September 18, 2024 – EthiopianReporter.com 

ኢትዮጵያን ለዘመናት እያሰቃዩ ከሚገኙ ችግሮች መካከል የሰላም ዕጦት፣ የምግብ ዋስትና መረጋገጥ አለመቻል፣ በተደጋጋሚ በድርቅ መጠቃት፣ ለሰው ሠራሽና ለተፈጥሮ አደጋዎች በቀላሉ ተጋላጭ መሆንና ከትናንት ስህተቶች አለመማር ዋነኞቹ ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች አሁንም ብሶባቸው እየቀጠሉ ሲሆኑ ለእርማት የሚደረጉ ጥረቶች በጣም አነስተኛ በመሆናቸው፣ በአራቱም ማዕዘናት የሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ በከባድ ሁኔታ ውስጥ እየኖረ ነው፡፡ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የተለያዩ መንግሥታት ቢቀያየሩም አሁንም የኢትዮጵያ ስም ከምፅዋት ጠባቂነት አልተላቀቀም፡፡ ሰላም ማስፈን ባለመቻሉ አሁንም በየቦታው ውጊያዎች ይካሄዳሉ፡፡ በጦርነትና በበሽታ ሰዎች አሁንም ይሞታሉ፡፡ ድርቅ አሁንም አልላቀቅ ያለ አበሳ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የመሬት መንሸራተት አዲስ ክስተት ሆኖ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ የኑሮ ውድነት ከአቅም በላይ ሆኖ መላወስ የማይቻልበት ደረጃ ላይ እየተደረሰ ነው፡፡ የጫናው ብዛት የዜጎችን ሕይወት እያመሰቃቀለ ነው፡፡

መንግሥት በአሁኑ ጊዜ ከኑሮ ውድነት ጀምሮ እስከ ተለያዩ ጉዳዮች ድረስ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎች በቅጡ መገምገም አለበት፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ይፋ ከተደረገ ወዲህ የብር ምንዛሪ ተመን ገበያ መር ሲሆን፣ የመንግሥት አገልግሎቶችን ጨምሮ ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ምርቶች ዋጋቸው እየናረ ነው፡፡ ከዜጎች ገቢ አቅም በላይ የሆኑ የዋጋ ጭማሪዎችና ታክሶች በስፋት እየተስተዋሉ ነው፡፡ መንግሥት ከአይኤምኤፍና ከዓለም ባንክ ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት ብድሮች የሚከፈሉት፣ በተለያዩ አገልግሎቶችና ምርቶች ላይ የተለያዩ ታክሶች ሲጣሉ ስለሆነ ከአቅም በላይ የሆኑ ክስተቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ኢኮኖሚው በሚገባ ተንቀሳቅሶ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በንግድና በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ብድር መክፈልም ሆነ የተሻለ ዕድገት ማስመዝገብ ይቻላል፡፡ ለዓመታት ንቅንቅ ማለት ካልቻለ ኢኮኖሚ የሚገኝ አነስተኛ ገቢ ላይ ርብርብ ሲደረግ ግን ከፍተኛ ችግር ያጋጥማል፡፡

በልቅ የገበያ ሥርዓት የሚመሩት ዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት ደሃ አገሮችን በሚያስቀምጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች በማሰር ያበደሩትን ማስመለስ ስለሚፈልጉ፣ የአገሮቹን ነባራዊ ሁኔታ ከማጤን ይልቅ ዜጎችን በተደራራቢ ታክሶችና ቀረጦች  መላወሻ በማሳጣት ድህነትን ያባብሳሉ፡፡ በተለያዩ አገሮች የተከሰቱ ችግሮችም እውነታውን ማሳያ ናቸው፡፡ ከዚህ በመነሳት መንግሥት አዋጭ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ ሳይረፍድ መንቀሳቀስ አለበት፡፡ ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ ኢንቨስትመንቶችን ማስፋፋት ላይ ከፍተኛ ትኩረት መደረግ ይኖርበታል፡፡ ወጣቶች በስፋት ወደ ሥራ የሚሰማሩባቸው መስኮች መብዛት አለባቸው፡፡ የዜጎችን ገቢ ሊያሳድጉ የሚችሉ የፖሊሲ ማዕቀፎች በስፋት እንዲኖሩ ማስቻል ተገቢ ነው፡፡ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ዝቅተኛ የነፍስ ወከፍ ገቢ ያላቸው ዜጎች በተደራራቢ ታክሶች ኑሮአቸው መቃወስ የለበትም፡፡ ለዚህም ሲባል በጥናት ላይ የተመሠረቱ ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎች ያስፈልጋሉ፡፡

