በመካከላቸው ልዩነት የተፈጠረው አቶ ጌታቸው ረዳና ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) የጊዜያዊ አስተዳደሩ የካቢኔ አባላት በተዋቀረበት ወቅት

ፖለቲካ

ዮናስ አማረ

September 18, 2024

የትግራይ ክልል ጦርነት በተፋፋመበትና መከላከያ ሠራዊቱ የትግራይ ዋና ዋና ከተሞችን በያዘበት ወቅት፣ ሕወሓት ከእነ ታጣቂዎቹ ወደ በረሃ መግባቱ ይታወሳል፡፡ በዚህ ወቅት የፌደራል መንግሥቱ ሕወሓት ዳግም ተሰብስቦ ጠንካራ የፖለቲካ ኃይል ሊሆን እንደማይችል ይገልጽ ነበር፡፡ ‹‹ሕወሓት የተበተነ ዱቄት ነው›› ይባል በነበረበት በዚያ ወቅት ግን፣ በተምቤን በረሃ ያደባ አንድ ኃይል ዳግም ውጊያ ለመጀመር ይዘጋጅ ነበር፡፡

ከመንግሥትነት ወርዶና ዳግም ወደ ደደቢት በረሃ ገብቶ አማፂ ሽፍታ ሆነ፣ እንዲሁም የተበተነ ዱቄት ሆነ ሲባል የነበረው ሕወሓት የትግራይ ሠራዊት (ቲዲኤፍ) የሚባል ሸማቂ ቡድን ሆኖ ዳግም መምጣቱ ተነገረ፡፡ ከሕወሓት ጋር የተጀመረው ጦርነት ከዚያ ወዲህ የትግራይ ሠራዊት (ቲዲኤፍ) ከሚባለው ኃይል ጋር ወደ መሆን መሸጋገሩ ይነገር ጀመር፡፡

ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔንና ሌተና ጄኔራል ታደሰ ወረደን የመሳሰሉ አንጋፋ የሕወሓት ሰዎች በጊዜው ይሰጡ በነበሩት መግለጫ እንዳብራሩት፣ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይል ያሰባሰበ የትግራይ ‹‹ሴንትራል ኮማንድ›› የሚባል ማዕከላዊ ዕዝ መፈጠሩን ተናግረው ነበር፡፡ ይህንን ዕዝ እንደሚያስተባብሩ በመጠቆም የትግራይ ሠራዊት (ቲዲኤፍ) የሚባለው ኃይልም የዚህ ማዕከላዊ ዕዝ ወታደራዊ ክንፍ መሆኑን አብራርተው ነበር፡፡ ሴንትራል ኮማንዱ በሕወሓት ሊቀመንበር በደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) እንደሚመራ የተነገረ ሲሆን፣ ቲዲኤፍ የተባለውን ኃይል አመራር በመወከል ደግሞ ሁለቱ ጄነራሎች በይፋ እየወጡ መግለጫ ሲሰጡ ይታይ ነበር፡፡

የመጀመሪያው ዙር የትግራይ ክልል ጦርነት ከሕወሓትና ሕወሓት ከሚመራቸው የትግራይ ታጣቂዎች ማለትም ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ጋር የተደረገ መሆኑ በግልጽ ይታወቅ ነበር፡፡ ሕወሓት ከጫካ ወጥቶ ዳግም ትግራይን ለመቆጣጠር ባደረገው ሁለተኛው ዙር የትግራይ ጦርነት ወቅት ግን የትግራይ ሠራዊት (ቲዲኤፍ) የሚባለው ወታደራዊ ክንፍ ስሙ ከፍ ብሎ መነሳት ጀመረ፡፡ ሕወሓት እንደ አማራና አፋር ባሉ አጎራባች ክልሎች ላይ ወረራ በከፈተበትና ጦርነቱ የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎችን ባዳረሰበት ወቅትም እንዲሁ፣ የትግራይ ሠራዊት የሚለው ቡድን ስም ነበር በትግራይ ኃይሎች በኩል በተደጋጋሚ ሲጠራ የነበረው፡፡ ሦስተኛው ዙር ጦርነት ሲካሄድም ቢሆን ቲዲኤፍ ወይም የትግራይ ሠራዊት የሚለው ኃይል ስም ነበር በተደጋጋሚ ስሙ የሚነሳው፡፡

