በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም. የተመዘገበው የስደተኞች ቁጥር በ30 በመቶ ጨምሯል ተብሏል

ማኅበራዊ ሳዑዲን ጨምሮ ወደ ኬንያና ጂቡቲ የሚሻገሩ ዜጎች ቁጥር መጨመሩን የዓለም አቀፍ ፍልሰተኞች…

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: September 18, 2024

የኢትዮጵያን አዋሳኝ አገሮች ድንበሮችን በማቋረጥ በተለይም ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኬንያና ጂቡቲ የሚሰደዱ ዜጎች ቁጥር መጨመሩን የዓለም አቀፍ ፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) አስታወቀ፡፡

አይኦኤም ሰኞ መስከረም 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም. ብቻ 42,688 የሰዎች ዝውውር ሲመዘገብ በሰኔ ወር ከነበረው 31,700 የሰዎች እንቅስቃሴ ጋር ሲነፃፀር በ30 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

በሐምሌ ወር በነበረው የሰዎች ዝውውር 58.9 በመቶ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ መሆናቸውን፣ 41 በመቶ ደግሞ ከኢትዮጵያ በስደት መውጣታቸውን፣ በዚህ መረጃ መሠረት ወደ አገር ውስጥ የገባው የስደተኞች ቁጥር በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ መጨመሩ በሪፖርቱ ተብራርቷል፡፡

ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ የሚሰደዱ ዜጎች ከሚጠቀሟቸው የመውጫ በሮች መካከል ጋላፊ፣ ደወሌና ቶጎ ጫሌ ድንበሮች 72 በመቶ ስደተኞችን እንደሚያስተናግዱ የተገለጸ ሲሆን፣ የሞያሌና የኩርሙክ ድንበሮች ቀሪውን ድርሻ በመያዝ እንደ መውጫ በርነት እያገለግሉ ነው ተብሏል፡፡

 በከፍተኛ ደረጃ ኢትዮጵያዊያንን ለስደት እየዳረጉ ናቸው ከተባሉት ዋነኛ ምክንያቶች መካከል በምግብ ራሰን አለመቻልና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ትልቁን መጠን ሲይዝ፣ ግጭት፣ የቤተሰብ ችግርና የተፈጥሮ አደጋዎች ቀሪውን ድርሻ እንደሚይዙ ተገልጿል፡፡ ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ስደተኞች በአመዛኙ በግጭት ምክንያት ነው ተብሏል፡፡

ወደ ውጭ ከሚሰደዱ ዜጎች ውስጥ 66 በመቶ ወንዶች ሲሆኑ፣ 33.5 በመቶ ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን ተጠቁሟል፡፡ ኢትዮጵያውያን እየተሰደዱባቸው ካሉ አገሮች ሳዑዲ ዓረቢያ 52.9 በመቶ፣ ኬንያ 16.8 በመቶ፣ ጂቡቲ 10.8 በመቶ፣ ሶማሊያ 5.1 በመቶ፣ ደቡብ አፍሪካ 4 በመቶ፣ የመን 3.6 በመቶና ሌሎች አገሮች 7.3 በመቶ መሆናቸውን ድርጅቱ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡

በሐምሌ 2015 ዓ.ም. ብቻ ከኢትዮጵያ ወደ ሌላ አገር ከተሰደዱት 25,123 ዜጎች መካከል 13,291 ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ 4,211 ወደ ኬንያ፣ 1,289 ወደ ጂቡቲ፣ 1,000 ወደ ሶማሊያ፣ እንዲሁም 914 ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደሆነ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

በግጭት ምክንያት ከሌሎች አገሮች ወደ ኢትዮጵያ ከገቡት 17,565 ስደተኞች ደግሞ 12,100 ከሱዳን 2,527 ከኬንያ፣ 1,893 ከጂቡቲ፣ 840 ከሶማሊያ፣ 205 ከየመን፣ ከኡጋንዳ፣ ከታንዛኒያ፣ ከኖርዌይና ከሳዑዲ ዓረቢያ የተነሱ ናቸው ተብሏል፡፡

የየመንን ድንበር አቋርጠው ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ጉዞ ከሚያደርጉ የተለያዩ አገሮች ዜጎች ውስጥ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን አይኦኤም አስታውቋል፡፡ ባለፉት ጥቂት ወራት ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ስደተኞች ውስጥ የኤርትራ ስደተኞች የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው ስለመግባታቸው በሪፖርቱ አልተጠቀሰም፡፡

በሰኔ 2015 ዓ.ም. 31 ሺሕ ዜጎች በስደት ድንበር ተሻግረው መውጣታቸው የተጠቀሰ ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ በነበረው የሰዎች ዝውውር ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኬንያ፣ ጂቡቲና ሶማሊያ ከፍተኛ መዳረሻ ናቸው ተብሏል፡፡