ዲዲ ማክሰኞ ዕለት ማንሀታን በሚገኝ ፍርድ ቤት ቀርቦ ሳለ
የምስሉ መግለጫ,ዲዲ ማክሰኞ ዕለት ማንሀታን በሚገኝ ፍርድ ቤት ቀርቦ “ጥፋተኛ አይደለሁም” ብሏል

ከ 4 ሰአት በፊት

ሴቶችን ለወሲብ ንግድ በማዘዋወር የተጠረጠረው ታዋቂው አሜሪካዊ ራፐር በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ በዋስትና እንዲለቀቅ የቀረበው ጥያቄ ውድቅ ሆነ።

በኒው ዮርክ የሚገኘው ፍርድ ቤት የፌዴራል ዳኛ፤ ሙዚቀኛው ከሀገር ሊጠፋ ስለሚችል በቁጥጥር ሥር እንዲቆይ አቃቤ ሕግ ያቀረበውን ጥያቄ ተቀብለው ዋስትና ከልክለዋል።

የ54 ዓመቱ ዲዲ ሰኞ አመሻሹን ነው በቁጥጥር ሥር የዋለው። ራፐሩ ከአውሮፓውያኑ 2008 ጀምሮ የወንጀለኛ ቡድን ይመራ እንዲሁም በዕፅ እና በጉልበት ታግዞ ሴቶች ላይ ጥቃት ሲያደርስ ነበር ይላል አቃቤ ሕግ።

14 ገፆች ያሉት የክስ መዝገብ እንደሚያሳየው ዲዲ በማጭበርበር ወንጀል፣ በግዳጅ የወሲባዊ ዝውውር እና ሰዎች በወሲብ ንግድ ላይ እንዲሰማሩ በማመላለስ ተጠርጥሯል።

የሙዚቃ ፕሮዲዩሰሩ በሶስቱም ክሶች ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ የ15 ዓመታት ፍርድ ሊጣልበት ይችላል።

ማክሰኞ ዕለት ማንሀታን ውስጥ በቆመው ችሎት ዲዲ በጥቁር ቲሸርት እና በግራጫ ቦላሌ ነው የታየው። ዳኛ ሮቢን ታርኖፍስኪ ጥፋተኛ መሆንህን ታምናለህ ወይ ብለው ሲጠይቁት “ጥፋተኛ አይደለሁም” ብሏል።

የፍርድ ቤት መዛግብት እንደሚያሳዩት ሾን ኮምብስ በተባለ የመዝገብ ስሙ የሚታወቀው ዲዲ ሴቶች “ያለፈቃዳቸው በተለያዩ ወሲባዊ ድርጊቶች ላይ እንዲሳተፉ አድርጓል”፤ ይህንም ድርጊት ‘ፍሪክ ኦፍስ’ የሚል ስያሜ ሰጥቶታል።

“በእነዚህ ፍሪክ ኦፍስ በተባሉ ድርጊቶች ላይ ለተጠቂዎች የተመጠነ አደንዛዥ ዕፅ ይሰጥ ነበር፤ ይህን ያደርግ የነበረው ተጠቂዎቹ ታዛዥ እንዲሆኑና ቅሬታ እንዳይቀርቡ ነበር” ይላሉ ክሱ ።

አቃቤ ሕግ ዳሚያን ዊሊያምስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከስድስት ወራት በፊት በግለሰቡ ቤት በተደረገ ፍተሻ 1000 ገደማ ማለስለሻ ቅባቶች መገኘታቸውን ገልፀዋል።

