በተለያዩ አካባቢዎች ፍንዳታዎች ደርሰዋል

ከ 4 ሰአት በፊት

በሊባኖስ ገመድ አልባ የመገናኛ መሳሪያዎች ላይ ለሁለተኛ ጊዜ በደረሰ ፍንዳታ ቢያንስ 20 ሰዎች ሲሞቱ ከ450 በላይ መቁሰላቸውን የአገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የታጣቂው ሄዝቦላህ ጠንካራ ይዞታዎች ናቸው በሚባሉት በዋና ከተማይቱ ቤይሩት ደቡባዊ ዳርቻዎች እና በደቡባዊ ሊባኖስ ቡድኑ የሚጠቀምባቸው ‘ዎኪ-ቶኪዎች’ (የሬዲዮ መገናኛዎች) መፈንዳታቸው ታውቋል።

አንዳንዶቹ ፍንዳታዎች የደረሱት ማክሰኞ ዕለት የሄዝቦላህ አባላት ‘ፔጀርስ’ (ሌላ ዓይነት የድምጽ እና የጽሁፍ መልዕክት መለዋወጫዎች) ፈንድተው የጠገደሉ 12 ሰዎች የቀብር ሥነ ሥርዓት በሚከናወንበት ወቅት መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ሄዝቦላህ ለጥቃቱ እስራኤልን ተጠያቂ አድርጓል። እስራኤል በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት አልሰጠችም።

ጥቃቶቹ የደረሱት የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት “የጦርነቱ አዲስ ምዕራፍ” መጀመሩን ካስታወቁ እና የተወሰነው የእስራኤል ጦር ወደ ሰሜን የአገሪቱ ክፍል እንዲሰማራ ከተደረገ በኋላ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በአካባቢው “ከፍተኛ የግጭት መባባስ አደጋ” አለ ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ሁሉም አካላት “ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም” ጥሪ አቅርበዋል።

“እነዚህን ሁሉ መሳሪያዎች እንዲፈነዱ የማድረጉ ምክንያት ከከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ በፊት እንደ ቅድመ መከላከል የሚወሰድ ነው” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

በጋዛ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ከሚካሄደው ጦርነት ጎን ለጎን ለ11 ወራት ዘለቀው በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል ሲካሄድ የቆየው ድንበር ተሻጋሪ ውጊያ ወደ ሁሉን አቀፍ ግጭት ሊያመራ ይችላል የሚል ፍራቻ ከወዲሁ እየጨመረ ነው።

ከረቡዕ ፍንዳታ ከሰዓታት በኋላ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ከሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተፈናቀሉ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩት ዜጎችን “በአስተማማኝ ሁኔታ ወደ ቤታቸው” ለመመለስ ቃል ገብተዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮአቭ ጋላንት በበኩላቸው እስራኤል “በጦርነቱ አዲስ ምዕራፍ እየከፈተች ነው” ካሉ በኋላ “የስበት ኃይሉ ማዕከል ወደ ሰሜን እየተሸጋገረ ነው” ብለዋል።

በቅርቡ በጋዛ የተሠማራው የሠራዊት ክፍል ወደ ሰሜን እንዲዘዋወር መደረጉን የእስራኤል ጦር አረጋግጧል።

በበርካታ ምዕራባዊያን አገራት በአሸባሪነት የተፈረጀው እና በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ በበኩሉ ሐማስን በመደገፍ እየሰራሁ ነው ብሏል። ድንበር ዘለል ጥቃቱን የሚያቆመውም በጋዛ ያለው ጦርነት ሲያበቃ ብቻ መሆኑን ገልጧል።

