September 18, 2024

በሙሉጌታ በላይ

ከሶስት ወራት በፊት ከእስር የተፈቱት ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው እና በላይ ማናዬ፤ ሀገራቸውን ለቅቀው ለመሰደድ መገደዳቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ሁለቱ ጋዜጠኞቹ የተሰደዱት፤ በመንግስት የጸጥታ አባላት በተሰጣቸው “ለህይወታቸው የሚያሰጋ” “ማስጠንቀቂያ” እና ከእስር ከተፈቱ በኋላ በሚደረግባቸው “ክትትል” ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል።

ጋዜጠኛ በላይ እና በቃሉ 11 ቀናት የፈጀ “አስቸጋሪ ጉዞ” በማድረግ ከሀገር የወጡት፤ ባለፈው ሳምንት ሰኞ ጳጉሜ 4፤ 2016 መሆኑን አስረድተዋል። ሆኖም ጋዜጠኞቹ በአሁኑ ወቅት ያሉበትን ሀገር፤ “ከደህንነት ስጋት” ጋር በተያያዘ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

ሁለቱ ጋዜጠኞች ለእስር ተዳርገው የነበረው፤ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ባበቃው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ነበር። በአማራ ክልል እና እንዳስፈላጊነቱ ደግሞ “በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ” ተፈጻሚነት የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ የተላለፈው ሐምሌ 28፤ 2015 ነበር

Post

Ethiopia Insider

@ethiopiainsider

የ“አልፋ ሚዲያ” መስራች እና ባለቤት የሆነው ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው፤ ለ4ተኛ ጊዜ በፖሊስ ቁጥጥር

ስር ዋለ። በቃሉ በፖሊስ የተያዘው የሁለተኛ ዲግሪ ምርቃቱን ከቤተሰቦቹ ጋር እያከበረ ባለበት ወቅት ነው

ተብሏል።

* ለዝርዝሩ፦ https://ethiopiainsider.com/2023/11707

Translate post

Image

·17.4K Views

53 Reposts 3 Quotes 150 Likes

“አልፋ ሚዲያ” የተሰኘው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን መስራች እና አዘጋጅ የሆነው በቃሉ፤ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አንድ ቀን በኋላ በቁጥጥር ስር ውሏል። ጋዜጠኛው በዚያው ዓመት ነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ ወደ አዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ተወስዶ ለዘጠኝ ወራት በእስር ላይ ቆይቷል።

በአፋር ክልል በሚገኘው በዚሁ ወታደራዊ ካምፕ የነበረውን ቆይታ፤ በቃሉ “እጅግ አሰቃቂ” ሲል ይገልጸዋል። በወታደራዊ ካምፑ ይደርስባቸው በነበረው እንግልት ምክንያት “እንደምንሞት ነበር የምናስበው” ሲል በወቅቱ የነበረባቸውን ጭንቀት ያስታውሳል።

“አዋሽ አርባ ቃል የሚገልጸው ነገር አይደለም። ወታደራዊ ካምፕ ነው። ከፍተኛ ወታደራዊ ልምምድ አለ። ወታደሮች የሚያደርሱብህ ጫና አለ። ከፍተኛ ተኩስ፣ ከባድ መሳሪያ ነው የሚሰማው። ከዚያ ደግሞ ምርመራ ተብሎ የሚደረግ አለ” ሲል በቃሉ በወታደራዊ ካምፑ የነበረውን ሁኔታ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል። 

ጋዜጠኛው በወታደራዊ ካምፑ ውስጥ ባሉ መርማሪዎች፣ ፌደራል ፖሊሶች እና የደህንነት አባላት “ዛቻ እና ማስፈራሪያ” ይደርስባቸው እንደነበር ጨምሮ ገልጿል። በተጠቀሱት የጸጥታ ኃይሎች “በማንኛውም ሰአት እንገላችኋለን”፣ “ትዕዛዝ እስኪሰጠን ነው የምጠብቀው” ይባሉ እንደነበርም አክሏል። 

እንደ በቃሉ ሁሉ በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ታስሮ የነበረው ጋዜጠኛ በላይ፤ “በየቀኑ በህይወት የመቆየት እና ያለመቆየት እድላችን ሁልጊዜ ጠባብ እንደሆነ እያሰብን ነው ያን ሁሉ ጊዜ የቆየነው” ሲል ይገልጻል። “ኢትዮ ኒውስ” የተሰኘው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ በላይ፤ በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ በእስር ላይ የቆየው ለሰባት ወራት ነው።

በህዳር 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው በላይ፤ ወደ አዋሽ አርባ የተወሰደው በዚያኑ ወር መጨረሻ ላይ ነበር። በወቅቱ የታሰረበትን ቦታ ቤተሰብ አለማወቁ፤ “አስጨናቂ ስነ ልቦና” ውስጥ ከትቶት እንደነበር ጋዜጠኛ በላይ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል። በካምፑ ውስጥ የነበረው ተኩስ፣ የሚካሄደው ወታደራዊ ስልጠና እና ተላላፊ በሽታዎች ሌሎች “አስጨናቂ” ጉዳዮች እንደነበሩም ገልጿል። 

