ድሮን ሲበር የሚያሳይ ምስል

ከ 5 ሰአት በፊት

አቶ ንጉሥ በለጠ* በድሮን ጥቃት በአንድ ጀምበር ሕይወታቸው ከተመሳቀለባቸው ግለሰቦች መካከል አንዱ ናቸው።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ባለቤታቸውን ጨምሮ ስምንት ቤተሰቦቻቸው እንደተገደሉባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የካቲት 11/2016 ዓ.ም. ሞጃ እና ወደራ ወረዳ ‘አይሱዙ’ በተባለ ተሽከርካሪ ላይ በተፈጸመው የድሮን ጥቃት ከሳሲት ወደ ጋውና ሲጓዙ የነበሩ ከ20 በላይ የአንድ ቤተሰብ አባላት እና ቤተ ዘመድ ሕይወት አልፏል።

“ድሮን ጣለ” ሲባል ሰምተው ስፍራው ላይ በአፋጣኝ የደረሱት አቶ ንጉሥ “[ስደርስ] ባለቤቴን ወድቃ አገኘኋት። ከዚያ በኋላ ራሴን አላውቅም፤ [ራሴን] ስቻለሁ። እንዴት ልሁን፣ ምን ልሁን በወቅቱ አላስታውስም። ወደ ጻድቃኔ ጸበል ገብቼ ነው ከ40 ቀን በኋላ ትንሽ መረጋጋት የጀመርኩት” ይላሉ።

በዚህ የድሮን ጥቃት ባለ ክርስትናው ህጻን በአያቱ እቅፍ ሆኖ የተረፈ ሲሆን፤ አብረው ተቀምጠው የነበሩ እናቱን ጨምሮ በርካታ የቤተሰብ አባላት ግን ተገድለዋል።

በወቅቱ ቢቢሲ ያናገራቸው እና በደቂቃዎች ውስጥ ስፍራው ላይ የደረሱ አንድ የዓይን እማኝ ጥቃቱን “እልቂት” ሲሉ ገልጸውታል።

በጥቃቱ 18 ቁስለኞች ወደ ጤና ጣቢያ ለሕክምና እንደገቡ የሕክምና ምንጭ አረጋግጠው፤ የተሽከርካሪውን ሹፌር ጨምሮ ሦስቱ ቁስለኞች ወዲያኑ ሕይወታቸው እንዳለፈ ተናግረዋል።

መስመር

ጥቅምት 23 2015 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ 460 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው ቢላ ከተማ ቦጂ በርመጂ ከ60 በላይ ሰዎች በድሮን ጥቃት ምክንያት መሞታቸውን የቢቢሲ ምንጮች ይናገራሉ።

በአካባቢው የሚገኝ የሕክምና ተቋም ሠራተኞች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሞቅ ባለ የገበያ ቀን ገበያተኞች በተሰበሰቡት በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ነው ከ60 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

የመካነ ኢየሱስ ቄስ የሆኑት እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ ግለሰብ የእህታቸውን ልጅ ጨምሮ በጥቃቱ የሞቱ 11 ሰው መቅበራቸውን ይናገራሉ።

ሌላ የዓይን እማኝ ደግሞ ከተገደሉት መካከል ልጃቸው እንደሚገኝበት እና ወደ ትምህርት ቤት እየሄደ ሳለ በድሮን ጥቃት መመታቱን እና መሞቱን ተናግረዋል።

“የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ነበር ልጄ። ቦጂ በርመጂ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር የሚማረው። ወደ ትምህርት ቤት እየሄደ ሳለ ነው የተገደለው” ብለዋል።

“ቢያንስ 60 ሰዎች ያህል ተገድለዋል፤ እኔም የእህቴን ልጅ ቀብሬያለሁ። ከአንድ ቤት ሁለት ሦስት ሰው የሞተበት አለ” ይላሉ የመካነ ኢየሱስ ቄስ የሆኑት ግለሰብ።

በዕለቱ በከተማዋ ምንም ዓይነት ውጊያ እንዳልነበር እና የድሮን ጥቃቱ ከመድረሱ በፊት የመንግሥት ወታደሮች አካባቢውን ለቅቀው መውጣታቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች በወቅቱ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

የድሮን ጥቃቶች በኢትዮጵያ ግጭቶች ውስጥ

የሰው አልባ አውሮፕላኖች (የድሮን) ጥቃት በኢትዮጵያ ምናልባትም ከ2013 ዓ.ም. በፊት ተሰምቶ አይታወቅም።

ነገር ግን በተለይም ለሁለት ዓመታት በተደረገው እና ደም አፋሳሽ በሚባለው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወቅት በሰፊው ጥቅም ላይ ውሏል።

ባለፉት አራት ዓመታትም በአራት የኢትዮጵያ ክልሎች በርካታ የድሮን ጥቃቶች በመንግሥት ሠራዊት ተፈጽመው፤ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰላማዊ ሰዎች እንደተገደሉ መረጃዎች ያሳያሉ።

በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ጥቃቶቹ አሁንም የቀጠሉ ሲሆን ትምህርት ቤቶች፣ አብያተ ክርስቲያናትን፣ የገበያ ስፍራዎች እና የትራንስፖርት መናኸሪያዎችን ጨምሮ የሕዝብ መገልገያ የሚባሉ ስፍራዎች የጥቃት ዒላማ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ግን ‘ድሮን ታጣቂ ላይ እንጂ ሕዝብ ላይ አይጣልም’ በማለት የሚቀርበውን ክስ ያስተባብላሉ።

ይኹን እንጂ ቢቢሲ ከዓይን እማኞች እና ከተለያዩ ምንጮች ባሰባሰው መረጃ በተለይም በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች መንግሥት “ምርጥ ዒላማ” በሚለው የድሮን ጥቃት ከታጣቂዎች ይልቅ ንጹሃን የእሳት እራት እንደሚሆኑ ተረድቷል።

ከ2013 ዓ.ም. እስከ ጥር 2016 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት በኢትዮጵያ 144 የሚሆኑ (የተመዘገቡ እና የተረጋገጡ) የድሮን ጥቃቶች ተፈጽመዋል።

ከ2013 ዓ.ም. እስከ ጥር 2016 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት በኢትዮጵያ 144 የሚሆኑ (የተመዘገቡ እና የተረጋገጡ) የድሮን ጥቃቶች ተፈጽመዋል።

ሞት ከሰማይ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በ2016 ዓ.ም. ዓመታዊ ሪፖርቱ ንጹሃንን ያልለዩ፣ አስፈላጊነትን እና የተመጣጣኝነት መርሆዎችን ያልጠበቁ የድሮን ጥቃቶች መፈጸማቸውን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ በጥቃቶቹ ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሲቪል ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን ጥቃት የተፈጸመባቸውን አካባቢዎች ጠቅሶ “በሕይወት የመኖር መብት ተጥሷል” ብሏል።

በድሮን ጥቃት ንጹሃን ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው የሚለው የመብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ “በግጭቱ ውስጥ ምንም ተሳትፎ የሌላቸው ሲቪሎችን ዒላማ ያደረጉ ግድያዎች እንዳሉ ሪፖርቶች አሉ” ይላል።

ከግድያዎች ባሻገርም በጥቃቶቹ የጦርነት እንቅስቃሴ ያልነበረባቸው “የንጹሃን መገልገያ የሆኑ መሠረተ ልማቶች ላይም ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው” ሲልም ያክላል።

ለአማራ እና ኦሮሞ ሕዝቦች እንቆረቆራለን የሚሉ ድርጅቶች በክልሎቹ ላይ የሚደርሱ የድሮን ጥቃቶችን “እጅግ አሳሳቢ” እንደሆኑ በተለያዩ ጊዜያት ገልጸዋል።

የአማራ ማኅበር በአሜሪካ የአድቮኬሲ ኃላፊ አቶ ሆነ ማንደፍሮ “በአማራ ክልል የሚፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች ዋና ሰለባ የሆኑት ንጹሃን ዜጎች ናቸው። አገዛዙ በጅምላ ሰዎች ሰብሰብ ብለው ሲያይ ታጣቂዎች (ፋኖ) ሊሆኑ ይችላሉ በሚል ሲያጠቃ [ነበር]” ይላሉ።

ማኅበሩ እንደሚለው ከነሐሴ 2015 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 2016 ዓ.ም. በአማራ ክልል ቢያንስ 80 “የተረጋገጡ” የድሮን ጥቃቶች ተፈጽመዋል። ከእነዚህ ጥቃቶች ከግማሽ በላይ ሚሆኑት (42 ጥቃቶች) የንጹሃን ግድያውን አስከትለዋል።

አቶ ሆነ በጥቃቶቹ 400 የሚደርሱ ንጹሃን ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጠናል ያሉ ሲሆን፤ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ማንነት እንደለዩም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ሁሉም በሚባል ደረጃ ድሮኖች ጉዳት ያደረሱት ንጹሃን ዜጎች ላይ ነው። በተለይ በመጀመሪያዎቹ የጦርነቱ ስድስት ወራት በአንድ ቦታ ላይ ሦስት እና አራት የድሮን ጥቃቶች አከታትሎ በመጣል በርካታ ንጹሃን የተጨፈጨፉበትን ሁኔታ አይተናል” ይላሉ።

መቀመጫውን ውጭ ያደረገ ሰብዓዊ መብት መከበር ላይ የሚሠራው ኦሮሞ ሌጋሲ ኤንድ አድቮኬሲ አሶሲየሽን፣ በኦሮሚያ ክልል ከትግራይ ጦርነት መቀስቀስ ጀምሮ የድሮን ጥቃቶች ተፈጽመዋል ይላል።

ማኅበሩ የድሮን ጥቃቶች በግለሰብ ቤቶች፣ በሃይማኖት ጉባኤዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በሰርግ ሥነ ሥርዓቶች እና በሌሎች ሕዝብ በሚሰበስብባቸው ቦታዎች ላይ ተፈጽመዋል ብሏል።

