‘ዩቱሪ ዋሪሚ’ የኢኳዶራውያን ስብስብ የሆነ የሴቶች ቡድን ነው።
የምስሉ መግለጫ,ኤልሳ ሴድራ

ከ 4 ሰአት በፊት

‘ዩቱሪ ዋሪሚ’ የኢኳዶራውያን ስብስብ የሆነ የሴቶች ቡድን ነው። አማዞን ደንን ለመጠበቅ ነው የተሰባሰቡት።

የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት አካባቢያቸው ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ቆርጠው ተነስተዋል።

ሰሬና የተባለ ማኅበረሰብ አማዛን ደን ውስጥ ይገኛል። ጃቱንያኩ የሚባል ወንዝ ያዋስናቸዋል።

ኤልሳ ሴድራ 43 ዓመቷ ነው። ጉያሱያ የተባለ ቅጠል ታበቅላለች።

በዚህ ቅጠል የሚከወን ባህላዊ ሥነ ሥርዓት በአማዞን ደን ውስጥ ያሉ ቀደምት ማኅበረሰቦች ቀናቸውን የሚጅምሩበት ነው።

ከቀደምት ቤተሰቦቻቸው ጋር የሚተሳሰሩበት መንገድም ነው።

ዕድሜያቸው ከ23 እስከ 85 የሆነ 35 ሴቶች ሥነ ሥርዓቱን ለመታደም ተሰባስበዋል።

ካሮና አንዲ በዕድሜ ትልቋ ናት። አቡዌላ እያሉ ይጠሯታል። አያት እንደማለት ነው።

መድኃኒትነት ባላቸው ቅጠሎች ሥነ ሥርዓቱን ትመራለች።

ወጣቶች ደግሞ ባህላዊ ዳንስ ይደንሳሉ።

ሴርዳ “ጥንካሬ፣ ጥንካሬ” ስትል ሌሎቹ ሴቶች “ጠባቂ፣ ጠባቂ” እያሉ በዜማ ይቀበሏታል።

ጠንካሮቹ ሴቶች

የቡድናቸው ስም ሲተረጎም ‘ጠንካሮቹ ሴቶች’ ማለት ነው።

የአማዞን ደንን ለመጠበቅ ያሰማሩት 154 ጠባቂዎችን ነው። በአካባቢው ያለውን ብክለት መቆጣጠር እንደቻሉ ይናገራሉ።

“ውሃው ንጹህ እንደሆነ አለ። ዓሣ እናሰግራለን” ትላለች አንዲ።

የሰሬና ማኅበረሰብ በአቅራቢያው ሌሎች 50 ቀደምት ማኅበረሰቦች አሉት።

የደን ጭፍጨፋን ጨምሮ የአማዞን ደንን ብዝኃ ሕይወት አደጋ ውስጥ የሚጥሉ ድርጊቶችን በማስቆም ይተባበራሉ።

አንድሪያ ሴማቲጊ፣ በዋሽንግተኑ ዋይትማን ኮሌጅ የፖለቲካ መምህርት እና ተመራማሪ ናት።

“ሥራቸው እምብዛም ዕውቅና ሲሰጠው ባይታይም፤ እንደዚህ ዓይነት ቡድኖች የአካባቢ ጥበቃ ትግሉን ይመራሉ” ትላለች።

የቡድኑ መሪ ሴርዳ እንደምትለው እነዚህ ሴቶች ለረዥም ጊዜ የአካባቢ ጥበቃ ትግልን በግንባር ቀደምነት መርተዋል።

ዕውቅና ሊሰጣቸው እንደሚገባም ታክላለች።

“ብርታትን፣ ቆራጥነትን በአማዞን ደን ውስጥ ይወክላሉ” ስትል ትገልጸዋለች።

በ2020 (እአአ) 35 የአካባቢው ነዋሪዎች መሬታቸው እና ወንዛቸውን ለመጠበቅ ተሰባሰቡ።

በየሳምንቱ እየተገናኙ ልምድ ይለዋወጡ ጀመር።

ሮዙያ አልቬርዶ የተባለችው የቡድኑ አባል እንደምትለው፣ በትውልዶች የተላለፈላቸውን ወንዝ መጠበቅ የጋራ ኃላፊነታቸው ነው።

“ለቀደምት ማኅበረሰቦች ተፈጥሮ መተሳሰሪያ ገመዳችን ነው። አንድ ነን። ተፈጥሮን መጉዳት ራሳችንን መጉዳት ነው” ትላለች።