ከዚህ በተጨማሪ የካቲት 7፤ 2016 በወታደራዊ ካምፑ አውሎ ነፋስ ተከስቶ፤ በቀኝ እግሩ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት በላይ ያስረዳል። አደጋው የደረሰው፤ በስፍራው የታሰሩ እስረኞች ለእራት በወጡበት ሰዓት እንደነበር ያስታውሳል።  

“አምስት ቤቶች ነበሩ። የመመገቢያ አዳራሽ፣ የፖሊስ ቢሮ፣ እንደ ክሊኒክ የሚጠቀሙበት ቤት ነበር። እሱን ሁሉ [አውሎ ነፋሱ] ወሰደ። ስቶሮች ነበሩ፤ እነሱን ሁሉ ነቃቅሎ ሲወስድ፤ ቤቱንም ከላያችን ላይ ነው ያነሳው። በወቅቱ ወደ ስድስት ልጆች ጉዳት ደርሶብን ነበር” ሲል በላይ በዕለቱ የደረሰውን አደጋ ያብራራል።   

“ከፍተኛ ጉዳት ደርሶብኝ የነበረው ቀኝ እግሬ ላይ ነው። ለተወሰነ ጊዜ እራሴን አላውቅም ነበር። በወቅቱ ህክምና ማግኘት አልቻልንም ነበር። የቴታነስ መርፌ ብቻ ነው መከላከያ ክሊኒክ ውስጥ ሄደን ያገኘነው” ሲልም ጋዜጠኛው ያክላል። በተመሳሳይ ሁኔታ ጋዜጠኛ በቃሉም በአዋሽ አርባ ቆይታው “በከባድ ደረጃ” ታምሞ እንደነበር ገልጿል።

Post

Ethiopia Insider

@ethiopiainsider

“ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ” በእስር ላይ የሚገኙ 3 ጋዜጠኞች፤ “አካልን ነጻ የማውጣት” አቤቱታ

ለፍርድ ቤት አቀረቡ። አቤቱታውን ያቀረቡት ጋዜጠኞች በቃሉ አላምረው፣ በላይ ማናዬ እና ቴዎድሮስ ዘርፉ

ናቸው።

ለዝርዝሩ https://ethiopiainsider.com/2024/13301/

Translate post

Image

·4,457 View
12
Reposts
25 Likes 1 Bookmarks

በቃሉ ያጋጠመው ህመም “ከፍተኛ የአንጀት እና የጉበት መድማት” በመሆኑ፤ በጥር 2016 ዓ.ም. ለተሻለ ህክምና ከአዋሽ አርባ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ ተደርጎ ነበር። በአዲስ አበባው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ በሚገኘው የእስረኞች ማቆያ ለሁለት ወራት ከተዛወረ በኋላ፤ “ህክምናውን ሳይጨርስ” በሚያዚያ ወር በድጋሚ ወደ ወታደራዊ ካምፑ ተመልሷል። 

በዚህ ሁኔታ በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ በእስር የቆዩት ሁለቱ ጋዜጠኞች፤ ከእስር ከመፈታታቸው አስቀድሞ በድጋሚ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እንዲቆዩ ተደርገዋል። ሁለቱም ጋዜጠኞች በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ በነበራቸው ቆይታ፤ “ሲቪል በለበሱ መርማሪዎች” ተመሳሳይ “ማስጠንቀቂያ” እንደተሰጣቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

“ሶስት ሆነው መጡ። ሲቪል የለበሱ ናቸው። የፌደራል ፖሊስ መርማሪ አባል ጭምር አለ፤ አራተኛ ማለት ነው። [የተነገረን] ሙሉ ለሙሉ ማስጠንቀቂያ ነው። ‘ሁሉንም ነገር እናውቃለን። የትኛውም ሚዲያ ላይ እንዳትቀርቡ፤ አርፋችሁ ቁጭ በሉ። በፈለግነው ሰዓት፤ የምንፈልገውን እርምጃ እንወስድባችኋለን። እርምጃ የምንወስድባችሁ እኛ ነን። ተዋወቁን” ብለውናል ሲል ጋዜጠኛ በቃሉ በወቅቱ በመንግስት የጸጥታ አባላት የተነገረውን አስታውሷል።    

“[የተነገረን] ሙሉ ለሙሉ ማስጠንቀቂያ ነው። ‘ሁሉንም ነገር እናውቃለን። የትኛውም ሚዲያ ላይ እንዳትቀርቡ፤ አርፋችሁ ቁጭ በሉ። በፈለግነው ሰዓት፤ የምንፈልገውን እርምጃ እንወስድባችኋለን። እርምጃ የምንወስድባችሁ እኛ ነን። ተዋወቁን [ብለውናል] ”– ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው ከመንግስት የጸጥታ አባላት የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ በተመለከተ የተናገረው

