ትራምፕ

ከ 4 ሰአት በፊት

የኢራን መረጃ መንታፊዎች ከዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ዘመቻ አስተባባሪዎች የወሰሰዱትን መረጃ ከባይደን የምርጫ ዘመቻ አስተባባሪዎች ጋር ግንኙነት ላላቸው ሰዎች መላካቸውን ኤፍቢአይ እና የአሜሪካ የደኅንነት ተቋማት ገልጸዋል።

በዚህ ሂደት የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ከእነሱ ፍቃድ ውጪ የኢሜል መልዕክቶችን ከባይደን ጋር ግንኙነት ወዳላቸው ሰዎች ልከዋል። ይህ የሆነው ባለፈው ሐምሌ ወር አካባቢ ሲሆን፣ ይህም ባይደን ከፕሬዝዳንታዊ ውድድር ከመውጣታቸው አስቀድሞ ነበር።

ሆኖም መረጃ መንታፊዎቹ መልዕክቶቹን በኢሜል ከላኩ በኋላ ከተቀባዮቻቸው ምላሽ ስለማግኘታቸው የታወቀ ነገር የለም።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ባለፈው ነሐሴ ወር ላይ ኢራን በመጪው የአሜሪካ ምርጫ ላይ ክፍፍልን ለመፈጠር እንዲሁም ዜጎች በአሜሪካ መንግሥታዊ ተቋማት ላይ ያላቸው እምንት እንዲሸረሸር ለማድረግ እንደምትጥር ሲያስጠነቅቁ ነበር።

ባለሥልጣቱ ኢራን ይህንን ዓላማዋን ለማሳካት እና የዲሞክራቶች እንዲሁም የሪፐብሊካኖች የምርጫ ማስተባባሪያዎችን በቀጥታ ለመበርብር “ማኅበራዊ ምህንድስና” የተባለ እና ሌሎች ስልቶችን ስትጠቀም ነበር ብለዋል። ይህንን ስልት ኢራን እና ሩሲያ በሌሎች አገራት ላይ የሚተገብሩት እንደሆነም አንስተዋል።

የአሜሪካ የፌዴራል የምርመራ ቢሮ ኤፍቢአይ ትላንት ረዕቡ ባሠራጨው መግለጫ “የኢራን መረጃ መንታፊዎች ካለፈው ሰኔ ጀምሮ ከቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጋር የተያያዙ እና ይፋዊ ያልሆኑ የምርጫ ቅስቀሳ መረጃዎችን በአሜሪካ ለሚገኙ መገናኛ ብዙኃን ለመላክ የሚያደረጉትን ጥረት ቀጥለው ነበር” ብለዋል።

በጉዳይ ላይ ከቢቢሲ ጥያቄ የቀረበላቸው የትራምፕ የምርጫ ቅሰቀሳ ቡደን ቃል አቀባይ ካሮሊን ሌቪቲ ኢራን በምርጫ ቅስቀሳው ላይ ጣልቃ ልተገባ እንደሞከረች ገልጸዋል።

ቃል አቀባዩ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከተመለሱ ኢራን ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ወደ ቦታው እንዲመለስ እና እንደሚጠናከር ስለሚያውቁ መረጃ መንታፊዎቹ ባይደን እና ካምላ ሃሪስን ለመርዳት ሞክረዋል ብለዋል።

ጨምረውም ሃሪስ እና ትራምፕ የተላከላቸውን መረጃዎች ምን እንዳደረጉት ሊገልጹ ይገባል ብለዋል።

ትራምፕ በዚህ ጉዳይ ላይ ትላንት በሰጡት አስተያየት “ኢራኖች ሁሉንም መረጃዎች ለባይደን ሰጥተዋል። ምክንያቱም አብረው ስለሚሠሩ” ሲሉ ከሰዋል።

የሃሪሰ የምርጫ አስተባባሪዎች በበኩላቸው እንዲህ ዓይነት መረጃ ስለመላኩ አናውቅም ብለዋል። ሆኖም አንዳንድ ግለሰቦች የተጨበረበረ የሚመስል መልዕክት በግል ኢሜላቸው ደርሷቸዋል ሲሉም ጠቅሰዋል።

ኤፍቢአይ በመግለጫው ምርመራው እና መልዕክቱን ከተቀበሉ ሰዎች ጋር ያለው ግንኙት እንደሚቀጥል ገልጿል።

በመንግሥታቱ ደርጅት የኢራን ቋሚ ተልዕኮ ቃል አቀባይ ለአንድ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ሲናገሩ፣ አገራቸው የአሜሪካ ምርጫ ላይ ጣልቃ የምትገባበት ምክንያትም ሆነ ፍላጎት እደሌላት ገልጸዋል።

ይህ መረጃ የተሰማው የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ ባለፈው እሁድ በጎልፍ መጫዋቻ ክበብ ውስጥ ሳሉ የግድያ ሙከራ ከተቃጣባቸው በኋላ ነው።