በጦርነቱ መገባደጃ ለፕሪቶሪያው ስምምነት ዝግጅት ሲደረግ ግን የትግራይ ኃይሎችን ወክሎ የሚደራደረው ማን ነው የሚለው ጉዳይ ማነጋገር ጀመረ፡፡ በድርድሩ ዋዜማም ሆነ ማግሥት የፌደራል መንግሥቱ ድርድር የሚያደርገውም ሆነ ያደረገው ከሕወሓት ጋር እንጂ፣ ከሌላ ኃይል ጋር እንዳልሆነ በግልጽ ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ በድርድሩ በተፈረመው የስምምነት ሰነድ ላይም ቢሆን ሕወሓት እንጂ የትግራይ ሠራዊት የሚል ስም አልተጠቀሰም፡፡ ይህ ደግሞ በናይሮቢ ኬንያ በሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች ወታደራዊ አመራሮች በተፈረመው የፕሪቶሪያው ስምምነት ማስፈጸሚያ በሚል በሚገለጸው ሁለተኛ ዙር ስምምነት ላይም በግልጽ የታየ ሲሆን፣ የትግራይ ሠራዊት (ቲዲኤፍ) የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት ተፈራራሚ ቡድን ሆኖ የቀረበበት አጋጣሚ አልነበረም፡፡

የፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነትን ተከትሎ ጊዜያዊ አስተዳደር በትግራይ ክልል ተመሠረተ፡፡ በዚህ ጊዜም ሕወሓትን ጨምሮ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎች የተሰባሰቡበት ጊዜያዊ አስተዳደር መመሥረቱ ነበር የተነገረው፡፡ ይህ ጊዜያዊ አስተዳደርም በፌደራል መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው ደንብ ቁጥር 533/2023 እንደተመሠረተና በዚህ መሠረት እንደሚመራ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ተብሎ የወጣው ይህ ደንብ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በርዕሰ መስተዳደር እንደሚመራ ይጠቅሳል፡፡ ርዕሰ መስተዳድር የሚሆነው ሰው ደግሞ በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚመረጥ ተደንግጓል፡፡

በደንቡ አንቀጽ ሦስት ንዑስ አንቀጽ ሁለት ላይ፣ ‹‹የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድሩ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት በሚደረግ የፖለቲካ ምክክር ተለይቶ፣ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሾማል፤›› ተብሎ ተቀምጧል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ ለአንድ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አግባብ ባላቸው ሕጎች የተሰጡ ሥልጣኖች እንደሚኖሩት የተጠቀሰ ሲሆን፣ የክልሉን ቢሮዎች ማደራጀትና የሥራ ኃላፊዎችን መሾም እንደሚጨምር በደንቡ ተዘርዝሯል፡፡ በርዕሰ መስተዳድሩ የሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደሩ የፕሪቶሪያው ስምምነትን ከፌደራል መንግሥት ጋር በመመካከር እንደሚያስፈጽምም በዚህ ደንብ ተጠቅሷል፡፡ በትግራይ ምርጫ ተካሂዶ መደበኛ አስተዳደር እስኪመሠረት ድረስ ይህ መዋቅር ኃላፊነቱን ይዞ እንደሚቀጥል ነው የተመለከተው፡፡

ይህ ከሆነ እነሆ ሁለት ዓመታት ሊቆጠር በተቃረበበት በአሁኑ ወቅት ግን፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከሕወሓት ጋር ከባድ እሰጥ አገባ ውስጥ ገብቷል፡፡ የጊዜያዊ አስተዳደሩና የሕወሓት ውዝግብ ደግሞ በጊዜያዊ አስተዳደሩ አመሠራረት ሒደትና የሥልጣን ወሰን ላይም ክርክር የፈጠረ ብቻ ሳይሆን፣ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ምንነትና የስምምነቱ አስፈጻሚ ባለቤትነት ላይም ጭቅጭቅ እንዲነሳ ያደረገ ይመስላል፡፡