እነዚሁ የጸጥታ አባላት “ስልካችሁን ይዘናል። የባለቤቶቻችሁን ስልክ ይዘናል። የምትኖሩበት ቤት ይሄ ነው። ስለዚህ ስልካችሁን እና መኖሪያችሁን መቀየር አትችሉም። በማንኛውም ሰዓት ስንፈልጋችሁ መጥተን እንወስዳችኋለን” የሚል ማስጠንቀቂያ ጭምር እንደሰጧቸው በቃሉ ገልጿል። በዚህ “ማስጠንቀቂያ” እና ከእስር ከተፈቱበት ከሰኔ 2016 ዓ.ም. በኋላ በሚደረግባቸው “ክትትል” ምክንያት ከሀገር መሰደዳቸውን በቃሉ ገልጿል። 

“በዋናነት ይህ ውሳኔ የመጣው በተሰጠን ማስጠንቀቂያ ነው። እና ወደ ሙያችን መመለስ እንደማንችል ስናውቅ ነው። ተከራይተን ወደነበርንበት ቢሮ እንኳን መሄድ አልቻልንም። ስራችንን፣ ሙያችንን መቀጠል አልቻልንም። ያ ሁሉ ደግሞ የሚሆነው በህይወት ስንኖር ነው። ስለዚህ በህይወት የመኖር እድላችን ጠባብ እንደሆነ ስለነገሩን፤ በማንኛውም ሁኔታ እርምጃ ሊወስዱብን እንደሚችሉ ስለነገሩን፣ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ከሀገር [ወጥተናል]” ሲል ጋዜጠኛ በቃሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል።  

ሁለቱ ጋዜጠኞች በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ በነበሩበት ወቅት በመንግስት የጸጥታ አባላት እና መርማሪዎች ተሰጥቶናል ስላሉት “ማስጠንቀቂያ” ጥያቄ የቀረበላቸው የፌደራል ፖሊስ ቃል አቃባይ ጄይላን አብዲ፤ ስለ ጉዳዩ “መረጃው የለንም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ሆኖም የፌደራል ፖሊስ “የወንጀል ምርመራን” የሚያካሄደው “ሰብአዊ መብትን በማይጥስ መልኩ” እንደሆነ ገልጸዋል።

እርሳቸው ይህን ቢሉም ጋዜጠኛ በቃሉ ግን በእስር ላይ በነበረበት ወቅት ስለደረሰበት የሰብአዊ መብት ጥሰት፤ ብሔራዊው የሰብአዊ መብት ተቋም ለሆነው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሪፖርት ማድረጉን አመልክቷል። በኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ስራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ፤ ተቋማቸው የጋዜጠኛ በቃሉን “ቃል መቀበሉን” ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። 

ሁለቱ ጋዜጠኞቹ በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ደረሰብን ስላሉት “እንግልት” እና “ሰብአዊ መብትን የጣሰ አያያዝ” በተመለከተ፤ የመከላከያ ሚኒስቴር እና የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም። ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (ሲፒጄ) ባለፈው ሰኔ ወር በወጣው ሪፖርት፤ በርካታ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች “ለህይወታቸው በመስጋት” መሰደዳቸውን አመልክቶ ነበር። 

ሲፒጄ ባጠናቀረው መረጃ መሰረት፤ ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ ከኢትዮጵያ የተሰደዱ ጋዜጠኞች ብዛት በትንሹ 54 ይደርሳል። አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች የሚሰደዱት ወደ “ጎረቤት የአፍሪካ ሀገራት” መሆኑን በሪፖርቱ ያመለከተው ሲፒጄ፤ የተቀሩት ሀገራቸውን ለቅቀው ወደ አውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ ለመሄድ መገደዳቸውን ጠቁሟል። 

ከጋዜጠኛ በላይ ማናዬ ጋር “ኢትዮ ኒውስ” የተሰኘውን የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን የመሰረተው በለጠ ካሳ፤ ባለፈው አንድ ዓመት ለስደት ከተዳረጉ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ መሆኑን ሲፒጄ በሪፖርቱ አመልክቷል። በለጠ በጸጥታ ኃይሎች በሚደረግበት ክትትል ምክንያት ለወራት ከተሸሸገ በኋላ ሀገሩን ጥሎ የተሰደደው ከስምንት ወራት በፊት ነው። 

ከአንድ ሳምንት በፊት የተሰደዱት ጋዜጠኛ በላይ እና በቃሉ በበኩላቸው“በህይወት ለመኖር ስንል የማንፈልገውን ውሳኔ ወስነናል” ብለዋል። ጋዜጠኞቹ “ሁኔታዎች ሲመቻቹ” ካሉበት ሆነው በሙያቸው ለመቀጥል ዕቅድ አላቸው። “ሙያችን፣ ማንነታችን ወንጀል ሆኖብን ስንሳደድ ከቆየን በኋላ፤ አሁን ደግሞ እድል ካገኘን በቀጥታ ሙያችንን መስራት፤ የቆየንበትን ስራ መቀጠል ነው” ሲል በላይ ወደ ጋዜጠኝነት ስራ ለመመለስ ያላቸውን እቅድ ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)