የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ከሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ ጋር

ዜና ኢጋድ ኢትዮጵያና ሶማሊያን ለማደራደር ጥረት መጀመሩ ተሰማ

ዮሐንስ አንበርብር

ቀን: September 18, 2024

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ)፣ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ውጥረት በድርድር ለመፍታት ጥረት መጀመሩ ተሰማ።

በኢጋድ ዋና ጸሐፊ የሆኑት ኢትዮጵያዊው ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ በሶማሊያ ሞቃዲሾ ተገኝቶ ከሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር የተወያየ ሲሆን፣ ይህንንም የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤትና ራሱ ኢጋድ በይፋ አስታውቀዋል።

የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፣ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ ከኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ (ዶ/ር) በነበራቸው ውይይት የቀጣናውን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ በትብብር ለመሥራት መስማማታቸውን ገልጿል።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የዲፕሎማቲክ ምንጮች ደግሞ የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወደ ሶማሊያ የተጓዙት ሁለት ግቦችን ለማሳካት እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል።

የመጀመሪያው ዓላማ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ያለውን ውጥረት በውይይት ለመፍታት ያለመ ሲሆን፣ ይህንንም ለማሳካት የጂቡቲ፣ የኬንያና የአሜሪካ መንግሥታት ድጋፍ ከጀርባ መኖሩን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በሶማሌላንድ በኩል የባህር በር ለማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ስምምነት እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 2024 በአዲስ አበባ ከተፈራረመች በኋላ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ከፍተኛ ፖለቲካዊ ውጥረት መፈጠሩን ያስታወሱት የዲፕሎማቲክ ምንጮቹ፣ በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ በቱርክዬ መንግሥት ሲደረግ የነበረው ጥረት የሚፈለገውን ውጤት እንዳላስገኘ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ሶማሊያ በቱርክዬ መንግሥት አሸማጋይነት የጀመሩት ድርድር ሦስተኛው ዙር በዚህ ሳምንት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቅ የነበረ ቢሆንም፣ ድርድሩ መቋረጡ ወይም መተላለፉ ይፋዊ በሆነ መንገድ ሳይገለጽ የቀጠሮው ቀን አልፏል።

በአንካራ የተጀመረው ድርድር የሚቀጥልበት ተስፋ የለም የሚሉት የዲፕሎማቲክ ምንጮች፣ ከዚህ ይልቅ በኢጋድ በኩል አዲስ ድርድር ለማድረግ በሁለቱም መንግሥታት በኩል ፍላጎት መኖሩን ገልጸዋል።

የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ (ዶ/ር) ቀደም ሲል የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩ መሆኑን ያስታወሱት ምንጮቹ፣ ዋና ጸሐፊው አሁንም በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ተሰሚነት ያላቸው በመሆኑ ድርድሩ የመሳካት ዕድል እንደሚኖረው አክለዋል።

ወርቅነህ (ዶ/ር) በሶማሊያ የነበራቸውን ቆይታ አስመልክቶ በሞቃዲሾ መግለጫ በሰጡበት ወቅት፣ የአገሪቱ የሚዲያ ተቋማት የዋና ጸሐፊውን ዜግነት መነሻ አድርገው ኢጋድ የሶማሊያን ሉዓላዊ ግዛትና አንድነት በማክበር ረገድ ያለውን አቋም ግልጽ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። ዋና ጸሐፊው በሰጡት ምላሽ፣ ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የመግባቢያ ስምምነቱን በተፈራረሙበት ወቅት የሶማሊያ ሉዓላዊነት እንዲከበር በቅድሚያ ጥሪ ያቀረበው ኢጋድ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢጋድ ኢትዮጵያና ሶማሊያን ለማደራደር ከያዘው ዕቅድ በተጨማሪ፣ ከሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ጋር የቆየ ቅርበት ያላቸውን የሶማሊያ ባለሥልጣናትን በማሳተፍ የሱዳን ጦር ኃይሎች አዛዥ ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃንና የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ መሐመድ ዳጋሎን ለማድራደር እንደሚፈልግ፣ የዋና ጸሐፊው የሶማሊያ ቆይታ ሌላኛው ዓላማም ይህ እንደሆነ ምንጮች ጠቁመዋል።

ሶማሊያ ከሱዳን ጋር የድንበር ግንኙነት የሌላት በመሆኑና ባለፉት ዓመታት በቀጣናው በተለይም በሱዳን ፖለቲካ ውስጥ አሉታዊ ተሳትፎ አለማድረጓ፣ በሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ተዓማኒነት ልታገኝ እንደምትችልም ምንጮች አስረድተዋል።