ቡካዮ ሳካ

30 ነሐሴ 2024

ተሻሽሏል ከ 1 ሰአት በፊት

በአዲሱ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ መርሀ ግብር በመጀመሪያው ምሽት ጨዋታ ሊቨርፑል ኤሲ ሚላንን ሲረታ፣ ሪያል ማድሪድ እና አስተን ቪላ ድል ቀንቷቸዋል።

ዳይናሞ ዛግሬብን ያስተናገደው ባየር ሙኒክ 9-2 ባሸነፈበት ጨዋታ እንግሊዛዊው ሀሪ ኬን 4 ጎሎች ማስቆጠር ችሏል።

በሁለተኛው ምሽት የረቡዕ ጨዋታዎች ማንቸስተር ሲቲ ከኢንተር ሚላን የሚያደርጉት ፍልሚያ ይጠበቃል። ሐሙስ ምሽት ደግሞ አርሰናል ወደ ጣሊያን ተጉዞ ከአታላንታ ይጫወታል።

በአዲሱ መርሀ ግብር እያንዳንዱ ክለብ በመጀመሪያው ዙር ስምንት ጨዋታዎችን የሚያደርግ ሲሆን እንደቀድሞው የምድብ ማጣሪያ የሚባል ግጥሚያ የለም።

በቴክኖሎጂ የታገዘው የዕጣ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓት ከሳምንታት በፊት በሞናኮ መካሄዱ ይታወሳል። በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የምን ጊዜም ምርጥ ጎል አስቆጣሪ የሚል ሽልማት የተቀበለው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በዕጣ አወጣጡ ላይ ተገኝቷል።

የእንግሊዝ ቡድኖች ከማን ይጫወታሉ?

ከበርካታ ዓመታት በኋላ ወደ አውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የተመለሰው አስተን ቪላ በሜዳው ከባየር ሙኒክ፣ ጁቬንቱስ፣ ሴልቲክ እና ቦሎኛ ይጫወታል። ከሜዳው ውጭ ደግሞ ከላይፕዚግ፣ ክለብ ብሩገ የሚጫወት ሲሆን በመጀመሪያው ጨዋታ ያንግ ቦይስ 3-0 ረትቶ ተመልሷል።

አርሰናል ደግሞ በሜዳው ፓሪ ሳን ዠርማ፣ ሻክታር ዶኔትስክ፣ ዳይናሞ ዛግሬብ እና ሞናኮን ያስተናግዳል። ከሜዳው ውጭ ወደ ኢንተር ሚላን፣ አታላንታ፣ ስፖርቲንግ ሊዝበን እና ጂሮና ይጓዛል።

ሊቨርፑል የአምናውን ዋንጫ ባለቤት ሪያል ማድሪድ በሜዳው ሲያስተናግድ ሌቨርኩሰን፣ ሊል እና ቦሎኛ ወደ አንፊልድ መጥተው ይጫወታል። ከሜዳው ውጭ ደግሞ ከላይፕዚግ፣ ፒኤስቪ አይንድሆቨን እና ጂሮና ይፋለማል። በመጀመሪያው ጨዋታ ወደ ኤሲ-ሚላን ተጉዞ ድል ተቀዳጅቷል።

የካቻምናው ባለድል ማንቸስተር ሲቲ በሜዳው ኢንተር ሚላን፣ ክለብ ብሩገ፣ ፌይኖርድ እና ስፓርታ ፕራግን ይገጥማል። ከፒኤስጂ፣ ጁቬንቱስ፣ ስፖርቲንግ ሊዝበን እና ስሎቫን ብራቲስላቫ የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ከሜዳው ውጭ የሚከናወኑ ናቸው።

ተጠባቂ ጨዋታዎች

‘ሊግ ፌዝ’ ተብሎ በሚጠራው የመጀመሪያው ዙር ከአንድ ሀገር ሁለት ቡድኖች እርስ በርስ አይገናኙም። በአዲሱ መርሀ ግብር ተጠባቂ የሚባሉ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

የአምናው ሻምፒዮና ሪያል ማድሪድ ከአምናው የዋንጫ ተፋላሚ ቦሩሲያ ዶርትመንድ ጋር የሚፋለም ሲሆን ማድሪድ ከዶርትመንድ በተጨማሪ ኤሲ ሚላን እና አታላንታን ይጋጠማል።

የቀድሞው የሊቨርፑል አማካይ ዣቢ አሎንሶ ቡድኑ ባየር ሌቨርኩሰንን ይዞ ወደ አንፊልድ ይመጣል። በ2020 ፍፃሜ የተገናኙት ፓሪስ ሳን ዠርማ እና ባየር ሙኒክ በመጀመሪያው ዙር የሚገናኙ ሲሆን ፒኤስጂ ከአትሌቲኮ ማድሪድ የሚያደርጉት ጨዋታም ተጠባቂ ነው።

ባርሴሎና ደግሞ ከባየር ሙኒክ እና ቦሩሲያ ዶርትመንድ ይጫወታል።

የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ

አዲሱ ቻምፒዮንስ ሊግ እንዴት ነው የሚሠራው?

በአዲሱ ውድድር 36 ክለቦች በአራት ምድብ ሆነው ነው ለዕጣ ድልድል የቀረቡት።

እያንዳንዳቸው በመጀመሪያው ዙር 8 ጨዋታዎች የሚያደርጉ ሲሆን አራቱን በሜዳቸው አራቱን ደግሞ ከሜዳቸው ውጭ ያደርጋሉ።

የደረጃ ሰንጠረዡን ከ1-8 ስምንት ሆነው ያጠናቀቁ ቡድኖች ቀጥታ ወደ ዙር 16 የሚያልፉ ሲሆን ከ9-24 ባለው ደረጃ የሚያጠናቅቁ ደግሞ በደርሶ መልስ ጨዋታ በጥሎ ማለፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ለመሸጋገር ይጫወታሉ።

ከ25ኛ በታች ሆነው ያጠናቀቁ ክለቦች ከውድድሩ ውጭ የሚሆኑ ሲሆን ወደ አውሮፓ ሊግ ውድድርም አይሻገሩም።

በአዲሱ ቅርፅ መሠረት በቻምፒዮንስ ሊጉ በጠቅላላው የሚደረጉ ጨዋታዎች ከ125 ወደ 189 ያድጋሉ። በቀድሞው አሠራር በምድብ ድልድል አንድ ክለብ 6 ጨዋታዎች ነበር የሚያደርገው። በአዲሱ መርሀ ግብር አንድ ቡድን ቢያንስ 8 ጨዋታዎች፤ እስከ ዋንጫው ከዘለቀ ደግሞ 17 ጨዋታዎችን ሊያደርግ ይችላል።

የዘንድሮው ቻምፒዮንስ ሊግ በአውሮፓውያኑ መስከረም 17 ይጀምራል። ሊግ ፌዝ የተባለው የመጀመሪያው ዙር እስከ ፈረንጆቹ ጥር መጨረሻ ድረስ ይዘልቃል።

ማክሰኞ ምሽት ከተደረጉት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች በኋላ ባየር ሙኒክ በግብ ክፍያ ቀድሞ የሰንጠረዡ አናት ላይ ተቀምጧል። አስተን ቪላ እና ሊቨርፑል ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነው ይከተላሉ።