ዜና
ቦሮ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሽናሻ ብሔረሰብ ጥያቄ ለ15 ዓመታት ታፍኗል…

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: September 18, 2024

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት ለቦሮ-ሽናሻ ሕዝብ የዘመን መለወጫ ማክበሪያ ቦታ እንዲሰጥ ለ15 ዓመታት የቀረበውን ጥያቄ አፍኖ መያዙን፣ የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አስታወቀ፡፡

በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ፓርቲው ማክሰኞ መስከረም 7 ቀን 2017 ዓ.ም. በወቅታዊ ጉዳዮች በሰጠው መግለጫ፣ በአባላቱና በደጋፊዎቹ ላይ በሕገወጥ መንገድ ከሥራ ማዘዋወርና ማዋከብን ጨምሮ በርካታ የሕግ ጥሰቶችን እየፈጸመባቸው ነው ብሏል፡፡

ፓርቲው ‹‹ጋሪ ዎሮ›› የተሰኘውን የዘመን መለወጫ በዓል የቦሮ-ሽናሻ ሕዝብ በድምቀትና በሚገባው ደረጃ ለማክበር በአዲስ አበባ፣ በክልሉ ዋና ከተማ አሶሳና እና በዞን ከተማዋ ግልገል በለስ የክልሉን መንግሥት ሲጠይቅ መቆየቱን አስታውቋል፡፡  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙ ብሔረሰቦች ውስጥ በርታ፣ ጉምዝ፣ ሽናሻ፣ ማኦና ኮሞ በባለቤትነት ይጠቃሳሉ፡፡

ይሁን እንጂ የክልሉ መንግሥት በክልሉና በዞን ደረጃ የጋሪ ዎሮ በዓልን ማክበሪያና የብሔረሰቡ ቋሚ የባህል ማዕከል ለመገንባት የሚያስችል ቦታ እንዲሰጥ በተደጋጋሚ ቢጠየቅም፣ ምላሽ አልሰጠም ብሏል፡፡ በዚህም ምክንያት የቦሮ -ሽናሻ ሕዝብ ባህሉን የማልማትና የማሳደግ ሕገ መንግሥታዊ መብቱ ጥያቄ ውስጥ ወድቋል ሲል ፓርቲው ቅሬታውን አቅርቧል፡፡  

ድርጊቱን በአገሪቱ ሕገ መንግሥትና በተሻሻለው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሕገ መንግሥት የተሰጠውን ብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋቸውን የመናገር፣ የመጻፍ፣ የማሳደግና ባህላቸውን የመግለጽ፣ የማዳበርና የማስፋፋት፣ እንዲሁም የመንከባከብ መብት የሚጋፋ ነው ሲል ገልጾታል፡፡

ማኅበረሰቡ ባህሉን እንዲያሳድግ በሕገ መንግሥቱ የተጎናፀፈውን መብት እንዳይጠቀም፣ የክልሉ መንግሥት በአሶሳና በግልገል በለስ ከተሞች የጋሪ ዎሮ በዓል ማክበሪያና የባህል ማዕከል መገንቢያ ቦታ እንደከለከለም ፓርቲው በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት 15 ዓመታት ለክልሉ መንግሥት በተደጋጋሚ የቀረበ ቢሆንም ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሊሆን እንዳልቻለ የገለጸው ፓርቲው፣ ለበዓሉ ማክበሪያና የባህል ማዕከል መገንቢያ ቦታ ጥያቄ በአስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ ሲልም ጠይቋል፡፡

በክልሉ ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በተካሄደው 6ኛ ዙር ቀሪና ድጋሚ ምርጫ ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አንድ የክልል ምክር ቤትና አንድ የፓርላማ መቀመጫ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ፓርቲው በመግለጫው የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ከወምበራ፣ ከድባጤና ከቡለን ወረዳዎች ከተውጣጡ የኅብረተሰብ ተወካዮች ጋር በቡለን ከተማ  ባደረጉት ስብሰባ ለምን ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን ዕጩዎችን መረጣችሁ በማለት ሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ዛቻ፣ ማስፈራሪያና ስድብ መሰንዘራቸውን አስታውቋል፡፡

‹‹የመንግሥት ሰዎች የሕዝብ ድምፅ ያገኙ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን በእስር ቤት እናጉራችዋለን በማለት ፍፁም አምባገነናዊና ኋላቀር አቋማቸውን በግልጽ በሕዝብ መድረክ ላይ አራምደዋል፤›› ብሏል፡፡ ‹‹ይህ ለሕዝብ ድምፅ ክብር አለመስጠት ፀረ ዴሞክራሲያዊና አምባገነናዊ አሳፋሪ ተግባር በመሆኑ የፌደራል መንግሥት፣  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ድርጊቱን እንዲያጣሩ፤›› ሲልም ጠይቋል፡፡ የክልሉ መንግሥትም ሕዝቡን በአስቸኳይ ይቅርታ እንዲጠይቅ ጥሪ አድርጓል፡፡

የፓርቲው ዕጩዎች ለክልልና ለፌዴራል ምክር ቤቶች በተወዳደሩባቸው ሁሉም የምርጫ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ የድርጅቱ አባላት፣ ደጋፊዎችና አመራሮች ላይ የተቀናጀ ወከባ፣ እስራት፣ ድብደባ፣ ሕገወጥ የሥራ ዝውውር፣ መብትና ጥቅም መንፈግ፣ በአጠቃላይ የፖለቲካ አመለካከትን መሠረት ያደረገ ጫናዎች በገዥው ፓርቲ አመራሮች ዘንድ እየተፈጸሙ ናቸው በማለት አስታውቋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ይህንን ድርጊት የሚፈጽሙና የሚያስፈጽሙ የዞንና ወረዳ አመራሮች ላይ የዕርምት ዕርምጃ  እንዲወስድ ፓርቲው ያሳሰበ ሲሆን፣ ድርጊቱ የማይታረም ከሆነ ከክልሉ መንግሥት ጋር የጀመረውን አብሮ የመሥራት ስምምነት እንደገና ለማጤን እንደሚገደድ አስታውቋል፡፡