በአካባቢው የሚኖሩ ወንዶች መጀመሪያ ላይ ንቅናቄውን ቢነቅፉም አሁን ደጋፊ ሆነዋል።

‘ዩቱሪ ዋሪሚ’ የኢኳዶራውያን ስብስብ የሆነ የሴቶች ቡድን ነው

አደጋ ውስጥ የወደቀው አማዞን

ዘጠኝ የደቡብ አሜሪካ አገራትን የሚያካልለው አማዞን አደጋ ውስጥ ወድቋል።

2.5 ሚሊዮን ስኩዌር ማይል የሚሸፍነውን ደን ለመጠበቅ የቀደምት ማኅበረሰቦች ሴቶች ንቅናቄ እያደረጉ ነው።

ኢኳዶር ውስጥ የሚገኘው የአማዞን ክፍል በኢንዱስትሪዎች መስፋፋት አደጋ ውስጥ ወድቋል።

የደን ጭፍጨፋ፣ የማዕድን ቁፋሮ እና ሌሎችም አደጋዎች ተጋርጠውበታል።

በተለይም ናፖ የተባለው ግዛት ተጋላጭ ሆኗል።

ከ2015 እስከ 2021 ባሉት ጊዜያት የማዕድን ቁፋሮ ያደረሰውን ጉዳት የሳተላይት ምሥል ያሳያል።

የማዕድን ቁፋሮ 21.7 ስኩዌር ማይል ያህል ተስፋፍቷል። ይህም የ316 በመቶ ጭማሪ ነው።

በናፖ ለአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም ሰብአዊ መብት የሚታገሉ ቡድኖች ይህንን ይነቅፋሉ።

የማዕድን ቁፋሮ የሚያስገኘው ገንዘብ በአካባቢው ካለው የምጣኔ ሀብት ውስንነት አንጻር ከፍተኛ የሚባል ነው።

በ2019 የኢኳዶር መንግሥት ማንኛውም ከነዳጅ ቁፋሮ ጋር የተያያዘ ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት ቀደምት ማኅበረሰቦች አስተያየታቸው እንዲካተት ውሳኔ አስተላልፏል።

ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት 60 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ የነዳጅ ቁፋሮን ተቃውሞ ድምጽ ሰጥቷል። ይህ በያሱኒ ብሔራዊ ፓርክ ቢተገበርም በሌሎች አካባቢዎች ግን አሁንም የነዳጅ ቁፋሮ እንደቀጠለ ነው።

መንግሥት ለ153 ድርጅቶች ፈቃድ ሰጥቷል።

ሕጋዊም ይሁን ሕገ ወጥ የማዕድን ቁፋሮ አካባቢ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።

በስፔን፣ በሜክሲኮ እና በኢኳዶር ዩኒቨርስቲዎች በ2022 የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው፣ በናፖ ወንዝ የመርዛማ ብረት ቅሪት ተገኝቷል።

ይህም ከወርቅ ቁፋሮ ሥራ ጋር የተያያዘ ነው።

በዚህ ምክንያት የካንሰር ተጋላጭነት እና ሞት ከፍ እንዳለ ጥናቱ ያመለክታል።

የሴቶቹ ቡድን ገቢ የሚያገኙበት የተለያዩ የዕደ ጥበብ ውጤቶችን ያመርታሉ
የምስሉ መግለጫ,የሴቶቹ ቡድን ገቢ የሚያገኙበት የተለያዩ የዕደ ጥበብ ውጤቶችን ያመርታሉ

በ2021 የውሃ ናሙና ተሰብስቦ የተሰሠራው ጥናት በናፖ ወንዝ የላይኛው ክፍል ብረት መገኘቱን ያሳያል። በአካባቢው ነዋሪዎች እንዲሁም ዓሣዎች ላይም ተጽዕኖ ማሳደሩን ቀጥሏል።