በሕወሓትና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መካከል ለአንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ሲብላላ የቆየው ውዝግብ ከሥልጣን ፍለጋና የበላይነትን ለመጨበጥ ከሚደረግ ሽኩቻነት ባለፈ የሕወሓት፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩና የትግራይ ሠራዊት (ቲዲኤፍ) የሚባለው ኃይል ተክለ ቁመናና የኃይል አሠላለፍን በተመለከተ ብዙ ጥያቄዎች እንዲነሱ እየጋበዘ ይገኛል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መመሥረትን ተከትሎ የትግራይ ሠራዊት (ቲዲኤፍ) ሲባል የቆየው የታጠቀ ኃይል፣ ወደ ትግራይ ክልል የፀጥታ ኃይልነት መቀየሩ ነው የታወቀው፡፡ በሕወሓትና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መካከል የተካረረ ውዝግብ በቀጠለበት ወቅትም ይኸው የትግራይ ፀጥታ ኃይል የሚባለውና ትጥቅ በእጁ እንዳለ የሚነገረው የትግራይ ሠራዊት (ቲዲኤፍ) ከሁለቱም ወገን ያልወገነ ገለልተኛ አካል መሆኑን ለማሳየት ሲጥር መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በቅርቡ 14ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ በማድረግ ድርጅታዊ ህልውናውን ዳግም ማረጋገጡንና በደብረ ጽዮን (ዶ/ር) የሚመራ ጠንካራ የፓርቲ አመራር መምረጡን የሚናገረው ሕወሓት፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንደማይወክለው እየተነገረ ነው፡፡

ሕወሓት ጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ያሉ አካላት የተፈራረሙት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትም እንደማይወክለውና ስህተት መሆኑን በይፋ እስከ መናገር ሄዷል፡፡ ሕወሓት ከዚህ በተጨማሪም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ በአመራርነት ያሉ ሰዎችን ከፓርቲ አባልነት ማገዱን ይፋ አድርጓል፡፡ ሕወሓት ከዚህ በተጨማሪም ሰኞ መስከረም 6 ቀን 2017 በሰጠው መግለጫ የትግራይ ፀጥታ ኃይል በእነዚህ ሰዎች ላይ ዕርምጃ እንዲወስድ እስከመጠየቅ መድረሱ ታውቋል፡፡

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ብቻ ሳይሆን የፌዴራል መንግሥትና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተቃወሙት የሕወሓት ጉባዔ በሚደረግበት ወቅት፣ የፀጥታ ኃይሉ ሰላማዊ እንቅስቃሴ በትግራይ እንዲኖር ማሳሰቢያዎችን ሲሰጥ ነበር፡፡ በሒደትም ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ፣ ትንኮሳ ላይ መሠረት ያደረጉ፣ ሰላማዊ ሠልፎች፣ ስብሰባዎች፣ መግለጫዎችና ሌሎች የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በክልሉ እንዳይኖሩ ለሁሉም ወገን ሲያሳስብ ነው የታየው፡፡ ቲዲኤፍ የሚባለው የትግራይ ፀጥታ ኃይል ሕወሓትና ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሚጓተቱበት ወቅት ሁሉ፣ አንተም ተው አንተም ተው ዓይነት አቋሞችን ነው በተደጋጋሚ ሲያንፀባርቅ የነበረው፡፡