ምግብ ማግኘት አስቸጋሪ በሆነባት ኢትዮጵያ ውስጥ 130 ሚሊዮን ይሆናል ለሚታሰበው ሕዝብ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ ከ130 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ ወጣት መሆኑ በተደጋጋሚ ተሰምቷል፡፡ ሰፊ ለም መሬትና የውኃ ሀብት ባላት አገር ውስጥ በዓመት ቢያንስ ሦስቴ ማምረት ይቻላል፡፡ ቴክኖሎጂውና ግብዓቱ ሲጨመርበት ደግሞ ምርታማነቱ በጣም ይጨምራል፡፡ ግብርናው የእንስሳት ሀብት ልማቱን አካቶ የመስኖ ልማቱ በስፋት ቢሠራበት ከፍተኛ ውጤት ሊመዘገብበት ይችላል፡፡ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም ገበያ መትረፍ አያቅትም፡፡ ከግብርና በተጨማሪ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በማዕድናት፣ በኃይል ማመንጫ፣ የብስን ጨምሮ በአየርና በባቡር ትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች፣ በመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ በቴክኖሎጂና በሌሎች መስኮች ወጣቱን ኃይል በስፋት ማሰማራት ለሚያስችሉ ሥራዎች ቅድሚያ ቢሰጥ እጆች ለምፅዋት መዘርጋታቸው ይቆማል፡፡

የሕግ የበላይነት ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ይሻል፡፡ በተለይ ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዘው የሚነሱ በርካታ ችግሮች ዜጎችን በሚያስመርሩበት አገር ውስጥ፣ በፖለቲካው ምክንያት የሚደርሱ የመብት ጥሰቶች ሲደመሩበት ተስፋ ያጨልማሉ፡፡ ሕግ ይከበር ሲባል መንግሥትን፣ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎችንና በአጠቃላይ ዜጎችን ይመለከታል፡፡ ሕግ የማስከበር ኃላፊነት ያለበት መንግሥት በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ስሙ ሲብጠለጠል ከማንም በላይ ሊያሳስበው ይገባል፡፡ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖ ለልማትና ለዕድገት የሚደረገው ጉዞ አስተማማኝ የሚሆነው ዜጎች በነፃነት ሲኖሩ ብቻ ነው፡፡ በአጠቃላይ የሕግ የበላይነት ነገር ሕክምና ይፈልጋል፡፡ ሕክምናው የሚገኘው ሁሉም ዜጎች በጋራ በሚደርሱበት መግባባት መሆን አለበት፡፡ አገር መልማትም ሆነ ማደግ የምትችለው ልማቱ የጋራ ሲሆን ነው፡፡ የንግግር ነፃነት፣ ሁሉንም የሚያስማማ የፖለቲካ ምኅዳርና የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ዴሞክራሲን ለማስፈን ፍቱን መድኃኒት ናቸው፡፡

የልማት እንቅስቃሴ ዋና ዓላማ የዜጎችን ዕድገትና መሠረታዊ ፍላጎት ማሟላት በመሆኑ፣ ገና ከጥንስሱ የሕዝብ ተሳትፎ ያስፈልገዋል፡፡ አገር ሲያድግና ሲለወጥ ዜጎች የሚከፍሉት መስዋዕትነት አለ፡፡ ይህ መስዋዕትነት የሚከፈለው መንግሥትና ሕዝብ የጋራ ዓላማ ሰንቀው ሲነሱ ብቻ ነው፡፡ ሕዝብን ማዕከል ያደረገ ልማት ተጠቃሚነትንና ዘለቄታዊነትን የሚያካትት በመሆኑ፣ ከሕዝብ ጋር ያስማማል፡፡ የልማቱ አጋር ብቻ ሳይሆን ግንባር ቀደም ተዋናይ እንዲሆን፣ ሕዝብ በመጀመሪያው ረድፍ ላይ መገኘት አለበት፡፡ በአጠቃላይ የአገር ጉዳይ እያንዳንዱን ዜጋ ያገባዋል፡፡ መንግሥትም አሠራሩ ለሕዝብ ግልጽ መሆን አለበት፣ ተጠያቂነቱም እንዲሁ፡፡ የልማቱ ውጤት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የሚዳረሰው የሕዝብ ተሳትፎ ሲጎለብት ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቱ ሲከበር ነው፡፡ የሕግ የበላይነት በተግባር ሲረጋገጥ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ለኢኮኖሚያዊና ለማኅበራዊ ምስቅልቅል የሚዳርጉ ችግሮች ይበዛሉ!