በዋናነት ደግሞ ወለጋ እና ጉጂ ዞኖች የሚገኙበት ምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ ላይ ጥቃቶቹ እንደተፈጸሙ የሚጠቅሰው ድርጅቱ፤ ከጊዜ ወዲህ ግን የጥቃቶች መጠን እየጨመረ እና ወደ መካከለኛው ኦሮሚያ ተስፋፍቷል ይላል።

ባለፉት ዓመታት በክልሉ በተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች የተገደሉ ሰዎችን ቁጥር ይህን ያህል ነው ማለት እንደማይችል የሚናገረው ማኅበሩ፤ “በሺህዎች ሊሆን ይችላል” ሲል ግምቱን ያስቀምጣል።

“. . . የጥቃቶቹ ድግግሞሽ፣ የሚፈጸምበት ወቅት እና በእያንዳንዱ ጥቃት የሚገደሉ ሰዎችን መሠረት አድርገን ቁጥሩ በሺህዎች ሊሆን እንደሚችል እንገምታለን” ብሏል።

“በንጹሃን ላይ የሚደርሰው ጉዳት እጅግ የሚያሳስብ ነው። የመንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት ሕዝቡን ከጉዳት መጠበቅ ነው። ነገር ግን መንግሥት ዜጎችን የመጠበቅ ኃላፊነቱን ካለመወጣቱ ባሻገር፣ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰው በደል ዋነኛ ፈጻሚ ሆኗል” ሲል ክስ ያቀርባል።

በኦሮሚያ ክልል የድሮን ጥቃትን ለመከላከል ታጣቂዎች ሕዝቡን እንደ ከለላ እንደሚጠቀሙ ይነገራል። በተለይም ታጣቂዎች አዲስ አባሎቻቸውን ሲያስመርቁ ለከለላነት (ጋሻ) ነዋሪዎችን አስገድደው እንደሚያስወጡ ይነገራል።

ይህንን ሁኔታ በተመለከተ ማኅበሩ እንደሚያውቅ ገልጾ፤ ነገር ግን እንዲህ ያለው ክስተት መጠኑ ምን ያህል እንደሆነ ማረጋገጥ እንደማይችል ጠቁሟል።

https://flo.uri.sh/visualisation/19288793/embed?auto=1

የድሮን አዝማሚያ

ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች የሆነው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፉት አራት ዓመታት የድሮን ጥቃት በኢትዮጵያ በሰፊው ጥቅም ላይ መዋሉን ይገልጻል።

ሌሎች ገለልተኛ ተቋማትም የድሮን ጥቃት የተፈጸሙባቸውን አካባቢ በመተንተን ጥቃቱ ያደረሰውን ጉዳት ይናገራሉ።

የፖለቲካ ግጭቶችን እና ተቃውሞዎችን የሚሰንደው አርምድ ኮንፍሊክት ሎኬሽን ኤንድ ኤቨንት ዳታ (አክሌድ) የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት የኢትዮጵያን ሰላም በሚከታተልበት መርሃ ግብሩ ከታኅሳስ 2013 ዓ.ም. እስከ የካቲት 2016 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት 139 የተረጋገጡ የድሮን ጥቃቶች ተፈጽመዋል ይላል።

በተጠቀሰው ጊዜ የተፈጸሙት የድሮን ጥቃቶች አራት ክልሎችን የሚሸፍን ሲሆን፣ ጥቃቶቹም ሰሜን እና በማዕከላዊ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ያነጣጠሩ ናቸው።

ከዚህም ውስጥ የትግራይ ክልል ለሁለት ዓመታት በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ከፍተኛ ድርሻ ያለውን (41 በመቶ) የድሮን ጥቃቶችን አስተናግዷል።

ከዚህ ጦርነት ጋር በተያያዘም የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎችን ዒላማ ያደረጉ የድሮን ጥቃቶች በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውስጥም ተፈጽመዋል።

የትግራይ ጦርነት በሰላም ስምምነት ማብቃቱን ተከትሎ፤ መንግሥት “መደበኛ ጦርነት አይደለም” በሚለው እና የትጥቅ ግጭቶች በቀጠለባቸው በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የድሮን ጥቃቶችን እየፈጸመ ነው።

አክሌድ በመዘገበው መረጃ በአማራ ክልል እስከ ጥር 2016 ዓ.ም. ድረስ 49 የድሮን ጥቃቶች ተፈጽመዋል። እነዚህ ጥቃቶች በትግራዩ ጦርነት ወቅት የህወሓት ተዋጊዎችን ዒላማ ያደረጉትን የሚጨምር ሲሆን፤ ከጥር 2016 ዓ.ም. በኋላ የተፈጸሙትን ግን አያካትትም።

በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ጥቃቶችን የሚከታተለው የአማራ ማኅበር በአሜሪካ፣ በክልሉ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የትጥቅ ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በአንድ ዓመት ውስጥ 80 ገደማ የድሮን ጥቃቶች እንደተፈጸሙ አመልክቷል።