ይሁን እንጂ አሁን የፀጥታ ኃይል የሚባለው ቲዲኤፍ ከሁለቱም ወገን የሚደረግበት ግፊትና ተፅዕኖ ማየሉ ነው የሚነገረው፡፡ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በቅርቡ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ የሕወሓትና የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፍትጊያ እስከቀጠለ ድረስ የፀጥታ ኃይሉ ገለልተኛ ሆኖ ለመቀጠል እንደሚፈተን ተናግረዋል፡፡ እስከ ዛሬም የፀጥታ ኃይሉ በገለልተኝነት ፀንቶ መቆየቱን ያደነቁት አቶ ጌታቸው፣ የፖለቲካ አመራሮቹ መወዛገብ በቀጠለ ቁጥር ግን የፀጥታ ኃይሉ ሳይነካ የሚቀር ደሴት እንዳልሆነ በማመልከት ችግሩ ወደ ፀጥታ ኃይሉ ሊጋባ ይችላል የሚል ሥጋታቸውን በይፋ ተናግረዋል፡፡

የፀጥታ ኃይሉ (ቲዲኤፍ) እስካሁን በሁለቱ የሕወሓትም ሆነ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ትዕዛዝ ሲሰማራና ተልዕኮ ሲፈጽም አልታየም፡፡ ይሁን እንጂ ሕወሓት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሰዎችን እንዲያስታግስለት ጥሪ ሲያቀርብ ከሰሞኑ ተሰምቷል፡፡ ይህን ጥሪ ተከትሎ የፀጥታ ኃይሉ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ሰዎች ላይ ዕርምጃ ከወሰደ ደግሞ፣ ከፍተኛ ምስቅልቅል ሊፈጠር እንደሚችል እየተሠጋ ነው፡፡

የፀጥታ ኃይሉ በሕወሓት ጥሪ መሠረት ሕወሓትን አይወክሉም፣ እንዲሁም የጊዜያዊ አስተዳደሩን መምራት የለባቸውም በሚል የተጠቀሱ 14 አመራሮችን ከኃላፊነት የሚያነሳና ዕርምጃ የሚወስድባቸው ከሆነ፣ ሕወሓት ሕግ ማስከበር ከሚለው በተቃራኒ እንደ መፈንቅለ መንግሥት ሊቆጠር የሚችልበት ዕድል የሰፋ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡

የፀጥታ ኃይሉ በሕወሓት ጥሪ መሠረት 14ቱን ሰዎች ከሥልጣን ካስወገደ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ መመሥረት ምክንያት የሆኑ ሕጎችና የሰላም ስምምነቱ አደጋ ላይ ይወድቃሉ የሚል ሥጋትም ይነሳል፡፡ የፀጥታ ኃይሉ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ቢያፈርስ በቀጥታ ከፌደራል መንግሥት ጋር ወደ ጦርነት ሊያስገባው ይችላል የሚል ከፍተኛ ሥጋትም ተፈጥሯል፡፡

በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት የፀጥታ ኃይሎ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ወይም ከሕወሓት ለየትኛው ያጋደለ አካሄድ ይከተላል የሚለው ጉዳይ የትግራይ ክልል ፖለቲካን ዕጣ ፈንታ እንደሚወስን ብዙ እየተባለ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ክልሉ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ያለውን ግንኙነት የሚለውጥና የአገሪቱንም ሰላም አደጋ ላይ የሚጥል ችግር ሊፈጥር እንደሚችል እየተገመተ ነው፡፡

ሪፖርተር በቅርቡ በትግራይ ክልል ሦስት የፖለቲካ ኃይሎች መፈጠራቸውን፣ ሕወሓት ለሁለት መከፈሉን ተከትሎ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥና በሕወሓት ጽሕፈት ቤት ውስጥ ያለው የሕወሓት ክንፍ መፈጠሩን በመጥቀስ፣ በዚህ መካከል ደግሞ ቲዲኤፍ (የትግራይ ሠራዊት) የሚባለው የፀጥታ ኃይል መቆሙን በማስታወስ የዚህ ኃይል ሚናና አቋም ምን ሊሆን እንደሚችል ለአንጋፋው የሕወሓት ታጋይ ለአቶ ገብሩ አስራት ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡

