ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ
የምስሉ መግለጫ,ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ከ1942 – 2017 ዓ.ም.

ከ 5 ሰአት በፊት

በአሁኑ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን ምሥራቅ ባዶዋቾ ሾኔ ከተማ አቅራቢያ ባለች ገጠራማ መንደር መጋቢት 1942 ዓ.ም. የተወለዱት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ኬንያ ውስጥ በህክምና ላይ ሳሉ በ74 ዓመታቸው አርፈዋል፡፡

የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የምሥራቅ ባደዋቾ በሾኔ፣ በኩየራ፣ በአዳማ የተከታተሉ ሲሆን፣ የከፍተኛ ደረጃ ትርምህርትን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በአሜሪካ ተምረዋል።

በሥነ ሕይወት የትምህርት ዘርፍ መምህርነት እና በተመራማሪነት በሠጡባቸው ረጅም ዓመታት ውስጥ ከማስተማር ጎን ለጎን ቁልፍ በሆኑ የጤና ዘርፍ ምርምሮች ላይ ጉልህ አስተዋጽኦን አበርክተዋል።

በወባ፣ በኤችአይቪ/ኤድስ፣ በሳምባ በሽታ እና በሌሎችም ተላላፊ በሽታዎች ላይ ወሳኝ ምርምር በማድረግ ስመ ጥር የሆኑት ምሁሩ እና ፖለቲከኛው ላበረከቱት ሙያዊ አስተዋጽኦ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተዋል።

ወታደራዊው መንግሥት ወድቆ ኢህአዴግ የሽግግር መንግሥት ሲያቋቁም ተሳታፊ የነበሩት ፕሮፌሰር በየነ፣ በወቅቱ ምክትል የትምህርት ሚኒስትር ሆነው ለአጭር ጊዜ አገልግለዋል።

ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ የትውልድ አካባቢያቸው እንደራሴ በመሆን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነዋል። በተለያዩ የፖለቲካ ፕረቲዎች እና የፓርቲዎች ጥረት ውስጥ በከፍተኛ አመራርነት ከ30 ዓመታት በላይ አስተዋጽኦ ያበረከቱት ፕሮፌሰር በየነ ስማቸው በተደጋጋሚ በበጎ ይነሳል።

በዩኒቨርስቲ ውስጥ በባልደረቦቻቸው እና በተማሪዎቻቸው መወደድ እና መከበርን ያተረፉት ፕሮፌሰር በየነ፣ ጽንፍ በያዘው በአገሪቱ ፖለቲካ መድረክ ላይ በነበራቸው ተሳትፎ ውስጥ የተለያዩ አመለካከቶችን ከሚያራምዱ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ጭምር ከፍ ያለ አክብሮት ያላቸው ፖለቲከኛ ነበሩ።

ፕሮፌሰር በየነ፡ ለትምህርት እና ለምርምር ቀናዒው

ማክሰኞ መስከረም 7/2017 ዓ.ም. ሕልፈታቸው የተሰማው ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በኢትዮጵያ ፖለቲካ እና የትምህርት ዘርፍ ስማቸው በጉልህ ይነሳል።

ለትምህርት፣ ለምርምር እንዲሁም ለአገር አንድነት እና ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ጉምቱ እና ግንባር ቀደም ፖለቲከኞች መካከልም ይጠቀሳሉ።

ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ ባሉት የአገሪቷ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ አሻራቸውን አኑረዋል።

በትምህርቱም ዘርፍ ቢሆን ያደረጉት አስተዋፅኦ ቀላል የሚባል እንዳልሆነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ትምህርት ከፍተኛ ተመራማሪው ተባባሪ ፕሮፌሰር በላይ ሐጎስ ይናገራሉ።

ለትምህርት ጥራት አብዝተው ይቆረቆሩ እንደነበር የሚናገሩት ፕሮፌሰሩ፣ በትምህርት ጥራት ላይ ለሚታየው ችግር ጥናቶች ተካሂደው መፍትሔ መገኘት አለበት ብለው የሚያምኑ ነበር ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ በቅርቡ እርሳቸው ያስጀመሩት ጥናት ለሕዝብ ይፋ ከመሆኑ በፊት በማረፋቸውም ተባባሪው ፕሮፌሰሩ የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።

ፕሮፌሰር በየነ ስለትምህርት የተለየ እውቀት እና ፍላጎት ነበራቸው።

በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ዘንድ የተመዘገበው ውጤት እጅጉን ያሳስባቸው እንደነበርም ተባባሪ ፕሮፌሰር ያስታውሳሉ።

