ሔለን ተስፋዬ

September 18, 2024

መንግሥት ዋጋ ከፍ አድርጎ በመተመኑ የኢትዮጵያ ሰሊጥ በዓለም የገበያ ገዥ ማጣቱን፣ የጥራጥሬና ቅባት እህል ላኪዎች ተናገሩ፡፡

ከዓለም ገበያ ትልቁ መሆኑ በሚነገርለት የቻይና ገበያ ኢትዮጵያ ከነበራት 50 በመቶ ድርሻ ወደ አምስት በመቶ ዝቅ ማለቱን የወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የጥራጥሬና የቅባት እህል ላኪ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ታንዛኒያ፣ ቶጎና የሌሎች አገሮች ሰሊጥ በቶን እስከ 1,400 ዶላር ሲሸጡ፣ የኢትዮጵያ ግን 1,800 ዶላር በቶን ተመን ወጥቶለት ለገበያ ይቀርባል፡፡

‹‹ይህ የዋጋ ተመን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዳይሆን ያደርጋል፤›› ያሉት ላኪው ላኪዎች፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በጋራ ያቋቋሙት የዋጋ ቦርድ በየ15 ቀናት እንደሚተምኑት ገልጸዋል፡፡

ጉዳዩን ለማስረዳት የተምታታ ችግር መኖሩንና አንዳንድ ነጋዴዎች በዓለም ገበያ ቀጥታ ገዥዎችን ካገኙ በቶን እስከ 2,000 ዶላር እንደሚሸጡ፣ ነገር ግን በደላላ ከሆነ እስከ 1,400 ዶላር እንደሚሸጡ አስረድተዋል፡፡

በአብዛኛው በቀጥታ ዓለም አቀፍ ገዥዎችን ማግኘት እንደሚያስቸግርና አንዳንድ ላኪዎች 2,000 ዶላር በቶን ሲሸጡ፣ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንደሚመዘገብና ያንን እንደ መነሻ በመጠቀም ተመን እንደሚወጣ ተገልጿል፡፡

ምርቱን በቅናሽ የሚያቀርቡ እንደ ቶጎ፣ ታንዛኒያና ናይጄሪያ የመሳሰሉ አገሮች በቻይና ገበያ ከፍተኛ ድርሻ እያገኙ መሆኑንና ኢትዮጵያ ደግሞ በተቃራኒው ድርሻዋ ዝቅ ማለቱን ሌላ ላኪም አስረድተዋል፡፡

የዋጋ አውጪ ቦርዱ በገበያ ላይ ያለውን ችግር የሚያውቅ ቢሆንም፣ ነገር ግን ከላኪዎች አንዳንዶች በቶን 2,000 ዶላር መሸጥ ስለሚችሉ ‹‹አንደር ኢን ቮይስ ልታደርጉ ነው›› በሚል ተመኑን ከፍ እንደሚያደርጉት ተናግረዋል፡፡

በዚህ ምክንያት የጥራጥሬና ቅባት እህል 21 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ምርት በኮንትሮባንድ እየወጣ መሆኑን፣ የዓለም ባንክ ያወጣውን ሪፖርት ዋቢ አድርገው ላኪው አስረድተዋል፡፡

የፀጥታና የኮንትሮባንድ ችግር ምክንያት እንደሆነ ጠቁመው፣ አሁን የተገኘው ውጤት የተመረተውን ስለማያሳይና በኮንትሮባንድ የወጣው ስለማይመዘገብ ነው ብለዋል፡፡

በዓለም ገበያ ኢትዮጵያ ያላት ድርሻ አነሰ ሲባል በኮንትሮባንድ የሚወጣው ምርት ስለማይመዘገብና የሚሰጠው መረጃ ትክክል ባለመሆኑ፣ የዓለም ባንክ በኮንትሮባንድ ከተቀባይ አገሮች በኩል ሆኖ በሠራው ሪፖርት መሠረት 21 በመቶ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች በኮንትሮባንድ እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

ይህም ማለት በኮንትሮባንድ ምክንያት ኢትዮጵያ ማግኘት ያለባትን የውጭ ምንዛሪ እያጣች እንደሆነ፣ በዓለም ገበያ ያላት ድርሻ ዝቅተኛ መሆኑ እንደሚያሳይ፣ እንዲሁም ተመኑ ከፍ ሲደረግባቸው ዝቅ ወዳለው ኮንትሮባንድ የሚመርጡ ነጋዴዎች መኖራቸውን ላኪው አክለዋል፡፡

በፀጥታ ችግር ምክንያት የሁመራን ሰሊጥ ሱዳን ውስጥ የግብፅ ነጋዴዎች በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከሚሸጥበት ከፍ አድርገው ከገበሬዎች እንደሚገዙ፣ ብዙ ምርት በዚህ መንገድ እንደሚወጣ መሰማታቸውን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም በሌሎች ገበያዎች ኢትዮጵያ ያላት ድርሻ ዝቅ እያለ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከፍተኛው የኢትዮጵያ ምርት ገዥ ቻይና እንደሆነች ገልጸዋል፡፡

ህንድ ከቻይና ቀጥላ ከፍተኛ ገዥ መሆኗንና ሰሊጥ ከኢትዮጵያ ከወሰደች በኋላ እሴት ጨምራበት ለሌሎች አገሮች እንደምትሸጥ ገልጸዋል፡፡

የፀጥታ ችግሩ እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያ በሳዑዲ ዓረቢያናበ እስራኤል ያላት የገበያ ድርሻ ዝቅ ማለቱንም ተናግረዋል፡፡