አቶ ገብሩ ስለዚሁ ሲያብራሩ፣ ‹‹ቲዲኤፍ የሕወሓት አንድ ክንፍ ነው፣ የተወሰነ የአካሄድ ካልሆነ በስተቀር በርዕዮተ ዓለምም ሆነ በፖለቲካ ተክለ ቁመና ልዩነት የላቸውም፤›› የሚል ድምዳሜ ነበር የሰጡት፡፡

ሁለቱም ልማታዊ ዴሞክራሲ ወይም አብዮታዊ ዴሞክራሲ እንጂ ሌላ ርዕዮተ ዓለም እንደሌላቸው ጠቁመዋል፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ለውጥ እናመጣለን የሚሉ ወጣት ኃይሎችም ቢሆኑ በዚሁ ርዕዮተ ዓለም ተጠርንፋችሁ ሂዱ በሚል የርዕዮተ ዓለም እስረኛ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ገብሩ፣ ይህ ደግሞ በሕወሓት ውስጥ የልዩነት መሠረት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

‹‹ሕወሓት ገንዘብ አለው፣ በስሜት የሚደግፈው ኃይል አለው፡፡ እንዲሁም በርካታ ካድሬ አለው፡፡ ለሕዝብ የሚጠቅም ሐሳብ ሳይሆን እነዚህን ነገሮች ይዞ አምባገነን ሆኖ መቀጠል ይችላል፡፡ ከዚህ ውጪ የሕወሓት የህልውና መሠረት የሆኑ ሌሎች ነጥቦችም አሉ፡፡ ሕወሓት ለ30 ዓመታት በሥልጣን የቆየ ኃይል ነው፡፡ በየቦታው ተጠቃሚ የነበሩ በእርሱ ዕገዛ ሀብት ያፈሩ ባለሀብቶች አሉ፡፡ እነዚህ የሥልጣን መሠረቱ ናቸው፡፡ ሁለተኛው በቲዲኤፍ ውስጥ ያሉ የተወሰኑ ወታደራዊ መኮንኖች በሕወሓት ሀብትና ሥልጣን ያፈሩ አሉ፡፡ የሕወሓት ህልውና ሲነካ የእኛም ህልውና ይነካል ብለው የሚያስቡ ናቸው፡፡

‹‹በማዕድን ዝርፊያ፣ በመሬት ዝርፊያ የተሰማሩ ናቸው፡፡ ሌላው ሕወሓት የካድሬ ድጋፍ አለው፡፡ ሥራ በሙያ፣ በክህሎትና በዕውቀት ይሁን ከተባለ ብዙ ካድሬ ከሥራ ውጪ ስለሚሆን ሕወሓትን ለጥቅም ሲል ይደግፋል፡፡ ሕወሓትን ሊታደገው የሚችለው በውስጡ ይህን መሰል የጥቅም ተጋሪዎች ትስስር መኖሩ ነው፡፡ ያም ቢሆን ግን የተወሰነ ለውጥ ካላመጣ በስተቀር መቀጠል የሚቻልበት ዕድል የጠበበ መሆኑ የገባቸውና ለውጥን የሚያበረታቱ ኃይሎችም አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ውስጥ ከፍተኛ የፖለቲካ ንቃት ተፈጥሯል፡፡ ጥያቄ የሚያነሱ ብዙ ሰዎች ተፈጥረዋል፡፡ ትግራይ ውስጥ ያለው ሁኔታ እየተለወጠ ነው፡፡ ብዙ ተቃዋሚዎች እየተፈጠሩ ነው፡፡ እንደ ድሮው በአንድ አምባገነን ቡድን እየገዛን እንቀጥል የሚለው አካሄድ ላያዋጣ ይችላል፡፡ ይህንን አይተው የተወሰኑ ሰዎች ለውጥ እንዲደረግ እየወተወቱ ናቸው፡፡ ይህን ደግሞ የተወሰነው የማኅበረሰብ ክፍል ሊደግፈው ይችላል፡፡ በምሁራኑም፣ በተቃዋሚውም፣ በማዕከላዊ ኮሚቴው ውስጥ፣ በካድሬው ውስጥ፣ እንዲሁም በቲዲኤፍ መኮንኖች ውስጥ ካለው ኃይል የተወሰነው ወገን ለውጡን ሊደግፈው ይችላል፡፡ የተወሰነው ደግሞ ለውጡ ከመጣ ተጠያቂነት ሊመጣ እንደሚችል በመሥጋት፣ የሀብትና የጥቅም መሠረቱን እንደሚያጣ በመፍራት ብቻ የለውጡን ሐሳብ ሊቃወመው ይችላል፤›› በማለትም አቶ ገብሩ ተናግረዋል፡፡

