ዜና
በአማራ ክልል ለሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት በመንፈጉ ተወቀሰ

ዮናስ አማረ

ቀን: September 18, 2024

የአማራ ማኅበር በአሜሪካ (Amhara Association of America) የተባለው ለአማራ ተወላጆች ሰብዓዊ መብቶች መከበር የሚሠራው ድርጅት ማክሰኞ መስከረም 7 ቀን 2017 ባወጣው ሪፖርት፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአማራ ላይ ይፈጸማል ያለውን ብሔር ተኮር ጥቃትና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ዓይቶ እንዳላየ በመሆን ያልፈዋል ሲል ወቀሳ አቀረበ፡፡

ድርጅቱ በአዲሱ ሪፖርቱ ባለፈው አንድ ዓመት ማለትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀበት ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. እስከ ሐምሌ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ባለው ጊዜ፣ በአማራ ክልል የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ይፋ ከማድረግ በተጨማሪ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለዚህ ቀውስ የሰጠውን ምላሽ ሚዛን የጎደለው ነው ሲል ተችቷል፡፡  

የጉዳት ሰለባ የሆኑ ሰዎችንና ቤተሰቦቻቸውን በቀጥታ በመጠየቅ፣ የተለያዩ አገር በቀልና የውጭ መገናኛ ብዙኃን፣ እንዲሁም የሲቪክ ማኅበራት ድርጅቶች ሪፖርቶችን በማገናዘብና የባለሙያዎችን መረጃ መሠረት በማድረግ አዘጋጀሁት ያለው ባለ 138 ገጽ የድርጅቱ ሪፖርት የአማራን ማኅበረሰብ ዒላማ ያደረጉ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በአማራ ክልልና ከአማራ ክልል ውጪም ተፈጽመዋል ብሏል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁንና በክልሉ ጦርነት መፋፋሙን ተከትሎ በመላው ኢትዮጵያ የአማራ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ የዘፈቀደ እስራት ሲፈጸም ነበር ይላል፡፡ ከቦታ ወደ ቦታ በሚንቀሳቀሱ አማሮች ላይ አስገድዶ ማስቆምና መፈተሽ፣ አስገድዶ ገንዘብ መቀበል ይፈጸም ነበር የሚለው ሪፖርቱ የሚታሰሩትን ደግሞ ቤተሰብ፣ ጠበቃም ሆነ የሰብዓዊ መብት ባለሙያ በማያገኙበት፣ ንፅህና በጎደለውና የጤና አገልግሎት በሌለው ቦታ እንዲቆዩ የማድረግ ዕርምጃ ሲወሰድ መቆየቱን ያትታል፡፡

በተለይ በአዲስ አበባ ከተማና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የፋኖ ደጋፊና አባላት ናቸው በሚል የአማራ ተወላጆች ለጅምላ እስራት፣ እንግልትና መፈናቀል ሲጋለጡ መቆየታቸውን የጠቀሰው ሪፖርቱ በአማራ ክልል የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ወንጀሎች እንዳይዘገቡ ጭምር የቴሌኮምና የኢንተርኔት አገልግሎት የማቋረጥ ዕርምጃ ሲወሰድ ቆይቷል ሲል አስታውቋል፡፡

ከዚህ በከፋ ሁኔታ ደግሞ ባለፈው አንድ ዓመት በርካታ አማራዎች ላይ የአስገድዶ መድፈርና ፆታዊ ወንጀሎችን ጨምሮ ግድያዎችና የአካል ጉዳት ወንጀሎች እንደተፈጸሙ ነው በሪፖርቱ የተካተተው፡፡

ከኦሮሚያ ክልል በአማሮች ላይ እየተፈጸመ ነው ያለውን ማፈናቀል ጨምሮ፣ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የአማራ ተወላጆች ከኖሩበት ቀዬና መንደር በተለያዩ መንገዶች መፈናቀላቸውን ይጠቅሳል፡፡ ይህ ደግሞ በክልሉ የሚካሄደው ጦርነት ከፈጠረውና፣ ድርቅና ረሃብ ከመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ጋር ተዳምሮ፣ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለአስቸኳይ የሰብዓዊ ዕርዳታ ጠባቂነት እንዲዳረጉ ያደረገ መሆኑን አክሏል፡፡

‹‹በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መቀጠላቸውን የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች ቢኖሩም፣ ምዕራባውያን መንግሥታትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለጉዳዩ ትኩረት ነፍገውታል፤›› ሲል ነው ድርጅቱ ከሪፖርቱ ጋር አያይዞ ባወጣው መግለጫው ላይ የወቀሰው፡፡ በትግራይ ክልል ውጊያ በሚካሄድበት ወቅት ያደርጉ ከነበረው ጠንካራ ግፊት በተቃራኒ በአማራ ክልል ለተፈጠረው ችግር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዝምታን መርጧል በማለትም ይተቻል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትን ተጠያቂ ለማድረግ ቸልተኛ ከሆኑት ከምዕራባዊያኑ በተጨማሪ፣ እንደ የተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ፣ ቱርክ፣ ቻይናና ኢራን ያሉ አገሮች ድሮንና መሣሪያ ለኢትዮጵያ መንግሥት በማቅረብ ለሰብዓዊ መብት ጥሰቱ መባባስ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ሲልም ይኮንናል፡፡ ይህ ሁሉ ሳያንስ እንደ አይኤምኤፍ ያሉና ሌሎች ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ምንጮች ለኢትዮጵያ መንግሥት ዕርዳታና ብድር በማቅረብ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹ እንዲቀጥሉ የሚደግፍ ሥራ ሠርተዋል በማለትም ይወቅሳል፡፡