እስከ ጥር 2016 ዓ.ም. በገለልተኛ አካል በተረጋገጡ የድሮን ጥቃቶች አማራ ክልል ከአገሪቱ ሁለተኛ ከፍተኛ የድሮን ጥቃት የተፈጸመበት ክልል ነው። የክልሉ ምሥራቅ እና ደቡብ ክፍሎች ደግሞ ተደጋጋሚ ጥቃት የተፈጸመባቸው ስፍራዎች ናቸው ነው።https://flo.uri.sh/visualisation/19288729/embed?auto=1

በኦሮሚያ ክልል ደግሞ 28 የድሮን ጥቃቶች እንደተፈጸሙበት የአክሌድ መረጃ ይጠቁማል። ጥቃቶቹ በአብዛኛው ሰሜን እና ምሥራቅ የክልሉ አካባቢዎች ላይ የተፈጸሙ ናቸው።

በአሜሪካ ኦስቲን ኮሌጅ መልክዓ ምድራዊ መረጃዎችን መሠረት አድርጎ የተለያዩ ትንተናዎች የሚሰጥበት የመልክዓ ምድር መረጃ ሥርዓት (GIS) መምህር እና ተንታኝ የሆኑት ዶ/ር ዳንኤል ካሳሁን እንደሚሉት በኢትዮጵያ የሚፈጸመው የድሮን ጥቃት ዓይነት “ተንቀሳቃሽ ዒላማን” (Dynamic Target) ለመምታት የሚፈጸም ነው ይላሉ።

የድሮን ጥቃቶችን መረጃ የሚተነትኑት ባለሞያው ጥቃቶቹ ምድር ላይ ባለ በቂ መረጃ ላይ የተመሠረቱ አይደለም ይላሉ። ይልቁንም ጥቃቶቹ “ለአደን እንደሚወጣ አውሬ” ዓይነት መልክ አላቸው ሲሉም ይገልጻሉ።

“ሰላማዊ ሰዎች በከፍተኛ መጠን በተሽከርካሪ ወይም በጭነት መኪና ተጭነው ሊጓዙ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ሰዎቹ ታጣቂዎች ይሆናሉ በሚል ሊተረጎም ይችላል። በዚህ ምክንያት ጥቃት ሊፈጸምባቸው ይችላል” ሲሉ ማሳያ ያቀርባሉ።

በኢትዮጵያ ድሮኖቹ የሰው ዓይን የሚያየው የዕይታ መጠንን (Visual Signal Range) እንደሚጠቀሙ የሚተነትኑት ባለሙያው፤ ከምሥል ላይ በተነሳ መረጃ ላይ ተንተርሶ ጥቃቱ እንደሚፈጸም ያብራራሉ። ይህም ለስህተት የተጋለጠ ነው ይላሉ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትም በድሮን ለሚፈጸሙ ጥቃቶች “ስብስብ ዒላማን” እንደሚጠቀም ተናግሯል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ባለፈው ዓመት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት “ድሮን የምንጠቀመው ለስብስብ ዒላማ ነው። ስብስብ ዒላማ ማለት የጠላት ቋጠሮ ነው። የጽንፈኛውን ስብስብ ስናገኝ እንመታለን” ሲሉ ተናግረው ነበር።

ይሁን እንጂ ተሟጋቾች የድሮን ጥቃቶቹ ከታጣቂዎች ይልቅ ንጹሃንን ዒላማ አድርገዋል አሊያም የጥቃቶቹ ገፈት ቀማሾች ንጹሃን ሰዎች ሆነዋል ይላሉ።

ዶ/ር ዳንኤል “[ድሮን] እያረፈ ያለው ከሕብረተሰብ ጋር የተቀላቀለ አማጺ ላይ ወይም አማጺ ነው ተብሎ በተጠረጠረ [ሕዝብ] ላይ ነው” ሲሉ ክፍተት እንዳለ ያነሳሉ።

በመላምት ደረጃ በውስጣዊ ግጭት ድሮኖች ጥቅም ላይ የሚውለው ወታደሮች መድረስ ባልቻሉባቸው አካባቢዎች ላይ፣ የመልክዓ ምድር አቀማመጡ በማይመች እና ከፍተኛ ዋጋ ያለው ዒላማ ከአነስተኛ የንጹሃን ሰዎች ጉዳት ጋር ሲገኝ ነው ተብሎ ይታመናል።

ታዲያ መንግሥት ለምን በድሮን ጥቃት ይፈጽማል? አካባቢዎቹ ጋር መድረስ ስላልቻለ? የሕዝብ ሥርጭቱ (ክምችቱ) አነስተኛ ስለሆነ?