የትግራይ ፖለቲካ ወዴት እየተለጠጠ እንደሄደ ሲያስረዱም፣ የምሥራቃዊ ኮንጎ ሁኔታን ከክልሉ ጋር ያነፃፅሩታል፡፡ በክልሉ የሚታየው ዘረፋ፣ የፀጥታ ችግሩም ሆነ የፖለቲካ ቀውሱ መሠረታዊ ምንጩ የሕወሓት የፖለቲካ አቅጣጫና አካሄድ ብልሽት መሆኑንም ያነሳሉ፡፡

‹‹ሕወሓት ሁሉን ነገር አፍኖ የሚሄድ ድርጅት ነው፡፡ ይህ ኃይል ሲዳከምና ችግር ውስጥ ሲገባ በትግራይ ውስጥም መቆጣጠሪያ የሌለው የጨነገፈ ሥርዓት (ፌልድ ስቴት) ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ደግሞ ከመንግሥት ውጪ ያሉ ኃይሎች ተፈጠሩ፡፡ ለዚህ ደግሞ ትግራይ በጣም የተመቻቸ ነው፡፡ ብዙ ታጣቂ አለ፡፡ በብዙ ሺሕ የሚቆጠር የቲዲኤፍ ታጣቂ አለ፣ ሚሊሻም አለ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሥራ አጥነቱና ሌላውም ማኅበራዊ ችግር ለዚህ ምቹ ሁኔታ ነው፡፡ በዚህ ጦርነት በተቃራኒው ብዙ ሀብት ያፈሩ አሉ፡፡ ሲነግዱና ሲያተርፉ የነበሩ አሉ፡፡ እነዚህ ኃይሎች ደግሞ ሥርዓት እንዲኖርና ሰላም እንዲፈጠር አይፈልጉም፡፡ እነዚህ እንደ ምሥራቃዊ ዴሞክራቲክ ኮንጎዋ ኪቩ ግዛት ሁሉ ሥርዓት አልበኝነት በትግራይ እንዲፈጠር የሚፈልጉ ናቸው፡፡ በየቦታው በጦር አበጋዞች የሚመሩ ታጣቂዎች እንዲፈለፈሉ ነው የሚፈልጉት፤›› በማለት የተናገሩት አቶ ገብሩ ችግሩ ዘርፈ ብዙ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በእሳቸው እምነት የፀጥታ ኃይሉ ውስጥም ሆነ ሕወሓት ውስጥ ያሉ ኃይሎች ከተጠያቂነት ለማምለጥ ሲሉ፣ ይህን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ቀውስ የበለጠ በማወሳሰብ ሊጠቀሙ ይችላል፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንዳይጠናከር ከማድረግ ጀምሮ በትግራይ ጠንካራ መደበኛ ሥርዓት እንዳይፈጠር እንቅፋት በመሆን ሕወሓት እንደሚንቀሳቀስ ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቲዲኤፍ ወይም የትግራይ ሠራዊት የሚባለውን የፀጥታ ኃይል ከጎኑ ከማሠለፍ ወደ ኋላ እንደማይል ጠቁመዋል፡፡

ፌደራል መንግሥቱም ሆነ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና አልሰጠነውም ያሉትን ምርጫ በትግራይ የጠራው የትግራይ ክልል መንግሥት በዚያ ምርጫም ሕወሓት ማሸነፉንና መንግሥት መመሥረቱን አወጀ፡፡