የውሃ ሃብት ባለሙያ የሆነው ሮድሪጎ ኤስፒኖሳ “በአንድ ወቅት ኩልል ያሉ የነበሩት ወንዞች አሁን ተመርዘዋል” ይላል።

የውሃውን ቀለም በማየት ብቻ የማዕድን ቁፋሮ በአካባቢው እንዳለ ማወቅ እንደሚቻል ይናገራል።

“እነዚህ ብረቶች ከባቢ አየር ውስጥ ሲበተኑ በአፍ እና በአፍንጫ ይገባሉ። ቆዳ ላይ የሚወጣ ቁስለት አንዱ ምልክት ነው” ይላል።

የቀደምት ማኅበረሰብ ሴቶች ይህን ለመከላከል ጥበቃ ያደርጋሉ።

ከሁለት እስከ ሦስት ቀናት ደኑን እየዞሩ ይጠብቃሉ። ማንኛውም የማዕድን ቁፋሮ ምልክት ወይም የተፈጥሮ ሀብት ጉዳትን ካዩ አያልፉም።

እያንዳንዱን ነገር ፎቶ ያነሳሉ፤ ቪድዮ ይቀርጻሉ። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ይለቋቸዋል።

በአገር ውስጥ እና ለዓለም አቀፉም ማኅበረሰብ ግንዛቤ የሚሰጡት በእነዚህ ማስረጃዎች ነው።

ወጣት የቡድኑ አባላት ሁሌም ሥልጠና ይሰጣቸዋል።

ሕገ ወጥ ድርጊት ሲገጥማቸው ነገሩን በጉልበት ከመፍታት ይልቅ ለአካባቢው ባለሥልጣናት ማሳወቅ ይመርጣሉ። ጉዳያቸውን ፍርድ ቤትም ይወስዳሉ።

በ2022 ሴቶቹ ተሰባስበው ከእንባ ጠባቂ ተቋም ጋር በመሆን ያደረጉት ንቅናቄም ይታወሳል።

ከ2021 እስከ 2022 ድረስ 700 ሕገ ወጥ ማዕድን አውጪዎች 103 ሄክታር መሬት ላይ ቁፋሮ ማካሄዳቸውን ያጋለጡበት ንቅናቄ ነበር።

ለሕገ ወጥ ቁፋሮ የዋሉ 107 ኤክስካቫተሮች በመንግሥት እንዲወረሱ ምክንያት ሆነዋል።

በ2022 ፍርድ ቤት የተፈጥሮ ሀብት ጉዳትን በተመለከተ ውሳኔ አሳልፏል። ይህም የአገሪቱን የአካባቢ ሚኒስትር ተጠያቂ ያደረገ ነው።

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ አወንታዊ ቢሆንም አሁንም ችግሮች እንዳሉ ሴቶቹ ይናገራሉ።

መንግሥት ተጨባጭ እርምጃ ሊወስድ እንደማይችል ሴቶቹ ያምናሉ። ሆኖም ግን ትግላቸውን አያቋርጥም።

አማዞን

ቆራጥ የሴቶች አመራር

በአካባቢው ወንዶች ከሚሠሩት የጥበቃ ሥራ የእነሱ የተለየ እንደሆነ ሴቶቹ ይናገራሉ።

ሴቶቹ የአካባቢ ጥበቃውን ባህልን ከመጠበቅ ጎን ለጎን ነው የሚያካሂዱት። ለምሳሌ የእጅ ሥራ እና ጌጣ ጌጥ ሥራ አላቸው።

ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘትም ይረዳቸዋል።

“እንዲህ ያለ ቆራጥ የሴቶች አመራር ማኅበረሰቡን ለተሻለ ሥራ ያነቃቃል” የምትለው ሴምርቲጊ ናት።

ሌሎች በአማዞን ደን ውስጥ የሚኖሩ ሴቶችንም አነሳስተዋል።

ጥያቄያቸው የአካባቢ ጥበቃን የሚያረጋግጡ ፖሊሲዎች እንዲኖሩ እና እንዲተገበሩም ነው። ይህም ባህልን ያማከለ ነው።

ፓውላ ሴርዳ የተባለችው ወጣት “እዚህ ያለሁት ለመማር፣ ልምዴን ለማካፈል እና ነጻነቴን ለማግኘት ነው” ትላለች።

የቀደምት ማኅበረሰብ ሴቶች አካባቢያቸውን የሚጠብቁበት እና ቤተሰቦቻቸውን የሚደግፉበትም መንገድ መፍጠር ግባቸው እንደሆነ ትናገራለች።