በአገሪቱ የደረሱ የድሮን ጥቃቶች ስብጥር ከመንገዶች እና ከሕዝብ ሥርጭት ጋር ሲነጻጸሩ ግን መንግሥትን እነዚህን ዘመናዊ የጥቃት መሳሪያዎች እንዲጠቀም ገፋፍተዋል ተብለው ሊታሰቡ የሚችሉ መላምቶችን የሚያፈርሱ ናቸው።

ዶ/ር ዳንኤል “ከፍተኛ የድሮን ጥቃት የተፈጸመው ከመንገዶች በ10 ኪሎ ሜትሮች ግራ እና ቀኝ በሚገኙ እና በቀላሉ ሊረስባቸው በሚችሉ ስፍራዎች ላይ ነው። ከዋና መንገዶች በራቅን ቁጥር የድሮን ጥቃቶች እያነሰ እያነሰ ነው የሚሄደው” ይላሉ።

በጥቃቶቹ ሊጎዱ የሚችሉ ንጹሃንን ታሳቢ በማድረግ የሕዝብ ክምችት ያለባቸውን አካባቢዎች አይጠቁም የሚልን መነሻ ሀሳብ ይዘው የድሮን ጥቃቶችን ከሕዝብ ሥርጭት ጋር የተመለከቱት ዶ/ር ዳንኤል፤ “ምናልባትም 95 በመቶ የሚሆነው የድሮን ጥቃት የተከናወነው ከፍተኛ የሕዝብ ክምችት ባለባቸው አካባቢዎች ነው” ይላሉ።

በኢትዮጵያ ድሮን ጥቃቶች በቀን እና በጋ በሚባሉ ወራት ወይም ዝናብ በሌለበት ወቅት የሚፈጸሙ ናቸው።

ከመስከረም እስከ ጥር ያሉ ወራት አብዛኞቹ የድሮን ጥቃቶች የተፈጸሙባቸው ሲሆኑ፤ ጥቅምት ወር ደግሞ ከፍተኛ ጥቃቶች የተፈጸሙበት ወር ነው።

ከየካቲት እስከ ነሐሴ ወራት የዝናብ ወቅት በመሆኑ በደመና ሽፋን ምክንያት የድሮኖች ዕይታ የሚቀንስ በመሆኑ፤ በእነዚህ ወራት የድሮን ጥቃቶች አልተፈጸሙም።

በድሮን ጥቃት የደረሱ አደጋዎች

ድሮኖች ለምን ፍቱን ሆነው ተገኙ?

ሰው አልባ አውሮፕላኖች የተለያየ ቅርጽ እና መጠን አላቸው። የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ድሮኖችን በሦስት መደብ ይከፍላል።

መደብ አንድ ድሮኖች አነስተኛ ሲሆኑ በእጅ የሚነሱ፣ እስከ 80 ኪ.ሜ ድረስ መብረር የሚችሉ እና የሦስት ሰዓት የአየር ላይ ቆይታ ብቻ ያላቸው ናቸው። አንዳንዶቹ እነዚህ ድሮኖች ከሰው እጅ ያነሰ መጠን አላቸው።

የአጭር ርቀት የሚባሉት መደብ ሁለት ድሮኖች ደግሞ ለመብረር አነስተኛ መንደርደሪያ የሚፈልጉ፣ እስከ 10 ሰዓት መብረር የሚችሉ እና ከ100 እስከ 200 ኪ.ሜ የሚሸፍኑ ናቸው። እነዚህ ድሮኖች ለዒላማ የሚሆኑ የቅኝት መሳሪያዎች ይገጠሙላቸዋል።

መደብ ሦስት ድሮኖች ‘መካከለኛ ከፍተኛ ረዥም’ ወይም ‘ከፍተኛ ረዥም’ በመባል የሚጠሩ ሲሆን፤ ለ24 ሰዓታት የመብረር አቅም አላቸው። ለመብረር መንደርደሪያ የሚያስፈልጋቸው እና በሰዓት 300 ኪ.ሜ እና ከዚያ በላይ በመብረር ከፍተኛ ፍጥነት ያላቸው ናቸው።

እነዚህን ድሮኖች የሚንቀሳቅሱ ባለሙያዎች በሺህዎች ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሆነው በሳተላይት ግንኙነት እገዛ ድሮኖቹን ማብረር ይችላሉ። አብዛኞቹ እነዚህ ድሮኖች መሳሪያዎችን መሸከም የሚችሉ እና ለውጊያ ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የድሮኖች ጥቅም የመዋል ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን መቀመጫውን ኔዘርላንድ ያደረገው የሰላም ግንባታ ድርጅት የሆነው ፓክስ ይገልጻል።

ከአውሮፓውያኑ 2007 ወዲህ ደግሞ የአፍሪካ ሰማዮች በጦር ድሮኖች እየተያዙ ነው የሚለው ድርጅቱ፤ ለዚህም ሰሜን አፍሪካ፣ የሳህል አካባቢ እና የአፍሪካ ቀንድ አገራት ተጠቃሽ ናቸው።