አክለው የፌዴራል ፖሊሶች ባደረጉት ብርበራ ሶስት ከፊል አውቶማቲክ የጦር መሣሪያዎች እና ቀለሀዎች ማግኘታቸውን ይፋ አድርገዋል።

አቃቤ ሕጉ ወደፊት ራፐር ሾን ኮምብስ ሌሎች ክሶች ሊቀርቡበት እንደሚችል ቢናገሩም ዝርዝሩን ከመናገር ተቆጥበዋል።

የዲዲ ጠበቃ የሆኑት ማርክ አግኒፊሎ ዳኛዋ የከለከሉትን ዋስትና ድጋሚ እንዲታይ ለማድረግ ይግባኝ ጠይቀው ረቡዕ ዕለት ቀጠሮ እንደተሰጣቸው አሳውቀዋል።

የፍርድ ቤት መዛግብት እንደሚጠቁሙት ሾን ኮምብስ “የራሱን ወሲባዊ ፍላጎት ለሟሟላት እና ስሟን ላለመቆሸሽሲል ሴቶች እና በዙሪያው ያሉ ሰዎች በዝብዟል፣ አስፈራርቷ እንዲሁም አስፈራርቷል።”

ከሳሽ የሆነው አቃቤ ሕግ እንደሚለው ራፐሩ “የወንጀለኞች ተቋም መሥርቷል”፤ ይህን ተከትሎም የተቋሙ አባላት የሆኑ ግለሰቦች ከሱ በሚሰጣቸው ትዕዛዝ በወሲባዊ ንግድ ዝውውር፣ በጉልበት ሥራ፣ በአፈና እና በዘረፋ ወንጀል ተሰማርተዋል።

ዲዲ እና የቀድሞ ፍቅረኛው ካሳንድራ
የምስሉ መግለጫ,ዲዲ እና የቀድሞ ፍቅረኛው ካሳንድራ

የክስ መዝገቡ እንደሚለው ዲዲ “በተለያዩ ጊዜያት” ሴቶችን “ተማትቷል፣ መሬት ለመሬት ጎትቷቸዋል፣ ዕቃ ወርውሮባቸዋል።”

ክሱ ምን ያክል ሴቶች በራፐሩ ጥቃት እንደደረሰባቸው አላስቀመጠም። አልፎም ሾን ኮምብስ ራሱ በእነዚህ ወሲባዊ ድርጊቶች ላይ ተሳትፏል የሚል አንቀፅ በክስ መዝገቡ ላይ አልሰፈረም።

ባድ ቦይ ሬከርድስ የተባለው ታዋቂ የሙዚቃ ፕሮዳክሽን መሥራች የሆነው ዲዲ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ድርጊቶች ቅሬታ ይቀርብበት ነበር።

ባለፈው ዓመት ኅዳር የቀድሞ ፍቅረኛው ካሳንድራ ኤሊዛቤት ቬንቹራ ክፉኛ አካላዊ ጥቃት እንዳደረሰባት በመጥቀስ ራፐሩን መክሰሷ አይዘነጋም። ራፐሩ ድርጊቱን አልፈፀምኩም ሲል ቢከራከርም በገለልተኛ ሸንጎ ጉዳዩን መፍታቱ ተነግሯል።

ከዚህ ክስ በኋላ የቀድሞ ፍቅረኛውን ሲደበድብ የሚያሳይ ቪድዮ መውጣቱን ተከትሎ ባለፈው ግንቦት የይቅርታ ቪድዮ ለቆ ነበር።

በራፕ የሙዚቃ ዘውግ እጅግ የተሳካላቸው ከሚባሉ ግለሰቦች አንዱ የሆነው ሾን ኮምብስ አሊያም ዲዲ ወሲባዊ እና አካላዊ ጥቃት በማድረስ በተለያዩ ሴቶች ክስ ቀርቦበት ያውቃል።

ራፐሩ የቀረበበትን ክስ ተከትሎ “የኒው ዮርክ ከተማ ቁልፍ” የሰጡት የከተማዋ ከንቲባ ቁልፉን እንዲመልስ ጠይቀውት ለመመለስ ተገዷል። ከቀናት በኋላ ደግሞ ሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ በአውሮፓውያኑ 2014 የሰጠውን የክብር ዶክትሬት ነጥቆታል።