የኤፍቢአይ አርማ

ከ 4 ሰአት በፊት

ከሳምንታት በኋላ የሚደረገውን ምርጫ ለሚያስተባብሩ በ17 የአሜሪካ ግዛቶች ለሚገኙ የምርጫ ኃላፊዎች የተላከ እሽግ ፖስታ ላይ ምርመራ እያደረጉ እንደሚገኙ ኤፍቢአይ እና የአሜሪካ ፖስታ አገልግሎት ገለጹ።

የአሜሪካ ፌዴራል ምርመራ ቢሮ ባልደረቦች እሽጎችን ከተቀባዮቹ መሰብሰባቸውን የገለጹ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ምንነቱ ያልታወቀ ነገር እንደተገኘባቸው አመልክተዋል። ሆኖም ግን በእሽጎቹ ምክንያት የደረሰ ጉዳት የለም ተብሏል።

እሽጎቹ ከኒው ዮርክ እስከ አላስካ ለሚገኙ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እና የምርጫ ኃላፊዎች የተላኩ መሆናቸውም ተዘግቧል።

ይህ ዜና የተሰማው የአሜሪካ ምርጫ እየተቃረበ ባለበት እና በምርጫ አስፈጻሚዎች ላይ የሚሰነዘሩ ዛቻ እና ፖለቲካዊ ጥቃቶች ሊበራከቱ ይችላሉ የሚሉ ማስጠንቀቂያዎች እየጨመሩ በመጡበት ወቅት ነው።

የፌዴራል የምርመራ ቢሮ ኤፍቢአይ እና የአሜሪካ ፖስታ አገልግሎት ምን ያህል ደብዳቤዎች እንደተላኩ እያጣሩ ነው። በተጨማሪም ከእነዚህ መልዕክቶች ጀርባ ያለው ፍላጎት ምን እንደሆነ ምርመራ እያደረጉ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

“አንዳዶቹ ደብዳቤዎች ምንነቱ ያልታወቀ ይዘት አላቸው። ከሕግ አስከባሪ አጋሮቻችን ጋር ሆነን ምላሽ ለመስጠት እና በጥንቃቄ ደብዳቤዎቹን ለማሰባሰብ እየሠራን ነው” ሲሉ በጋራ አሳውቀዋል።

እነዚህ አጠራጣሪ እሽጎች ወደ አላስካ፣ ጆርጂያ፣ ኮኔክቲኬት፣ ኢንዲያና፣ ኬንተኪ፣ ማሳቹሴትስ፣ ኒው ዮርክ እና ቴኔሲ ግዛቶች ለሚገኙ የምርጫ ኃላፊዎች መላካቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።

እንዲሁም በዋዮሚንግ፣ ኮሎራዶ ለሚገኘው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥራያ ቤት ቅርንጫፍ ተልኮ በፈንጂ አምካኞች በኩል መሰብሰቡ ተነግሯል።

ቢያንስ በአራት ግዛቶች የሚገኙ የምርጫ ኃላፊዎች በተላከላቸው እሽግ ላይ የዛቻ መልዕክት እንዳላገኙ ተገልጿል። በኦክላሆማ ግዛት የሚገኘው የምርጫ ቦርድ በደረሰው እሽግ ውስጥ ዱቄት መሰል ነገር እንዳገኘ ገልጿል።

እንዲህ ዓይነት እሽጎች በአሜሪካ ለሚገኙ የምርጫ ኃላፊዎች ሲላኩ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ባለፈው ጥቅምት ወር በጆርጂያ፣ በኔቫዳ፣ በካሊፎርኒያ፣ በኦሬገን እና በዋሽንግተን ግዛቶች ፌንታኒል የተባለው እንክብል እና ሌሎች ይዘቶች ያሉባቸው ፖስታዎች ተልከዋል።