ፓክስ በአፍሪካ የጦር ድሮኖች ዙሪያ ባወጣው ሪፖርቱ ድሮኖች ውጤታማ እና በአንጻራዊነት ርካሽ ተደርገው ይታያሉ ይላል።

ድሮን በሰፋፊ ቦታዎች ተዘዋውረው የደኅንነት መረጃዎችን ለመሰብሰብ እና ለክትትል ይሰማራሉ። ዓይን ውስጥ ሳይገቡ ተሽከርካሪዎችን እና ሰዎችን የሚከታተሉት ድሮኖች ማን ወይም ምን ላይ ጥቃት እንደሚፈጸም የሚወሰንበት መረጃ ይሰበስባሉ። ሲወሰንም የተሰጣቸው ዒላማ ላይ ጥቃት ሊሰነዝሩ ይችላሉ።

በአሜሪካ ኦስቲን ኮሌጅ የመልክዓ ምድር መረጃ ሥርዓት (GIS) መምህር እና ተንታኝ የሆኑት ዶ/ር ዳንኤል ካሳሁን ከ100 በላይ ድሮኖችን የሚጠቀሙ አገራት እነዚህን በራሪዎች ለሦስት ዓይነት ግጭቶች (ዘርፎች) እየተጠቀሙበት ነው ይላሉ።

ከመስከረም 11ዱ ጥቃት በኋላ አሜሪካ ለጀመረችው የፀረ-ሽብር ዘመቻ፣ በአገራት መካከል ባለ ጦርነት ለአብነትም የአዘርባጃን እና የአርሜኒያ እንዲሁም የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በተጨማሪም ኢትዮጵያ የምትመደብበት የአገር ውስጥ ተቀናቃኞችን እና አማጺያንን ለመደምሰስ ጥቅም ላይ እንደሚውል ያብራራሉ።

ይሁን እንጂ ድሮኖች በሚያደርሱት የንጹሃን ጉዳት አጠቃቀማቸው ፈር መያዝ አለበት የሚሉ ድምጾች እየተበራከቱ ቢሆንም፣ በትጥቅ ግጭት የበላይ ለመሆን ሲባል ግን ጥቅማቸው እያደገ ነው።

የ21ኛው ክፍለ ዘመንን የጦርነት ገጽታን እንደቀየሩት የሚነገርላቸው ድሮኖች፤ በኢትዮጵያ በትግራዩ ጦርነት በስፋት ጥቅም ላይ ውለው በጦነቱ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ነበራቸው።

ዶ/ር ዳንኤል በጦርነቱ ድሮኖች በነበራቸው ሚና ምክንያት መንግሥት ለተመሳሳይ ውጤት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎችም እተጠቀመባቸው ነው ብለው ያምናሉ።

“መንግሥት [በትግራዩ ጦርነት] አለቀለት ሲባል መልሶ ማንሰራራት የቻለው ድሮኖችን በስፋት በመጠቀሙ ስለሆነ፤ ተቃዋሚን፣ አማጽያንን [በድሮን] ማጥፋትም ማዳከምም ይቻላል እንዲል ሳያደርገው አልቀረም” ይላሉ።

“ልጆቻችሁን ያዙ”

የአገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ “ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችን” በሚመለከት ባለፈው ታኅሣሥ ባደረጉት “ቃለ ምልልስ” በድሮን ጥቃቶች ንጹሃን ስለመገደላቸው አስተባብለዋል።

“እኛ የገጠመንን ነው የምንገጥመው” ሲሉ ለሕዝቡ እንደሚጠነቀቁ እና ያልታጠቁ ንጹሃን ላይ ጥቃት እንደማይፈጽሙ ተናግረዋል።

“አንዳንድ ዒላማዎች ሕዝብ ውስጥ በመሆናቸው የተውናቸው አሉ” ሲሉ ሠራዊታቸው “ሕዝባዊ እና ሕግ አክባሪ” እንደሆነ ያሰመሩት ኢታማዦር ሹሙ፤ “የዘፈቀደ ሽፍታ አይደለንም” ብለዋል።

ይሁን እንጂ በድሮን ጥቃቶቹ በርካታ ንጹሃን እንደተገደሉ የተጎጂ ቤተሰቦች፣ የዓይን እማኞች፣ መንግሥታዊውን ኢሰመኮን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች አረጋግጠዋል።

ኢታማዦር ሹሙ እንደ አቶ ንጉሥ ቤተሰቦች ለብዙዎች እልቂት ምክንያት የሆነውን ድሮንን ከክላሽ ለይተው እንደማያዩት ተናግረዋል።

የአገሪቱ ከፍተኛው የጦር መኮንን ሠራዊታቸው እየተዋጋቸው ያለውን ታጣቂዎችን መሠረት አድርገው “. . . ገጥመዋል እኮ፤ እኔ መሳሪያ ልመርጥለት ነው? ‘ድሮን ተውና ክላሽ ለክላሽ እንግጠም’ ነው እያለ ያለው?” ሲሉም “የተመጣጣኝነትን” ጉዳይ አጣጥለዋል።

