ጋዜጠኞቹ በቃሉ አላምረው እና በላይ ማናዬ
የምስሉ መግለጫ,ጋዜጠኞቹ በቃሉ አላምረው እና በላይ ማናዬ

18 መስከረም 2024

ለወራት በእስር ላይ የቆዩት ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው እና በላይ ማናዬ ወደ “ሙያቸው መመለስ ስላልቻሉ” ከአገር መሰደዳቸውን ተናገሩ።

የ“አልፋ ሚዲያ” መገናኛ ብዙኃን መስራች የሆነው በቃሉ አላምረው እና የ“የኢትዮ ኒውስ” መገናኛ ብዙኃን መሥራች የሆነው በላይ ማናዬ አገር ጥለው መሰደዳቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ሁለቱ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ከአገር ለመውጣት ከነሐሴ 28፤ 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለአስራ አንድ ቀናት መጓዛቸውን ገልጸዋል።

ጋዜጠኛ በቃሉ “በጣም አስቸጋሪ የሚባለውን መንገድ ተከትለን በእግር፥ በመኪና እና በሞተር ሳይክል ነው የወጣነው። የነበሩብን [የጉዞ] እገዳዎች እና ክትትሎች መደበኛውን የጉዞ መንገድ እንድንጠቀም አላስቻለንም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ሁለቱ ጋዜጠኞች ለወራት ከቆዩበት እስር የተፈቱት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ነበር።

ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው በ2015 ዓ.ም. መጨረሻ ነው። በቃሉ በጊዜው በቁጥጥር ስር የዋለው ከኒው ጀነሬሽን ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ ከተመረቀ ጥቂት ሰዓታት በኋላ ነበር።

ሌላኛው ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ በበኩሉ ባለፈው 2016 ዓ.ም ሕዳር ወር ላይ ነው በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር የዋለው።

ሁለቱም የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በጸጥታ ኃይሎች ከታሰሩ በኋላ አንድ ጊዜ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ነው ከእስር የተለቀቁት። ከእስር ከተለቀቁ ሦስት ወራት ገደማ በኋላ ደግሞ አገር ጥለው ተሰድደዋል።

ጋዜጠኞቹ ከአገር የተሰደዱት በሁለት ምክንያት መሆኑን በቃሉ ለቢቢሲ ገልጿል።

“ከእስር ስንወጣ ያናገሩን የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ሰዎች እና የፌደራል ፖሊስ አባል ከዚህ በኋላ የምናደርገውን እንቅስቃሴ እንደሚከታተሉን ገልጸውልናል” ሲል የመጀመሪያውን ምክንያት ተናግሯል።

በቃሉ አክሎም “ወደ ሙያችን መመለስ ስላልቻልን ያለውን ችግር እና አፈናም መስበር የምንችልበት አቅም ስለሌለን [ከአገር ወጥተናል]” ብሏል።

ጋዜጠኛ በቃሉ አክሎም፤ “ያንን ማድረግ የምንችለበት ዕድል ልናገኝ የምንችለው ከሀገር ስንወጣ ነው፥ መጀመሪያ ሕይወታችንን ማትረፍ አለብን በሚል ነው። በመንግሥት በኩል ሊገድሉን የሚችሉበት ዕድል ነበራቸው በተደጋጋሚ በእስር ቤት ውስጥ የሚነግሩን ያንን ነው። መውጣቱ ሕይወትን ለማትረፍ ያሰብነው ነው፤ ቀጥሎ ደግሞ በሙያችን ለመስራት ያስችለን ይሆናል ብለን የገመትነው ነው” ሲሉ ውሳኔያቸውን አብራርቷል።

“በሙያችን መስራት ነው ዕቅዳችን” የሚሉት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹ፤ “በሀገር ውስጥ ካሉ ችግሮች አንጻር ስንሰራ የነበረውን ስራ የማስቀጠል ፍላጎት ነው ያለን” ብለዋል።