የአማራ ማኅበር በአሜሪካ በአዲሱ ሪፖርቱ ባለፈው አንድ ዓመት በአማራ ክልል በቀጠለው ጦርነት፣ እንዲሁም በተለያዩ ክልሎች በተፈጸሙ አማራውን ዒላማ ባደረጉ ጥቃቶች በ200 አጋጣሚዎች ላይ የንፁኃን ዜጎች ሞትና አካል ጉዳት መድረሱን እንደመዘገበ ይገልጻል፡፡ በዋናነትም እነዚህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መከላከያን ጨምሮ በኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች፣ በኦነግ ሸኔና በሕወሓት ታጣቂዎች መፈጸማቸውን ያስረዳል፡፡ የታገቱ፣ የታሰሩ፣ የአስገድዶ መድፈር ሰለባ የሆኑ፣ የተገደሉ፣ የቆሰሉ፣ የድሮን ጥቃት ሰለባ የሆኑ በሚል ዝርዝር፣ እንዲሁም በ16 ዞኖች የደረሱ ያላቸውን የሰብዓዊ መብት ጉዳቶችን፣ ከነተጎጂዎቹ ስምና ማንነት፣ እንዲሁም ፎቶግራፎች ጋር አስደግፎ በዝርዝር ሪፖርቱ አውጥቶታል፡፡

በአንድ ዓመት ወደ 3,286 ንፁኃን አማራዎች የጉዳት ሰለባ ሆነዋል የሚለው ሪፖርቱ፣ ከእነዚህ መካከል ደግሞ 2,592 ለሞት መዳረጋቸውንና 691 መቁሰላቸውን ይጠቅሳል፡፡ ወደ 53 ጊዜያት በተለያዩ 16 ዞኖች ውስጥ የድሮን ጥቃት መፈጸሙን የሚጠቁመው ሪፖርቱ፣ በዚህም 433 ሰዎች ተገድለው 118 ቆስለዋል ይላል፡፡ ወደ 269 ሰዎች ላይ የአስገድዶ መድፈርና ፆታዊ ወንጀሎች እንደተፈጸሙ ማረጋገጡንም በስምና በቦታ እየዘረዘረ ያቀርባል፡፡ በአማራ ክልል በአጠቃላይ 4,178 ትምህርት ቤቶች ወድመዋል የሚለው ሪፖርቱ በዚህና በቀጠለው ግጭት የተነሳ ወደ 4.1 ሚሊዮን ታዳጊ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ መነጠላቸውን ይጠቁማል፡፡ ሪፖርቱ በአማራ ክልል የቀጠለው ጦርነት የጤናና የተለያዩ መሠረተ ልማት አገልግሎቶችን እንዳቃወሰ ይዘረዝራል፡፡

አማራ ከጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዴሞክራሲ ዕጦት የተነሳ ልክ እንደ ሌላው ማኅበረሰብ ሲበደልና ሲጨቆን መኖሩን ሪፖርቱ ይተርካል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1968 በጎጃም የተካሄደው የገበሬዎች አመፅ የአማራ ክልል በቀደሙ ሥርዓቶች ሲበደል መኖሩ የወለደው መሆኑን በመጠቆም፣ በኢትዮጵያ እኩልነት የሰፈነበት የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲሰፍን በርካታ የአማራ ተወላጆች ሲታገሉና መስዋዕት ሲከፍሉ እንደነበር ይጠቁማል፡፡ ይሁን እንጂ የኢሕአዴግ መንግሥት ከተተከለ ጀምሮ ባለፉት 30 ዓመታት፣ እንዲሁም አሁንም ባለው አስተዳደር ወቅት የአማራ ማኅበረሰብ በቀደሙ ሥርዓቶች የተሻለ ተጠቃሚና ጨቋን ነው የሚል ፍረጃ መቀጠሉን ይገልጻል፡፡ ይህ የተዛባና ለረዥም ጊዜ የቀጠለ አማራውን እንደ ማኅበረሰብ የመፈረጅ አካሄድ ደግሞ ማኅበረሰቡ በአገሩ በሰላም እንዳይኖርና ለጥቃት እንዲጋለጥ አድርጎታል ሲል ይገልጻል፡፡

ሪፖርቱ በማጠቃለያው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምዕራባዊያኑን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች አማራውን ዒላማ እንዲሆን የሚገፋፉ የተዛቡ አመለካከቶች በኢትዮጵያ መኖራቸውን በመረዳት፣ አማራን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶችን እንዲያስቆሙ ይጠይቃል፡፡ በክልሉ ለቀጠለው ጦርነትም ሰላማዊ መፍትሔ እንዲያፈላልጉና ቀውሱን በአስቸኳይ ለማስቆም እንዲሠሩ ምክረ ሐሳብ አቅርቧል፡፡