ምንም እንኳ በአገሪቱ ባለፉት ጊዜያት የድሮን ጥቃቶች ከዓመት ዓመት መጨመራቸው እየተነገረ ቢሆንም፤ መንግሥት ግን “የአቅሜን ያህል አልተጠቀምኩም” ይላል።

“ይህን ያህል ተጠቅመናል ብዬ ልወስድ አልችልም። [ድሮን] ባለን አቅም ልክ አልተጠቀምንም። የማይገኝ ምርጥ ዒላማ ስናገኝ ግን እንተኩሳለን” ብለዋል – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ።

“ከጽንፈኛ ጋር አትደባለቁ። ልጆቻችሁ የሚፎክር፤ የሚሸልል ጽንፈኛ አይተው እይሄዱ። ልጆቻችሁን ያዙ። 70፤ 80 ጽንፈኛ ተሰብስቦ ከተገኘ ሊያጠቃ፣ ወይም ሊማከር [ነው] ወይም ሲመገብ ካገኘነው እንመታለን። ይሄ ይቀጥላል” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

‘ጆሮ ዳባ ልበስ’

በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በጥቃቶቹ ስለሚደርሰው የንጹሃን ጉዳት እምብዛም ሪፖርት አልተደረገም የሚል ቅሬታ ይቀርባል።

የመንግሥታቱ ድርጅትን ጨምሮ አገራት እና ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾች በተለይም በሰሜኑ ኢትዮጵያ ላይ የነበራቸውን ክትትል ለሁለቱ ክልሎች ነፍገዋል በሚል ይነቀፋሉ።

ይህም የጉዳቱ መጠን እንዲቀበር ከማድረጉ ባለፈ መንግሥት ተጠያቂ እንዳይሆን አድርጓል ይላሉ።

ኦሮሞ ሌጋሲ ሊደርሽፕ ኤንድ አድቮኬሲ አሶሲየሽን ለትግራይ ጦርነት የተሰጠውን ያህል ትኩረት ለኦሮሚያ አልተሰጠም በማለት “የክልሉ ግማሽ ክፍል ላለፉት አምስት ዓመታት ተቆልፎበታል” ይላል።

የአማራ ማኅበር በአሜሪካ ኃላፊ አቶ ሆነ ማንደፍሮ በበኩላቸው ጥቃቶቹ “ተገቢውን ትኩረት አላገኙም” ይላሉ፤ ለዚህም የመገናኛ ብዙኃን ሽፋንን ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ምርመራን በመጥቀስ “ጥቃቶቹ በዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፍላጎት መነፈግ ምክንያት ትኩረት አላገኙም” ይላሉ።

ይህን ሀሳብ የሚጋሩት እና የድሮን ጥቃቶችን አዝማሚያ በመከታተል ጽሁፎችን ያሳተሙት ዶ/ር ዳንኤል ካሳሁን፤ “የተደበቁ ጉዳዮችን ሲፈለፍሉ የነበሩ ሚዲያዎች እና ድርጅቶች አሁን ሥራቸውን ያቆሙ ይመስላሉ” በማለት ይተቻሉ።

“. . . [በትግራይ ጦርነት] ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ሳተላይቶች ኢትዮጵያ ላይ አተኩረው ነበር። [የድሮን] እንቅስቃሴዎችን፣ ሲነሳ እና ሲያርፍ፣ አውሮፕላን ሲነሳና ሲያርፍ የካርጎ መጠኑን እየተነተኑ [ነበር]። ልክ የትግራይ ጦርነት ሲያበቃ ካሜራቸውን አጥፍተው. . . ከዚያ በኋላ ማንም አይናገርም” ሲሉ ይተቻሉ።

መርማሪዎች በበኩላቸው አካባቢዎችን ለመድረስ አስቸጋሪ መሆኑን በማንሳት፤ በመንግሥት እንደተዘጋባቸው ያነሳሉ።

ተጠያቂነት

ቢቢሲ ያሰባሰባቸው መረጃዎች የመንግሥት ኃይሎች ሰላማዊ ሰዎችን ባላገናዘበ ወይንም ከወታደራዊ ዒላማዎች ባልለየ የድሮን ጥቃቶች ንጹሃንን ሰዎች መገደላቸውን ይጠቁማሉ።

“ጦርነት የራሱ መንገድ አለው፤ አካሄድ አለው። [የጦርነት ሕግ] ታጣቂዎችን ከንጹሃን በነጠለ ሁኔታ መዋጋት እንዳለባቸው ያዛል። ያንን ለማድረግ እንኳን ሙከራ ፍላጎት የለም። የድሮን ጥቃቶቹ የሚፈጸሙባቸው ቦታዎች የሚያሳዩት የንጹሃንን መጨፍጨፍ ነው፤ [ይህንም] በተጨባጭ አይተናል” ይላሉ አቶ ሆነ ማንደፍሮ።

ኦሮሞ ሌጋሲ ሊደርሽፕ ኤንድ አድቮኬሲ አሶሲየሽን እና የአማራ ማኅበር በአሜሪካ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ሰላማዊ ሰዎች ሰለባ በሆኑባቸው የድሮን ጥቃቶች መንግሥት “ወንጀል” እየፈጸመ ነው ብለው ያምናሉ።

