Ethiopian Reporter - ሪፖርተር


የኮሌራ ወረርሽኝ የተከሰተበት የወልዲያ ከተማ ከፊል ገጽታ

ማኅበራዊ በወልዲያ ከተማ በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ የአንድ ሰው ሕይወት ሲያልፍ 85 ሰዎች መታመማቸው…

አበበ ፍቅር

ቀን: September 18, 2024

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በወልዲያ ከተማ በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ፣ እስከ ማክሰኞ መስከረም 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ የአንድ ሰው ሕይወት ሲያልፍ፣ በወረርሽኙ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 85 መድረሱ ተገለጸ፡፡

ወረርሽኙ ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም. በእቴጌ ጣይቱ ብጡል ክፍለ ከተማ አድማስ ባሻገር ተክለ ሃይማኖት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በወቅቱ በነበረ የፀበል ርጭት መከሰቱን፣ የወልዲያ ከተማ ጤና መምርያ ሜዲካል ኦፊሰር ሲስተር ዘሬ በቀለ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የሁለት ሰዎችን ናሙና ወደ ደሴ ሆስፒታል ላቦራቶሪ በመላክ ወረርሽኙ መከሰቱ ተረጋግጧል ያሉት ሲስተር ዘሬ፣ ሁለቱ ሰዎች በበሽታው ተጠቅተው እንደነበር አክለዋል፡፡

ወረርሽኙ በፍጥነት በመዛመቱ 85 ሰዎች ታመው በሦስት ጤና ተቋማት ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከታማሚዎቹ መካከል 11 ያህሉ በፅኑ መታከሚያ ከፍተኛ ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ሲስተር ዘሬ አክለዋል፡፡

በወልዲያ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሕክምናው እየተሰጠ ነው ያሉት ኦፊሰሯ፣ በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በተቋቋመ ጊዜያዊ ማቆያና በከተማዋ በሚገኙ ሁለት ጤና ጣቢያዎች ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሕክምና መስጫዎች የመድኃኒት፣ የአልጋና የብርድ ልብስ እጥረት እንዳለ የተናገሩት ሲስተር ዘሬ፣ በሚመለከተው አካል ርብርብ እንዲደረጉ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ወረርሽኙ በአጭር ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ በመሠራጨት ላይ ነው ያሉት ኦፊሰሯ፣ በከተማዋ በተሽከርካሪ በመንቀሳቀስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ቅስቀሳ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ወደ አጎራባች ወረዳዎች የመስፋፋት ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ያሉት ሲስተር ዘሬ፣ የጤና ተቋማትም ከወዲሁ ዝግጁ ሆነው ቅድመ ምርመራና ክትትል ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