ቡድኑ በቀጣይ ስለሚወስደው እርምጃ ፍንጭ የሚገኘው የቡድኑ መሪ ሐሰን ናስራላህ ከሚያደርጉት ንግግር ይሆናል ተብሏል።

የሄዝቦላህ የሚዲያ ፅህፈት ቤት ከሁለተኛው የፍንዳታ በኋላ የ16 ዓመት ልጅን ጨምሮ 13 ተዋጊዎቹ መሞታቸውን ረቡዕ ዕለት አስታውቋል።

በተመሳሳይ ቀን በድንበር አቅራቢያ እና እስራኤል በተቆጣጠረችው የጎላን ተራራዎች ላይ የሚገኙ የእስራኤል ወታደሮችን ዒላማ ያደረጉ የሮኬቶች ጥቃቶችን መፈጸሙን ገልጿል።

የእስራኤል ጦር በበኩሉ ረቡዕ ከሊባኖስ ወደ 30 የሚጠጉ ሮኬቶች ተተኩሰው እሳት ከመፍጠር ውጪ ምንም ጉዳት አላደረሱም ብሏል።

የእስራኤል አውሮፕላኖች በደቡባዊ ሊባኖስ የሄዝቦላህ ተዋጊዎችን ዒላማ ማድረጉንም አክሏል።

አንዳንዶቹ ፍንዳታዎች በቀብር ስነ ስርዓት ላይ የደረሱ ናቸው

የረቡዕ ፍንዳታዎች ለሄዝቦላ ሌላ ውርደት ሲሆን፣ አጠቃላይ የመገናኛ አውታሩ በእስራኤል ሰርጎ ገብነት መተብተቡን አመላካች ነው ተብሏል።

ማክሰኞ ዕለት ከሄዝቦላህ የመጣ ነው ተብሎ የታመነ መልዕክት ከደረሳቸው በኋላ በሺህዎች የሚቆጠሩ ‘ፔጀሮች’ በተመሳሳይ ጊዜ በመፈንዳታቸው በርካታ ሊባኖሳውያን ከመደናገጥ ባለፈ ብስጭት ውስጥ ገብተዋል።

በፍንዳታው 12 ሰዎች (የስምንት ዓመት ሴት ልጅን እና የ11 ዓመት ወንድ ልጅን ጨምሮ) ሲሞቱ 2 ሺህ 800 ሰዎች ቆስለዋል ሲሉ የሊባኖስ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ተናግረዋል።

የቢቢሲ ባልደረቦች በደቡባዊ ቤይሩት ዳሂያ ከተማ ከተገደሉት መካከል በአራቱ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ በተገኙበት ወቅት ከፍተኛ ፍንዳታ ሰምተዋል።

በሐዘንተኞች መካከል ትርምስ እና ግራ መጋባት ከመፈጠሩም ባለፈ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎችም ስለተፈጸሙ የፍንዳታ ዘገባዎች መስማት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በአንድ ባልተረጋገጠ የማኅበራዊ ሚዲያ ቪዲዮ ላይ ብዙ ሰዎች በተገኙበት የሄዝቦላህ ሰልፍ በሚመስል ዝግጅት ላይ አነስተኛ ፍንዳታን ተከትሎ አንድ ሰው ሲወድቅ ይታያል።

የሊባኖስ ቀይ መስቀል ከ30 በላይ አምቡላንሶች በዋና ከተማው ደቡባዊ ዳርቻዎች እንዲሁም በደቡባዊ ሊባኖስ እና በቤካ ሸለቆ ለደረሱ ፍንዳታዎች ምላሽ ሰጥተዋል ብሏል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ፍንዳታዎቹ “ያነጣጠሩት ዎኪ-ቶኪዎች” ላይ ነው ብሏል። ለሄዝቦላህ ቅርብ የሆነ ምንጭ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደገለጸውም አባላቱ የሚጠቀሙባቸው ዎኪ ቶኪዎች መፈንዳቸውን ገልጿል።

የሊባኖስ መንግሥት የሚያስተዳደረው ብሔራዊ የዜና አገልግሎት (ኤንኤንኤ) እንደገለጸው በስልክ መሸጫ ሱቅ ውስጥ ዎኪ ቶኪ ፈንድቶ አንድ ሰው ገድሏል።