“12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከተፈተኑት ውስጥ 3.2 በመቶዎቹ ብቻ ለምን አለፉ? ሥርዓታችን ትክክል አይደለም፤ በትምህርት ዘርፍ ሥራ እየሠራን አይደለም” የሚል ቁጭት ነበራቸው።

በዚህም ምክንያት ነው “ጥናት እንዲሠራ እና ለዚህ ጉዳይ መፍትሔ እንዲገኝለት የበኩላቸውን ጥረት እና ግፊት ሲያደርጉ ሞት ቀደማቸው እንጂ” ይላሉ ረ/ፕሮፌሰር በላይ።

ባልደረባቸው አክለውም ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በትምህርት እንዲሁም በጥናት እና በምርምር ሥራዎች ላይ ያላቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ይላሉ።

“የትምህርት ጥራት ከሌለ አገር መገንባት አይቻልም ብለው ያምናሉ። ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይም በትምህርት ላይ መፍሰስ አለበት ይሉ ነበር፤ የትምህርት ጥቅም ለሁሉም ዘርፍ ወሳኝ በመሆኑ ለውጥ እንዲመጣ የሚመኙ ታላቅ ሰው ነበሩ” ሲሉም ያስታውሷቸዋል።

ፕሮፌሰር በየነ በሥነ ሕይወት (ባዮሎጂ) በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ እና ምርምር አንቱ የተባሉ ምሁር ናቸው።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሥነ ሕይወት መማሪያ መጽሐፍትን ያዘጋጁ እንደነበር የሚያስታውሱት የቀድሞው ተማሪያቸው እና የተፈጥሮና ኮምፒውቴሽናል ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ፕሮፌሰር ጥልዬ ፈይሳ፣ ለሙያቸው እራሳቸውን የሰጡ እንደሆኑ ይመሰክራሉ።

“ፕሮፌሰር በየነ ታታሪ የሆኑ አንጋፋ እና የሚመሰገኑ ጠንካራ ሠራተኛ ነበሩ። የሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ጥናታዊ ጽሑፋቸውን በደንብ እያዩ ጥራት ያለው ሥራ እንዲሠሩ የሚያበራታቱ ነበሩ” ብለዋል።

ፕሮፌሰር በየነ የትምህርት እና የምርምር ሥራቸውን የጀመሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍል ነበር። የኢትዮጵያ ባዮሎጂካል ሶሳይቲ መሥራች እና ፕሬዚዳንት በመሆንም አገልግለዋል።

በተለይ በዘርፉ በወባ በሽታ ላይ ባካሄዷቸው በርካታ ጥናት እና ምርምሮች ስማቸው ይነሳል።

ቀደም ሲል ፓራሳይቶሎጂ በአሁኑ ደግሞ ተላላፊ በሽታዎች [ኢንፌክሽየስ ዲዚዝ] በተባለው የትምህርት ክፍል ውስጥ ከፍተኛ ምርምር ሲያደርጉ እንደነበሩ የሚያስታውሱት ፕሮፌሰር ጥልዬ፣ ካላቸው የላቀ እውቀት ባሻገር “በባህሪያቸው የሚመቹ ፣ የሚናገሩት መሬት ጠብ የማይል፣ የሚከበሩ ሰው ነበሩ” ይላሉ።

ፕሮፌሰር በየነ በአገር ደረጃ የሚታወቁ ትጉ ሰው ስለነበሩም እርሳቸው በሚሠሩበት ትምህርት ክፍል ሲመደቡ ተሰምቷቸው የነበረውን ደስታ የትናንት ያህል ነው የሚያስታውሱት።

ፕሮፌሰር በየነ፡ የሰላማዊ ፖለቲካ ትግል ምልክት

ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ከትምህርት እና ምርምር ዘርፍ ባሻገር ስማቸው በመላው አገሪቱ ጎልቶ በወጣበት የፖለቲካ ታሳትፏቸውም ያሳረፉት አሻራ ጉልህ ነው።

የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሊቀ መንበር የነበሩት ፕሮፌሰሩ፣ እምብዛም የርዕዮተ ዓለም ልዩነት የሌላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጣምረው በአንድነት እንዲሠሩ ሲጥሩ ቆይተዋል።

የቀድሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሊቀ መንበር እና አሁን የኢሶዴፓ ምክትል ሊቀ መንበር የሆኑት ዶ/ር ራሄል ባፌም ይህንኑ ያስረግጣሉ።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ መንገድ ፈታኝ እና ጠባብ በሆነበት ጊዜ በድፍረት ለሕዝብ የቆሙ ሰው ነበሩም ይሏቸዋል።