ይህ በወቅቱ በፌደራል መንግሥቱና በሕወሓት መካከል ተፈጥሮ የቆየውን አለመግባባት የበለጠ ያሰፋ አንድ አጋጣሚ ነበር፡፡ ፌደራል መንግሥቱ በትግራይ የተካሄደው ምርጫ የጨረባ ምርጫ ነው አልቀበለውም እንዳለው ሁሉ፣ ሕወሓት ደግሞ በተቃራኒው መስከረም 30 አልፏልና የፌደራል መንግሥቱ የሥልጣን ጊዜ ገደቡ አብቅቷል፣ እንዲሁም ምርጫ ማራዘም የሚችልበት ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን የለም በሚል ለፌደራል መንግሥቱ ዕውቅና መንፈጉ አይዘነጋም፡፡

በሁለቱ ወገኖች መካከል አንዱ የሌላውን ህልውና መካድና መናቆሩ ተባባሰ፡፡ በዚህ መነሻነት በተፈጠረው የፖለቲካ መካረር የተነሳም አስከፊው ጦርነት ተጀመረ፡፡ ጦርነቱ ለሁለት ዓመታት ከተካሄደና ብዙ ውድመት ካስከተለ በኋላ የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት ተፈረመ፡፡

የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት ከተፈረመ እነሆ በቀጣዩ ጥቅምት ሁለተኛ ዓመቱን ይይዛል፡፡ ይህ ስምምነት በትግራይ ክልል የጥይት ጩኸትን በማስቆም ሰላም እንዲሰፍን ያደረገ በሚል ሲወደስ ቆይቷል፡፡ ስምምነቱን በሚመለከት በመጀመሪያ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ይነሳ የነበረው ክርክር የስምምነቱ አንቀጾች በአግባቡ በተግባር ይተርጎሙ፣ እንዲሁም ስምምነቱ ይከበር በሚሉ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ ነበሩ፡፡ በሒደት ግን የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት በራሱ በሕወሓት መካከል በተፈጠረው መከፋፈል ዓይነተኛ መነሻ ሲሆን ነው የታየው፡፡

አሁን ሕወሓት ፕሪቶሪያ ሄዶ ስምምነቱን የተፈራረመው ቡድን እንደማይወክለው እየተናገረ ነው፡፡ ከዚህ ስምምነት ውስጥ ተኩስ ማቆም ከሚለው አንቀጽ ውጪ ባሉ ጉዳዮች እንደማይስማማም እያስታወቀ ነው፡፡ ሕወሓት ይህን የሚለው በስምምነቱ መሠረት በትግራይ የነበረው መንግሥት ፈርሶ በጊዜያዊ አስተዳደር መተካቱ አግባብ አይደለም በሚል ቅዋሜ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ሕወሓት የጊዜያዊ አስተዳደሩን የሚመሩ ከፍተኛ አመራሮችን አይወክሉኝም ከኃላፊነት አንስቼዋለሁ ማለቱ የሚታወስ ሲሆን፣ አክሎም በፕሪቶሪያው ሰነድ የማይስማማበት አንቀጽ ብዙ እንደሆነ እየገለጸ ነው፡፡ ቲዲኤፍ (የትግራይ ሠራዊት) ትጥቅ ማስፈታት የሚለውንም ሐሳብ እንዳልተቀበለው ነው ሕወሓት የሚናገረው፡፡

ሕወሓት ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር የገባበት እሰጥ አገባ በሒደት የሰላም ስምምነቱን መሠረታዊ ጉዳዮች ጥያቄ ምልክት ውስጥ ወደ መክተት እየተሸጋገረ ይመስላል፡፡ በዚህ መሀል የታጠቀው የቲዲኤፍ ፀጥታ ኃይል ወዴት ያጋደለ አቅጣጫ ይከተላል የሚለው ተጠባቂ ጉዳይ ሆኗል፡፡