መንግሥት ግን በድሮን ጥቃቶቹ የሚገደሉ ንጹሃን አሉ ብሎ አያምንም። በዚህም በጥቃቶቹ የሚገደሉ እና የሚቆስሉ ንጹሃንን በተመለከተ ኃላፊነት ሲወስድ አልያም ተጠያቂ ሲሆን አይስተዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ንጹሃን ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት በጣም አሳሳቢ ነው የሚለው አምነስቲ፤ ይህም አፋጣኝ እርምጃ የሚሻ ነው ይላል።

“አሁን ያሉ ጥቃቶችን እያባባሱ ካሉ ምክንያቶች መካከል ዋነኛው ፍትሕ ማጣት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ያለመቀጣት (ተጠያቂ ያለመሆን) ሁኔታ አለ። ይሄ መሰበር አለበት፤ ፍትሕ መምጣት ያስፈልጋል” ሲልም ያክላል።

የአማራ ማኅበር በአሜሪካ የድሮን ጥቃቶችን ጨምሮ ንጹሃን ላይ እየደረሰ ነው ላለው ጥቃት ጫና ለመፍጠር ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ባለፈ በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ክስ ማቅረቡን አስታውቋል።

“በኢትዮጵያ መንግሥት የሚፈጸም የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲያቆም [ኮሚሽኑ] ጣልቃ እንዲገባ ጠይቀናል። የኢትዮጵያ መንግሥት መልስ እንዲሰጥ [ክሱ] ተልኮለት እየጠበቅን ነው” ብለዋል አቶ ሆነ።

በኦሮሚያ ውስጥ ያሉ የሰብአዊ መብት ጉዳዮችን ለአሜሪካ እና ለአውሮፓ ኅብረት መንግሥታት ማሳወቁን እንደሚቀጥል የሚገልጸው ኦሮሞ ሌጋሲ ሊደርሽፕ ኤንድ አድቮኬሲ አሶሲየሽን እርዳታ እና የገንዘብ ድጋፎች የመንግሥት የሰብዓዊ መብት አያያዝን በቅድመ ሁኔታነት የተመለከቱ እንዲሆኑ እወተውታለሁም ብሏል።

ሰላማዊ ሰዎችን ባላገናዘቡ የድሮን ጥቃቶች ንጹሃን ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች የጦር ወንጀል አሊያም በሰብዓዊነት ተብሎ በምርመራ የሚፈረጅ ነው።

“ሰው ሳይሞት አይቀበር”

“የታጠቀ ኃይል ያስታውቃል። [ቤተሰቦቼ] የለበሱት ነጠላ ነው፤ ነጫጭ ነበር የለበሱት። የታጠቀ ኃይል እንደዚያ ለብሶ አይሄድም። ፈጣሪ መድኃኒዓለም እሱ ይፍረደው እንጂ. . .” ሲሉ ጥቃቱ ለምን እንደደረሰ ማወቅ እንዳልቻሉ በድሮን ጥቃት ስምንት ቤተሰቦቻቸውን ያጡት አቶ ንጉሥ ሐዘን በሰበረው ድምጽ ይናገራሉ።

በደረሰባቸው ከባድ ሐዘን የተጎዱት አቶ ንጉሥ “ያልሞተ ሰው ሳይሞት አይቀበር” በማለት ያሉበትን ሁኔታ ከሞት እንደማያንስ በመግለጽ “ዝም ብሎ መኖር ነው እንግዲህ፤ እኛም እንደነሱ እስክንሆን [እስክንሞት] ድረስ። . . . አለን እንግዲህ፤ እየኖርን ነው እንግዲህ መኖር ከተባለ” ይላሉ።

ባለቤታቸውን እና ወንድማቸውን ጨምሮ ስምንት ቤተሰቦቻቸው በድሮን ጥቃት የተገደሉባቸው አቶ ንጉሥ ባለፈው ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም. ለቤተሰቦቻቸው ‘የመንፈቅ ሙት ዓመት’ የመታሰቢያ እና የፀሎት ሥነ ሥርዓት አካሂደዋል።

አቶ ንጉሥ ቤተሰባቸውን ላሳጣቸው ግድያ ፍትሕ አሊያም ካሳ አይፈልጉም፤ ይልቁንም እልቂቱ “በእኛ ይብቃ” ይላሉ፤ አሁንም ስጋታቸውን እየገለጹ።

“ከእንግዲህ በኋላ እንኳ በእኛ በቃ ብሎ ሌላ ሰው እንዲተርፍ ነው፤ ሌላ ምን እፈልጋለሁ? በእኛ ይብቃ። ሌላ ፈልጌስ ምን የማመጣው ነገር አለ? ምንም የለም። ስለዚህ በእኛ እንኳ እንዲበቃ፤… ሌላ ሰው እንዳይገደል ቢበቃ ይሻላል” ይላሉ።

*ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው የተቀየረ