ፕሮፌሰር በየነ የኢትዮጵያን ዲሞክራሲ ማየት ምኞታቸውም፤ ጥረታቸውም ነበር የሚሉት ዶ/ር ራሄል፣ “በኢትዮጵያ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርን፣ የሥርዓት ለውጥን፣ ለሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት የመገዛትን፣ የሕግ የበላይነትን የማስፈን ጉጉት ነበራቸው። እናም በዚህ ሁኔታ ነበር በሰላማዊ መንገድ ሲፋለሙ የቆዩት” ብለዋል።

አክለውም ላለፉት ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ላለው ሰላማዊ የፖለቲካ መንገድም ፈር ቀዳጅ ነበሩ ይላሉ ዶ/ር ራሄል።

ፕሮፌሰር በየነ ሰላማዊ ፖለቲካ በታሰበ ቁጥር “በኢትዮጵያ ሕዝብ አዕምሮ ውስጥ የሚያቃጭሉ የሕዝብ ምልክት ናቸው” የሚሉት ዶ/ር ራሄል፣ ከእርሳቸው ብዙ ትምህርት መቅሰማቸውን ይናገራሉ።

“እኛ እንደ ፓርቲ፣ ከፓርቲ ባለፈ እንደ አባት፣ ከዚያም እንደ ቤተ መጽሐፍት ነበር በእርሳቸው ስንገለገል፣ ስንማር፣ ስንቀረጽ የነበረው። እስካሁን ድረስ ለብዙ ጥያቄዎቻችን ከእርሳቸው መልስ እናገኝ ነበር። . . . እኔም በእርሳቸው የተቀረጽኩ ሰው ነኝ” በማለት ምስክርነታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር በየነ፡ በኢትዮጵያ አንድነት ባለጽኑ አቋሙ

በርካታ ቁጥር ባላቸው እና የተለያየ ፍላጎት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በተፈጠሩበት ጊዜ ውስጥ ፕሮፌሰር በየነ በዋናነት በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ጽኑ አቋም ስላላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ በመቆም አገራቸውን አስቀድመው እንዲሠሩ ታግለዋል ይላሉ ዶ/ር ራሄል።

“እምብዛም የርዕዮተ ዓለም ልዩነት የሌላቸው በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አንድነት እንዲመጡ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ወደ ንግግር እንዲመጣ፣ ከጦርነት እና ከመጠላለፍ እንዲንወጣ የለፉ ሰው ናቸው።”

በሽግግር ወቅት የደቡብ ፓርቲዎችን ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን አስተባብረው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲ ኅብረት የተባለ የፖለቲካ ድርጅት በመመሥረት በተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ 17 መቀመጫዎችን ይዘው ነበር።

እሳቸው ሲመሩት የነበረው የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲም የ15 ፓርቲዎች ሕብረት ነው። እነዚህ ፓርቲዎች እንዲዋሃዱ አድርገው በአንድ ፓርቲ ሥር እንዲሠሩ ያዋቀሩ መሪ ናቸው- ፕሮፌሰር በየነ።

በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ከቅንጅት ጋር ዋነኛ ተፎካካሪ የነበረውን ኅብረት እንዲሁም ከዚያ በኋላ መድረክ የተባሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረትን ካቋቋሙ ቁልፍ ፖለቲከኞች መካከል ተጠቃሹ ናቸው።

“የውይይት አጀንዳዎችን ወደ ፊት በማምጣት የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደመተዳዳሪያ በሚቆጠሩበት እና በተከፋፈሉበት ወቅት ሳይቀር ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሃሳብ ደረጃ ተዋቅረው እንዲዋሃዱ ጥረት አድርገዋል” ይላሉ ዶ/ር ራሄል።

ከዚህም ባሻገርም ፕሮፌሰር በየነ ከሕዝብም ሆነ ከመሪዎች ጋር ሲሰሩ በዓላማ ፅናት እና በቅንነት እንደሆነ ዶ/ር ራሄል ይናገራሉ።

“በእርሳቸው ዓይን ሰው ሁሉ ሰብዓዊ እኩልነት ያለው ነው” ሲሉ ለአንዱ ያጋደለ እና የተንጋደደ አመለካከት እንዳልነበራቸው ያስታውሳሉ።

ፕሮፌሰር በየነ ከታኅሣሥ 2014 ዓ.ም ጀምሮ በመንግሥታዊው የፖሊሲ ጥናት ተቋም አምስተኛው ዳይሬክተር ጄነራል ሆነው እያገለገሉ ባሉበት ወቅት ነው ሕልፈታቸው የተሰማው።

ሕልፈታቸውን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና የተለያዩ አቋምን ያሚያራምዱ ፖለቲከኞች የተሰማቸውን ሐዘን እየገለጹ ነው።