ናርዶስ ዮሴፍ

September 18, 2024

የኔዘርላንድስ ኩባንያ ዝቋላ ሆርቲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ውት ቫን ኮፐን

ዝቋላ ሆርቲ የተባለ በአውሮፓ ከሚገኙ ግዙፍ የአበባ አቅራቢ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ኢኤሜስ የተሰኘ የኔዘርላንድስ ኩባንያ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ አዲስ ተግባራዊ ያደረገው የአረንጓዴ አፀድ (Green House) ቴክኖሎጂ ግብፅ፣ ሞሮኮና ስፔን በተለይም በአውሮፓ የኢንጆሪ አቅርቦት ካላቸው የገበያ ድርሻ ገፍቶ ማስወጣት የሚያስችለው እንደሆነ ይፋ አደረገ።

በኦሮሚያ ክልል ሞጆ ከተማ ቢቃ ቀበሌ በሚገኝ 37 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ የአበባና ፍራፍሬ በማምረት በዋናነት ለውጭ ገበያ የሚያቀርበው ኩባንያው በአጠቃላይ 27 ሔክታር መሬት በብቸኝነት ኢንጆሪ የሚያመርትበት እንደሆነ፣ የአሠራር ዘዴውን ከቴክኖሎጂው ጋር ለማስተሳሰር በአንድ ካሬ ሜትር 30 ዩሮ ኢንቨስትመንት ፈሰስ ማድረጉም ታውቋል።

በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ በእርሻ መሬት ላይ ብቻ ተወስኖ የቆየውንና የግብፅና የሞሮኮ ኩባንያዎች እንደሌላቸው የተገለጸውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም፣ በዓመት በሁሉም ወራት በአንድ ካሬ ሜትር እስከ 12 ኪሎ የኢንጆሪ ምርት የሚያስገኝ እንደሆነም ተገልጿል።

የኢንጆሪ ምርት ከፍተኛ ፍላጎት በሚኖርበት ወቅት ከሚደረጉ በረራዎች ውጪ በአሁኑ ወቅት ኩባንያው ወደ 21 የአውሮፓ፣ የመካከለኛው ምሥራቅና የሩቅ ምሥራቅ አገሮች ምርቶቹን የሚያከፋፍል መሆኑን የዝቋላ ሆርቲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ውት ቫን ኮፐን ገልጸዋል፡፡ ልማዳዊው በእርሻ ማሳ ላይ ብቻ የተወሰነው የምርት ዘዴ ለኩባንያቸው ጠቃሚ የማይሆንበት ቀዳሚ ምክንያት፣ በክረምት ወቅት ከሚገናኝ ዝናብ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ እንደሆነ አስታውቀዋል።

ኩባንያው የቴክኖሎጂውን ትግበራ በይፋ ባስተዋወቀበት ማክሰኞ መስከረም 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ለኢንዱስትሪ ባለድርሻ አካላት በተደረገ የጉብኝት መርሐ ግብር እንደገለጹት፣ ልማዳዊው የእርሻ ማሳ ምርት ሥልት የክረምት ወቅት እንደተጠናቀቀ ምርቱን መሰብሰብ የሚያስችል ቢሆንም በአውሮፓ በሚኖራቸው የገበያ ድርሻ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ‹‹በክረምት ወቅት የተመረተውን ምርት መሰብሰብና ማቅረብ የምንችለው በጥር ወር ነው። ይህንን ደግሞ ልናቀርብ የምንችለው ከፍተኛ የፍላጎት ጣሪያ ላይ የሚደርሰው የአውሮፓ ገበያ ነው። ለእኛ በዚያን ወቅት ምርቱን የማቅረብ ችግር የለብንም። ነገር ግን ግብፅ፣ ሞሮኮና ስፔን በዓለም ከፍተኛ ኢንጆሪ አምራቾች ከሚባሉት አገሮች ቀደምት ተጠቃሾቹ ናቸው። ሦስቱም ከእኛ እኩል ለአውሮፓ ገበያ ሲያቀርቡ የምርቱ መሸጫ ዋጋ ይወርዳል፤›› ብለዋል።

በተለይም ሦስቱ አገሮች ለአውሮፓ ቅርብ ሥፍራ ላይ ስለሚገኙ በኢትዮጵያ የሚገኘው ኩባንያ ምርቶቹን በአየር ትራንስፖርት ማድረስ ሲኖርበት፣ የአገሮቹ አቅራቢዎች ግን በመኪናም ሊያደርሱ ስለሚችሉ የምርቶቻቸውን የመሸጫ ዋጋ በተነፃፃሪ ዝቅ እንደሚያደርገው በማብራራት፣ ‹‹ይህም ልንፋለመው የተዘጋጀንበት የገበያ ውጊያ መድረክ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከታወቁት አቅራቢ አገሮች አልፎ ለምን የኢትዮጵያ ኢንጆሪ በገበያው ሊፈለግ ይችላል? ምን የተለየ ነገር አለው? በማለት ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹የግብፅና የሞሮኮ ኩባንያዎች ከኅዳር ወር መጨረሻ ጀምሮ እስከ መጋቢት ድረስ የእርሻና የምርት ጊዜያቸው ነው፡፡ እነሱም ምርት ላይ በሚሆኑበት ጊዜ እኛ ያለ ውድድር ሥጋት ገበያውን ልንይዘው እንችላለን፡፡ በተመሳሳይ ወቅት ኢትዮጵያ የኢንጆሪ አምራች አገር በሚል ባትታወቅም፣ የእኛ ኩባንያ ግን በአውሮፓ ታዋቂ ነው። እናም ተጠቃሚዎች ግብፅን ቢያቋትም ምርቷ ግን የእኛን ያህል ጣፋጭነት እንደሌለው ያውቃሉ። ስለዚህ የጥራት ደረጃችንን ከፍ ስናደርግ ሰዎች ከፍ ያለ ዋጋ ለማቅረብ ፈቃደኛ ናቸው፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

