሞ ከአንድ ወር በኋላ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ከህወሓት ጋር የተያያዘ ማንኛውንም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ማገዱን ሰኞ አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ህወሓት ደም አፋሳሹ ጦርነት ካበቃ እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከተመሠረተ በኋላ በአመራሩ ውስጥ ልዩነት ተፈጥሮ በተለያዩ ጊዜያት ተደጋጋሚ ረጃጅም ስብሰባዎችን ቢያደርግም፣ ለገጠመው ችግር መፍትሄ ሳያገኝ አመራሮቹ በተለያየ አቋም ላይ ሆነው እየተወዛገቡ ይገኛሉ።

የድርጅቱ ሊቀመንበር በመሩትና ጥቂት የማይባሉ አመራሮቹ እና አባላቱ ባልተሳተፉበት ጠቅላላ ጉባኤ የተለየ አቋም የያዙት እና በጉባኤው ያልተሳተፉት አመራሮችን ከኃላፊነት አንስቶ ደብረ ጽዮን በሊቀመንበርነት እንዲቀጥሉ መወሰኑ ይታወሳል።

ነገር ግን የአገሪቱ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ሕግን የተከተለ አይደለም በሚል ዕውቅና እንደማይሰጠው ማሳወቁ ይታወሳል።

በጠቅላላ ጉባኤው ከአመራርነት ተነስተው በተራ አባልነት እንዲቆዩ ተወስኖባቸዋል የተባሉት አቶ ጌታቸው ረዳ እና ሌሎች የፓርቲው ባለሥልጣናት በደብረ ጽዮን (ዶ/ር) የሚመራው ማዕከላዊ ኮሚቴ ከህወሓት እንዳገዳቸው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ማዕከላዊ ኮሚቴው እሁድ ምሽት አደረግሁት ባለው ስብሰባ ከፍተኛ አመራሮቹን በሚመለከት እና በቀጣይ ስለሚወስዳቸው እርምጃዎች ውሳኔዎችን አሳልፏል።

በዚህም በ14ኛው የህወሓት ጉባኤ የታገዱ አመራሮች “ከስህተታቸው ተምረው ይቅርታ ጠይቀው ይመለሳሉ በሚል የአንድ ወር ጊዜ ቢሰጣቸውም” ይህንን ለማድረግ ባለመፈቀዳቸው እገዳ እንደተላለፈባቸው መግለጫው አመልክቷል።

መግለጫው አቶ ጌታቸውን ጨምሮ የህወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት 16ቱ ሰዎችን “ከውስጥ ሆነው ድርጅቱን ለማፍረስ ከሚሠሩ አካላት ጋር በመመሳጠር እየሰሩ ችግር ሲፈጥሩ ነበር” ሲል ከሷቸዋል።

ጨምሮም ዕግዱ የተጣለባቸው የህወሓት አመራሮች ድርጅቱ “በሰጣቸው ውክልና የጊዜያዊ አስተዳደር ኃላፊነታቸው ተጠቅመው በሕገወጥ መንገድ ገንዘብ በመበተን ድርጅቱን ለማፍረስ እየሠሩ ነው” በማለት በዚህም የተነሳ አቶ ጌታቸው የሚገኙበት 16 አመራሮች “ህወሓትን ወክልው ማንኛውንም ሥራ እንዳይሠሩ አግጃለሁ” ብሏል።

በዚህም ምክንያት ግለሰቦቹ ትግራይን በሚያስተዳድረው ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ያላቸውን ኃላፊነትን በሚመለከት “ከሚመለከተው ጋር በመነጋገር የማስተካከል ሥራ ይሠራል” ብሏል።

ይህ የዕግድ ውሳኔ ይፋ የሆነው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ እሁድ መስከረም 6/2017 ዓ.ም. በሽረ ከተማ ከነዋሪዎች ጋር ሊያደርጉት የነበረው ስብሰባ ላይ በተፈጠረ ረብሻ መቋረጡን ተከትሎ በተደረገ ስብሰባ መሆኑ ታውቋል።

በደብረ ጽዮን (ዶ/ር) የሚመራው ማዕከላዊ ኮሚቴ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንትን ጨምሮ በ16 የህወሓት አመራሮች ላይ የዕግድ ውሳኔ ያሳለፍበትን ስብሰባ እሁድ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ ነው ሰኞ አመሻሽ ላይ ሳኔውን ያሳወቀው።