የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴን ውይይት ሊቀመንበሩ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) እና ምክትላቸው አቶ አማኑኤል አሰፋ ሲመሩ

ዜና ሕወሓት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ በ16 አመራሮቹ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ አሳለፈ

ዮሐንስ አንበርብር

ቀን: September 18, 2024

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ሲያካሂድ የነበረውን ስብሰባ ሰኞ መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም. አጠናቆ ባወጣው መግለጫ፣ ራሳቸውን ከ14ኛ የሕወሓት ጉባዔ ያገለሉትን አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ በ16 የቀድሞ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ላይ የመጨረሻ ያለውን ውሳኔ ማሳለፉን አስታወቀ።

ሕወሓት ባወጣው መግለጫ አቶ ጌታቸውን ጨምሮ 16 የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ሆነ ብለው ራሳቸውን ከ14ኛው የሕወሓት ጉባዔ በማግለል ፓርቲውን ለማፍረስ ሙከራ ያደረጉ ቢሆንም፣ በፓርቲው ደንብ መሠረት ይቅርታ ጠይቀው እንዲመለሱ ተወስኖ የነበረ መሆኑን አስታውሷል።

እነዚህ ከፍተኛ አመራሮች ከስህተታቸው በመማር ይቅርታ ጠይቀው እንዲመለሱ የሕወሓት ጉባዔ የተሰጣቸውን ዕድል ይጠቀማሉ በሚል ፓርቲው ለአንድ ወር የጠበቀ ቢሆንም፣ ግለሰቦቹ ከስህተታቸው ተምረው ይቅርታ ከመጠየቅ ይልቅ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ያላቸውን ሥልጣን በመጠቀም ሕወሓትን ለማጥፋትና የትግራይን ሕዝብ አንድነት የመበተን እንቅስቃሴያቸውን መቀጠላቸውን በመግለጫው ገልጿል።

በመሆኑም አቶ ጌታቸውን ጨምሮ 16 የሕወሓት የቀድሞ አመራሮች ከፓርቲው እንዲባረሩና የፓርቲ ውክልናቸውም እንዲሳ መወሰኑን አስታውቋል።

በዚህም መሠረት 16ቱ የሕወሓት የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮች ከሕወሓት አባልነት ሙሉ በሙሉ እንዲሰናበቱ ተወስኗል ያለው የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ እነዚህ የቀድሞ አመራሮች በሕወሓት ስም ስም መንቀሳቀስ የማይችሉ መሆኑን አስታውቋል። በተጨማሪም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር ከፓርቲው የተባረሩት እነዚህ የቀድሞ አመራሮች፣ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ከያዙት ኃላፊነት ተነስተው በምትካቸው ሌሎች እንዲሾም ለማድረግ እንደሚሠራ አስታውቋል። 

ከሕወሓት አባልነት የተሰናበቱና ከፓርቲ ውክልና የተነሱት የቀድሞ አመራሮች አቶ ጌታቸው ረዳ፣ አቶ በየነ ምክሩ፣ ክንደያ ገብረ ሕይወት (ፕሮፌሰር)፣ሓጎስ ጎደፋይ (ዶ/ር)፣ ወ/ሮ አልማዝ ገብረፃዲቅ፣ አቶ ረዳኢ ሐለፎም፣ ወ/ሮ ሰብለ ካህሳይ፣ አቶ ነጋ አሰፋ፣ አቶ ኢሳያስ ታደሰ፣ አቶ ሰለሞን ማዓሾ፣ አቶ ሺሻይ መረሳ፣  ገብረ ሕይወት ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር)፣ አቶ ርስቁ አለማው፣ አቶ ሃፍቱ ኪሮስ፣ አቶ ብርሃነ ገብረ ኢየሱስና አቶ ሩፋኤል ሽፋረ ናቸው።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም በየደረጃው የሚገኙ የአመራር እርከኖችና የሕዝቡን አንድነት ለማደፍረስ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ተመሳሳይ ዕርምጃ መውሰድ እንደሚቀጥልም የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አስታውቋል።

በሌላ በኩል ሕወሓት በውስጡ ያለውን የጥገኝነትና የመበስበስ አደጋ የገመገመና የተቸ ቢሆንም፣ በነበረው መድረክ የመጨረሻ ድምዳሜ ያልተሰጠ መሆኑን በማስታወስ፣ በመድረኩ በሙስና የተጠረጠሩ የቀድሞ አመራሮች ላይ ሕጋዊ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ መወሰኑን አስታውቋል።

በዚህም መሠረት የሚመለከታቸው የትግራይ የፍትሕና የፀጥታ አካላት አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ በሙስና የተጠረጠሩትን የቀድሞ የሕወሓት አመራሮች በሕግ እንዲጠየቁ የማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ፣ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በመግለጫው ጥሪውን አቅርቧል።