ናርዶስ ዮሴፍ

September 18, 2024

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ የሚረከበው ኤርባስ 350-1000 ግዙፍ አውሮፕላን

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ አኅጉር የመጀመሪያውንና ከ350 እስከ 410 መንገደኞች ማሳፈር የሚያስችለውን ግዙፍ ኤርባስ አውሮፕላን በጥቅምት ወር እንደሚረከብ ታወቀ።

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ አየር መንገዱ ከአውሮፓው አውሮፕላን አምራች ድርጅት ኤርባስ ያዘዘውን ኤ350-1000 በመባል የሚታወቀውን ግዙፍ አውሮፕላን በጥቅምት ወር ርክክብ ይፈጽማል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኤርባስ እ.ኤ.አ. እስከ 2022 ድረስ የኤ350 ቤተሰብ በመባል ከሚታወቁት ሁለት የአውሮፕላን ዓይነቶች ማለትም ኤ350-900 እና ኤ350-1000 ሃያ ሁለት አውሮፕላኖችን ለመረከብ የግዥ ትዕዛዝ ፈጽሞ የነበረ ሲሆን፣ የመጀመሪያውን በተረከበበት ወቅትም ከአፍሪካ ብቸኛው የአውሮፕላኑ ባለቤት እንደነበር አይዘነጋም።

በወቅቱ ከ22 አውሮፕላኖች መካከል እስከ ሐምሌ ወር 2022 ድረስ ኤርባስ 16 ያህሉ ማቅረቡን አየር መንገዱ በወቅቱ ማሳወቁ ይታወሳል።

አዲሱን አውሮፕላን በሚመለከት ሪፖርተር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሚመለከታቸው ኃላፊ ጥያቄ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም፣ የርክክቡ ቁርጠኛ ቀን መቼ እንደሆነ ከመግለጽ ተቆጥበዋል። ነገር ግን ምንጮች አየር መንገዱ አዲስ የሚያስገባው ግዙፍ አውሮፕላን ዓይነት ያዘዘው ብዛት አራት መሆኑን አረጋግጠዋል።

የሪፖርተር ምንጮች አራቱም አውሮፕላኖች በአንድ ጊዜ ርክክብ የሚፈጸምባቸው ሳይሆኑ በቅድሚያ በመጪው ጥቅምት ወር የመጀመሪያውን ርክክብ ከተካሄደ በኋላ፣ በተከታታይ ጊዜያት ከአምራቹ የጊዜ መርሐ ግብር ጋር እየታየ በስምምነቱ መሠረት ለአየር መንገዱ እንደሚቀርቡ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በጥር ወር 2016 ዓ.ም. የአየር መንገዱን የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ መግለጫ ሲሰጡ፣ አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅ ከሆኑት የቦይንግና የኤርባስ ኩባንያዎች ጋር በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት 124 አውሮፕላኖችን ለመረከብ የሚያስችለው ስምምነቶችን መፈጸሙን አስታውቀው ነበር።

ከእነዚህም ውስጥ 70 አውሮፕላኖችን የግዥ ግዴታ ውል የተፈጸመባቸው እንደሆኑ ሲገለጽ፣ የተቀሩት 54 አውሮፕላኖችን በተመለከተ ከአምራቾች ጋር የዋጋና የርክክብ ቀን ስምምነት ላይ ተደርሶ ነገር ግን አስገዳጅ ውል ያልተፈጸመባቸው እንደሆኑም መግለጻቸውን መዘገባችን አይዘነጋም።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው በወቅቱ፣ ‹‹ከአምራቾች በኩል አውሮፕላን የማስረከቢያ ቀናቸውን በራሳቸው ችግር ወደፊት የመግፋት ነገር አለ። ቢሆንም ተከታትለን እነዚህን አውሮፕላኖች ለማስገባት እንሞክራለን፤›› ብለው ነበር።