ማለትም በሰሜናዊ የቤካ ሸለቆ ውስጥ የመገናና መሳሪያዎችን በሚሸጥ ሱቅ ውስጥም ፍንዳታ አጋጥሟል።

መሳሪያው አይኮም-ቪ82 የተባለ በእጅ የሚያዝ የመገናኛ ራዲዮ መሆኑ ታውቋል። ይህ መሳሪያ ጃፓን በሚገኘው የኤሌክትሮኒክስ አምራቹ አይኮም የሚመረት የነበረ ቢሆንም ይህ የመገናኛ ራዲዮ ምርት እንዲቋረጥ ተደርጓል።

ሌላ አይኮም-ቪ82 የመገናኛ ራዲዮ የበአልቤክ ከተማ ዳርቻ ላይ በሚገኝ ቤት ፈንድቷል ሲል ኤንኤንኤ ዘግቧል።

ከሌሎች ሁለት አካባቢዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተለጠፉ ፎቶዎችም ተመሳሳይ ሞዴል የመገናኛ ራዲዮን ያሳያሉ።

አይኮም ያመረታተቸው የመገናኛ ራዲዮዎች ናቸው የፈነዱት ተብሏል

የሮይተርስ የዜና ወኪል የሊባኖስን የደኅንነት ምንጭን ጠቅሶ እንደዘገበው ዎኪ ቶኪዎቹ በሄዝቦላህ የተገዙት ከአምስት ወራት በፊት ነው። ፔጀሮቹ በተመሳሳይ ወቅት ነው የተገዙት።

አክሲዮስ የዜና ድረ-ገጽ ሁለት ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው የእስራኤል የስለላ ተቋማት በሺህዎች የሚቆጠሩ የመገናኛ ራዲዮዎች ለሄዝቦላህ ከመድረሳቸው በፊት አነስተኛ ፈንጂ በድብቅ እንዲገጠምባቸው ተደርጓል።

ቢቢሲ የአይኮም ዩናይትድ ኪንግደም ቢሮን ስለሪፖርቶቹ አስተያየት እንዲሰጠው ጥያቄ ቢያቀርብም ሁሉንም የሚዲያ ጥያቄዎች ጃፓን ለሚገኘው የኩባንያው ዓለም አቀፍ ግንኙነት አስተላልፏል። ቢቢሲ ለአይኮም ጃፓን ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ አላገኘም።

የአሜሪካ እና የሊባኖስ ምንጮች ለኒውዮርክ ታይምስ እና ለሮይተርስ እንደተናገሩት እስራኤል ማክሰኞ ዕለት በፈነዱት ፔጀሮች ውስጥ አነስተኛ መጠን ያላቸውን ፈንጂዎች መትከል ችላለች።

በቤይሩት በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ውስጥ የሚሠሩ የዓይን ሐኪም ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ካዩዋቸው ሰዎች ቢያንስ 60 በመቶ ያህሉ ቢያንስ አንድ ዓይናቸውን ያጡ ሲሆን አብዛኞቹ ደግሞ እጃቸውን አጥተዋል።

“ምናልባት ይህ በሕክምና ሕይወቴ ከሁሉ የከፋው ቀን ነው። የሟቾቹ ቁጥር እና የደረሰው የጉዳት አይነት ከፍተኛ ነው ብዬ አምናለሁ” ሲሉ ዶክተር ኤልያስ ዋራክ ተናግሯል።

“እንደ አለመታደል ሆኖ ብዙ ዓይኖችን ለመታደግ አልቻልንም። በሚያሳዝን ሁኔታም ጉዳቱ በዓይን ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም። አንዳንዶቹ ከፊት በተጨማሪ የአንጎል ጉዳት ደርሶባቸዋል” ብለዋል።