አዲስ ተግባራዊ የተደረገው ቴክኖሎጂ በሁሉም ወራት ምርት ለገበያ ማድረስ የሚያስችል መሆኑ፣ ኩባንያው በዓለም ላይ የተለያዩ የገበያ መዳረሻዎችን ዒላማ ማድረግ የሚያስችለው እንደሆነም ጠቅሰዋል።

በዚህም መሠረት ለአብነት የጠቀሱት በግንቦት ወር እንደ ዱባይና ኳታር ያሉ የመካከለኛ ምሥራቅ አገሮችን ገበያ፣ ከጥር ወር በኋላ ባለው የአውሮፓ ገበያ በሚዘጋበት ወቅት ወደ ደቡብ አፍሪካና የሩቅ ምሥራቅ አገሮች ማዳረስ የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል።

በሌላ በኩል የእርሻ ማሳን መሠረት ያደረገው ምርት ማዳበሪያ ከተረጨ በኋላ ከባድ ዝናብ ካጋጠመ ታጥቦ ሊያድርና ይህም ለብክነት ተጋላጭ እንደሚያደርግ፣ በአዲሱ ቴክኖሎጂ ግን የሚባክን ውኃ እንደማይኖርና በድጋሚ ታክሞ ለኢንጆሪ ልማት እንደሚውል፣ እንዲሁም ፀረ ተባይን ጥቅም ላይ ከማዋል አንፃርም ወጪን መቀነስ የሚያስችል መሆኑ ተጠቅሷል። ሚስተር ኮፐን ‹‹ይህ ለአካባቢውም ሆነ ለኪሳችን አዋጭ ነው›› ብለዋል።

የአውሮፓ ኅብረት በቅርቡ ያፀደቃቸው የፍራፍሬና የአበባ ምርቶችና የአካባቢ ከአካባቢ ጥበቃ ከማረጋገጥ ጋር በተያያዘ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች በአውሮፓ ገበያቸው ላይ ምን ዓይነት ጫና እንደሚያሳደር ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ መሆናችን ጥሩ ነገሩ ወደ 130 መዳረሻዎች ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያለ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ከአየር ትራንስፖርት ካርጎ አያያዝ ጋር በተያያዘ ምርታችንን እንዳናደርስ የምንገደድባቸው የአውሮፓ አገሮች የሚኖሩ ከሆነ፣ እነዚያን ምርቶች ወደ ሌሎች አገሮች እንወስዳቸዋለን፤›› ብለዋል።

የአውሮፓ ኅብረት በቅርቡ ተግባራዊ ያደርገዋል ከተባሉት ፍራፍሬና አትክልትን በአየር ትራንስፖርት ከሚጓጓዝበት መንገዶች ጋር ተያይዞ ያሉ አየር መንገዶች፣ የራሳቸውን ባዮ ነዳጅ እንዲጠቀሙ የሚያዘው መመርያ ኢንጆሪን የሚያካትት መሆኑና አለመሆኑ በግልጽ ባይሰፍርም ሚስተር ኮፐን፣ ‹‹ይህ በእርግጥም ችግር የሚሆን ከሆነ አንዳንድ ነጋዴዎች በዚህ መንገድ የተጓጓዘ ምርት አንፈልግም ካሉ፣ እንዳልኩት ሌሎች ልናዳርሳቸው የምንችላቸው ገበያዎች አሉ። ለምሳሌ ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ ሲንጋፖር፣ ጋቦንና ሲሼልስ ምርቶቻችንን የምናቀርብላቸው ገበያዎች ናቸው፣ ወደ እዚያ እናዞረዋለን። እኛ በቂ ምርት ስላልነበረን ነው እንጂ ገበያው አለ፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

በተያያዘ በሞጆ የሚገኘው የኢንጆሪ ማምረቻ ኩባንያ የተገነባው ደን ተመንጥሮ ባለመሆኑ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ የራሱን የሆነ ባዮ ነዳጅ ለማምረት ስትራቴጂዎችን ቀርፆ እየሠራ ስለሆነ ይህ ስኬታማ ከሆነ የአውሮፓ ኅብረት መመርያ አሳሳቢ እንደማይሆንም ተገልጿል።