የተጎጂ ቤተሰቦች

ከ 4 ሰአት በፊት

በሊባኖስ የሚገኙ የሄዝቦላህ አባላት መረጃ ለመለዋወጥ የሚጠቀሙባቸው በእጅ የሚያዙ ‘ፔጄሮች’ ፈንድተው አንድ ሕፃንን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች ሲሞቱ ወደ ሦስት ሺህ የሚጠጉ ሰዎች መቁሰላቸውን የአገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር አስታወቀ።

በቤይሩት እና በሌሎች በርካታ ክልሎች በተመሳሳይ ሰዓት በደረሰው ፍንዳታ ከቆሰሉት ከ2 800 በላይ ሰዎች መካከል በሊባኖስ የኢራን አምባሳደር ይገኙበታል።

ፔጀር አነስተኛ ገመድ አልባ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ሲሆን የድምጽ እና የጽሑፍ መልዕክቶችን ለመለዋወጥ ያግዛል። ተንቀሳቃሽ ስልኮች ክትትል ስር ሊገቡ ስለሚችሉ እና የመጠለፍ ስጋት ስላለባቸው አንዳንዶች ፔጀርን ተመራጭ ያደርጋሉ።

በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ ፔጀሮቹ “የተለያዩ የሄዝቦላህ ክፍሎች እና ተቋማት ሠራተኞች ንብረት ናቸው” ከማለት ባለፈ ስምንት ተዋጊዎች መሞታቸውን አረጋግጧል።

ቡድኑ “ለዚህ የወንጀል ጥቃት” እስራኤልን ተጠያቂ አድርጎ “ፍትሃዊ ቅጣት” ያለው ምላሽ እንደሚጠብቃት ገልጿል። የእስራኤል ጦር በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።

ከፍንዳታዎቹ ከሰዓታት በፊት የእስራኤል ካቢኔ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በሠላም እንዲመለሱ ለማድረግ በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ላይ የሄዝቦላ ጥቃቶችን ማስቆም ይፋዊ የጦርነት ግቡ መሆኑን አስታውቋል።

በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በጋዛ ጦርነት ከጀመረ ወዲህ በእስራኤል-ሊባኖስ ድንበር ላይ በየቀኑ ማለት በሚቻል ደረጃ የተኩስ ልውውጦች እየተካሄዱ ነው።

ሂዝቦላህ በኢራን ከሚደገፈው የፍልስጤም ቡድን ጎን በመቆም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቋል። ሁለቱም ድርጅቶች በእስራኤል፣ በዩናይትድ ኪንግደም እና በሌሎች አገራት በአሸባሪነት የተፈረጁ ናቸው።

የተባበሩት መንግሥታት ቃል አቀባይ በሊባኖስ የተፈጠሩት ክስተቶች “በጣም አሳሳቢ ናቸው” ብለዋል።

በርካታ ሊባኖሳውያን በማክሰኞ ምሽቱ ክስተት በድንጋጤ እና ባለማመን ሁኔታ ውስጥ ገብተዋል።

ሄዝቦላህ እንደገለጸው ከሆነ ቡድኑ ለግንኙነት አገልግሎት የሚጠቀምባቸው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ፔጀሮች በዋና ከተማዋ ቤይሩት እና በሌሎች በርካታ አካባቢዎች በተመሳሳይ ሰዓት ፈንድተዋል።

አንድ የደኅንነት ቪዲዮ በአንድ ሱፐርማርኬት ውስጥ በነበረ ግለሰብ ቦርሳ ወይም ኪስ ፍንዳታ እንደነበር አሳይቷል። ግለሰቡ መሬት ላይ ወድቆ በስቃይ ሲያቃስት እና ሌሎች ሰዎች ሲሸሹ ይታያል።

ከሰዓታት በኋላ ጭምር አምቡላንሶች በተጎጂዎች ቁጥር ወደ ተጨናነቁ ሆስፒታሎች ሲመላለሱ የነበረ ሲሆን፣ ከተጎጂዎች ውስጥ 200 ያህሉ በከባድ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ከሆስፒታል ውጪ የተሰባሰቡ የተጎጂ ዘመዶች መረጃዎችን ለማግኘት በተስፋ እየጠበቁ ነው።

በቤይሩት አሽራፊህ አካካቢ የሚገኘው የኤልኤዩ የህክምና ማዕከል ዋና በሩን ዘግቶ የሚገቡትን ሰዎችን ቁጥር ገድቧል። “በጣም ከባድ ነው። አንዳንዶቹ ጉዳቶች አሰቃቂ ናቸው” ሲል አንድ ሠራተኛ ለቢቢሲ ተናግሯል።

በቤሩት ጥበቃው ተጠናክሯል

አብዛኞቹ ጉዳቶች ወገብ፣ ፊት፣ ዓይን እና እጅ ላይ የደረሱ መሆናቸውን ጠቅሶ “ብዙ ተጎጂዎች የተወሰኑ ሌሎች ደግሞ ሁሉም የእጅ ጣቶቻቸውን በፍንዳታው አጥተዋል” ብሏል።

የኢራኑ አምባሳደር ሞጅታባ አማኒ ሚስት በአንደኛው ፍንዳታ “ትንሽ ተጎድተው” በሆስፒታል ውስጥ “በደህና ሁኔታ ላይ ይገኛሉ” ብለዋል።

የሄዝቦላህ ሚዲያ ቢሮ በበኩሉ የስምንት ተዋጊዎቹ ሕይወት ማለፉን አስታውቋል። ሟቾቹ “ወደ እየሩሳሌም በሚወስደው መንገድ ላይ በሰማዕትነት እንደተገደሉ” ብቻ በመግለጽ ስለቦታው እና ስለሁኔታው ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።

ለቡድኑ ቅርብ የሆነ ምንጭ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደገለጸው የሄዝቦላህ የፓርላማ አባል አሊ አማር ልጅ እና የ10 ዓመት የሚሆናት የሄዝቦላህ አባል ሴት ልጅ ከተገደሉት መካከል ይገኙበታል።

ሄዝቦላህ ከመንግሥት ኃይሎች ጎን እየተዋጋ በሚገኝባት ሶሪያ ውስጥ 14 ሰዎች በፍንዳታ እንደቆሰሉ የሶሪያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስታውቋል።

ሂዝቦላ ማክሰኞ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ “ለዚህ የወንጀል ጥቃት እስራኤልን ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ እናደርጋለን” ብሏል።

“ይህ ተንኮለኛ እና ወንጀለኛ ጠላት ለዚህ ጥቃት ተመጣጣኝ ቅጣት ያገኛል” ሲል አክሏል።

የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ሚካቲ ለፍንዳታዎቹ እስራኤልን ተጠያቂ አድርገዋል። “የሊባኖስን ሉዓላዊነት የሚጥስ እና በሁሉም መመዘኛዎች ወንጀል” መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በበኩላቸው “የእስራኤልን አሸባሪነት አጥብቀው እንደሚያወግዙ” ለሊባኖሱ አቻቸው መግለጻቸውን ተናግረዋል።

የእስራኤል የቅርብ አጋር የሆነችው አሜሪካ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንደሌላት በመግለጽ ኢራን ውጥረቱን እንዳታባብስ አሳስባለች።